የሌላ ወንድ ልጅ አርግዛ ሳለች የቀድሞ ባሏ በወሊድ ክፍል ገብቶ ልጁን ተቀበለላት፤ ዛሬ ደግሞ የቀድሞ ባሏ፣ የአሁኑ ባሏ እና ልጆቿ በአንድ ላይ እንደ አንድ ቤተሰብ በፍቅር ይኖራሉ!
በባህላችንና በማህበረሰባችን ፈጽሞ የማይታሰብ፣ ብዙዎችን ያስደነገጠና ያስደመመ እውነተኛ የስደት ታሪክ!
በብዙዎቻችን ማህበረሰብ ውስጥ ፍቺ ማለት ቂም፣ በቀል፣ ፍርድ ቤት መመላለስ እና አንዳንዴም ደም መፋሰስ ነው። ይህች ኢትዮጵያዊት እናት ግን በስዊዘርላንድ ምድር የኖረችው ታሪክ ሁሉንም ማህበራዊ ህግጋት የሰበረ እና የሰው ልጅ ደግነት ምን ያህል ጥግ ሊደርስ እንደሚችል ያሳየ ነው።
ታሪኩ የሚጀምረው ከ26 ዓመታት በፊት ነው። ወደ ስዊዘርላንድ ተሰዳ በስደተኞች ካምፕ ውስጥ በሳምንት በ77 ፍራንክ በችግር ስትኖር፣ የመኖሪያ ፍቃድ ለማግኘትና ከአገር ላለመባረር ቶማስ የተባለውን ደግ ስዊዛዊ ታገባለች።
ነገር ግን ከጋብቻው ማግስት ያልታሰበ ከባድ የመንፈስ እና የስነ-ልቦና ህመም ውስጥ ወደቀች። በፍርሃትና በጭንቀት ተውጣ እንደ ሚስት መሆን፣ አብሮ መተኛትም ሆነ ትዳር መምራት ፈጽሞ አቃታት።
በባህላችን አንድ ወንድ ሚስቱ እንደ ሚስት መሆን ካቃታት የሚያደርገው ግልጽ ነው። ቶማስ ግን ያላሰቡትን ታሪክ ጻፈ።
"አንቺ በሁለት እግርሽ ቆመሽ ሙሉ ጤነኛ እስክትሆኚ ድረስ የትም አልጥልሽም፤ ከዚህ በኋላ እንደ ባል ሳይሆን እንደ አባትሽ ሆኜ አስታምምሻለሁ" አላት። ቃሉንም በተግባር አሳየ። ራስን እስከማጥፋት ያደረሳትን ስቃይ ሁሉ እንደ አባት ታግሶ አስታመማት። በዚያ ወቅት ነበር "ባሌ አባቴ ሆነ... ቀረና ትዳሩ" የሚለውን ዝነኛ ዘፈኗን ለእሱ የጻፈችለት።
ነገሩ ግን በዚህ ብቻ አላበቃም! በጣም አነጋጋሪው ክፍል የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው።
ከጊዜ በኋላ በስምምነት ተለያዩ። እሷም ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ከሌላ ሰው ጋር ተዋውቃ አረገዘች።
የፍቺያቸው ጉዳይ ፍርድ ቤት ባለቀበት ቀን የአምስት ወር ነፍሰጡር ነበረች! ይህ ስዊዛዊ የቀድሞ ባሏ ግን ጀርባውን ከመስጠት ይልቅ፦ "የኢትዮጵያን የህክምና ሁኔታ አይቻለሁ፤ የሌላም ሰው ልጅ ቢሆን እዚህ በሰላም በኔ ኢንሹራንስ ሆስፒታል መውለድ አለብሽ" ብሎ ወደ ስዊዘርላንድ አስመጣት።
በወሊድ ሰዓት አብሯት ወደ መውለጃው ክፍል ገባ፤ ልጇን ተቀብሎ አቀፈ፤ የክርስትና አባት ሆኖ በሙሉ ፍቅር አሳደጋት።
ይህም አልበቃ ብሎ፣ ከዓመታት በኋላ እሷ ሌላ አዲስ ባል አግብታ ሁለተኛ ልጅ ስትወልድ፣ አዲሱን ባሏንና ልጆቿን ይዛ ስዊዘርላንድ ስትመጣ የተቀበላቸው ይኸው የቀድሞ ባሏ ቶማስ ነበር! ለሁለት ወራት ያህል በአንድ ቤት ውስጥ አብረው ኖሩ።
ዛሬም ድረስ አዲሱ ባሏ ሄዶ የቶማስን ግቢና አትክልት ያስተካክላል፤ ቶማስ ደግሞ ለልጆቹ ልብስ እየገዛ፣ ዋና እያስተማረ እንደ አያትና እንደ አባት ሆኖ ይንከባከባቸዋል። በማህበረሰባችን ውስጥ ለግድያ የሚፈላለጉ የቀድሞና የአሁን ባሎች፣ እዚህ ጋር እንደ ወንድማማች ተቃቅፈው ይኖራሉ!
ነገር ግን የዚህች እናት ታሪክ ትልቁ እና መራራው አነጋጋሪ ርዕስ ይሄ ብቻ አይደለም፤ የገዛ ቤተሰቦቿ የፈጸሙባት ክህደት እንጂ!
ለቤተሰቦቿ የመጀመሪያ የስደት በር ከፋች ሆና፣ ከኮንቴነር ልብስ እየለበሰች፣ ራሷን ረስታ ገንዘብ ስትልክ ኖራለች። እህትና ወንድሞቿን አውሮፓ ድረስ እንዲመጡ መንገድ ከፍታለች። ነገር ግን እሷ ታማ፣ አእምሮዋ ተጨንቆ፣ ስራ መስራት አቅቷት እጇ ባጠረ ጊዜ የገዛ ደሟ የሆኑት ቤተሰቦቿ ጀርባቸውን ሰጧት።
"ቤተሰብ ለፎቶ የሚሆን መልክ ስታጣ አብሮህ መቆም አይፈልግም! የስደተኛ ዘመዱ ገንዘቡ ብቻ ነው!" ስትል በቁጭት ትናገራለች። "ችለህ ያላደረግከውን ሳይሆን፣ ሳትችል የቀረኸውን ብቻ ይዘው ያኮርፉሃል፤ ያገልሉሃል፤ ስምህን ያጠፋሉ።"
ለዚህም ነው በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የዲያስፖራ ወገኖች እጅግ አከራካሪና ድፍረት የተሞላበትን ይህንን ምክር የሰጠችው
"75% ለራስህ ኑር፤ ለቤተሰብህ የምትሰጠው 25% ብቻ ይሁን! ለቤተሰብ እረዳለሁ ብለህ ሳታገባ፣ ሳትወልድና ራስህን ሳትሰራ እድሜህን አትጨርስ። ካልሰጠህ አትሰደብም፤ ትንሽ ስትሰጥ ግን እንደተከበርክ ትኖራለህ። የስደተኛ ዘመዱ ጤናውና ኪሱ ያለው ገንዘብ ብቻ ነው!"
የባዳው ፈረንጅ እንደ አባት ሆኖ ሲታደጋት፣ የገዛ ቤተሰቧ ግን የገንዘብ ምንጭነቷ ሲያበቃ ፊታቸውን አዙረውባታል። ከብዙ አመታት የስቃይ መንገድና የጸበል ፈውስ በኋላ፣ ዛሬ ላይ ፈጣሪዋን በዝማሬ እያመሰገነች ከባለቤቷ፣ ከልጆቿ እና ካልተለያት መልካም ሰው ከቶማስ ጋር በሰላም ትኖራለች።
ደም ሁልጊዜ ዘመድ አይሆንም፤ አንዳንዴ እውነተኛው ቤተሰብ በፈጣሪ ልብ ውስጥ የተመረጠ ባዳ ነው!
Via፦ አሀዱ ሚዲያ
ግዮን ማለዳ
@GhionMaleda