የፍ/ሕ/ቁ.1179 ተፈጻሚ የማይሆንባቸው ልዩ ጉዳዮች
#የታወቀ ግንኙነት መኖር
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት
የፍ/ሕ/ቁ.1179 ተፈጻሚነት የሚኖረው በባለይዞታውና በዚህ ይዞታ ላይ ቤት በሰራው ሰው መካከል የታወቀ ግንኙነት በሌለበት ሁኔታ ብቻ ነው በማለት በሰ/መ/ቁ. 189608 (ቅጽ 25) የሰጠው ትርጉም በጉዳዩ ላይ ገዢ ትርጉም ነው።
ይህንን ገዢ ትርጉም መሰረት በማድረግ የታወቀ ግንኙት የሚለውን ዘርዝር አድርገን አንድ በአንድ እናያለን።
#የውል ግንኙነት
የውል ግንኙነት የታወቁ ግንኙነቶች ሊባሉ ከሚችሉት ግንኙነቶች መካከል አንዱ ነው። የውል ግንኙነት ሲባል የሽያጭ ውል፣ የስጦታ ውል፣ የመያዣ ውል፣ የአገልግሎት ትውስት ውል ወዘተ ያካትታል። እነዚህን ልዩ ልዩ የውል ግንኙነቶች መሰረት አድርገው በሚነሱ ክርክሮች ላይ የፍ/ሕ/ቁ.1179 ድንጋጌ ተፈጻሚነት ምን ይመስላል የሚለውን አንድ በአንድ ማየት ያስፈልጋል።
#የሽያጭ ውል
አንድ በሽያጭ ውል ቤት የገዛ ሰው በገዛው ቤት ጊቢ ውስጥ ቤት ይሰራል። ከዚያ በኋላ ውሉ በተለያዩ ምክንያቶች ሲፈርስና ወደ ነበሩበት የመመለስ ጉዳይ ሲነሳ ገዢው በገዛው ቤት ጊቢ ውስጥ የሰራውን ቤት ተቃውሞ ሳይቀርብብኝ የሰራሁት በመሆኑ የግል ንብረቴ ነው በማለት ሲከራከር ይስተዋላል። ፍ/ቤቶችም የተለያዩ ውሳኔዎች ሲወስኑ ቆይተዋል። በመጨረሻ ጉዳዩ በመ/ቁ. 49326
(ቅጽ 10) የቀረበለት ሰበር ሰሚ ችሎት ይህ ክርክር መታየት ያለበት በውል ሕግ አንቀጽ 1818 መሰረት እንጂ በፍ/ሕ/ቁ.1179 መሰረት አይደለም በማለት መሰረታዊ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል። ይሄው ሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ. 189608 (ቅጽ 25) በሰጠው ውሳኔ ጉዳዩን ዘርዘር አድርጎ በማየት ውሉ መፍረሱን ተከትሎ በውሉ መሰረት በቦታው ላይ የተሰራን ቤት ሕጋዊ ውጤት አስመልከቶ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1179 ተፈጻሚነት የለውም።
ይህ ድንጋጌ ተፈጻሚነት የሚኖረው በግራ ቀኙ መካከል የታወቀ ግንኙነት በሌለበት ሁኔታ ብቻ ነው የሚል ትርጉም ሰጥቷል። ይህም የውል ሕግን ከንብረት ሕግ ጋር በማምታታት ሲፈጠሩ የነበሩ የሕግ አተረጓጓም ችግሮችን የፈታ ተገቢ ትርጉም ነው።
#የኪራይ ውል
የኪራይ ውል ሌላው አንድ ሰው የሌላን ሰው ይዞታ የሚይዝበት የታወቀ ግንኙነት ነው። አንድን ቤት ወይም ይዞታ የተከራየ ሰው በኪራይ በያዘው ይዞታ ላይ ቤት ሊሰራ ይችላል። የኪራይ ውሉ ፈርሶ ግራ ቀኙ ወደነበሩበት የሚመለሱበት አግባብ ሲታይ ተከራዩ ተቃውሞ ሳይቀርብብኝ የሰራሁት ቤት የግሌ ይባልልኝ የሚል ክርክር ሲያቀርብ ይስተዋላል። ይሁን እንጂ እንደ ሽያጭ ሁሉ በኪራይ ውልም ተከራዩ ቤቱን የያዘው በአንድ በግራ ቀኙ መካከል መብት እና ግዴታን በሚያስቀምጥ የውል ግንኙነት ነው። የተለየ ድንጋጌ ከሌለው በስተቀር የኪራይ ውል በዋናነት ለተከራዩ ቤቱን የመጠቀም መብት ለአከራዩ ደግሞ ኪራይ የመቀበል መብት የሚሰጥ ውስን ግንኙነት ነው። በዚህም መሰረት በአከራዩ በኩልም በኪራዩ ቤት ይዞታ ውስጥ ተከራዩ ለራሱ ቤት ይሰራል የሚል እሳቤ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም። አከራዩ ቤቱ ሲሰራ አውቆ ሳይቃወም ቢቀር እንኳን ያልተቃወመው የኪራይ ውሉ ጊዜ ሲያልቅ ወይም ውሉ ሲፈርስ በሕግ በተቀመጠው አግባብ መብቴን አስከብራለሁ በማለት እንጂ ተከራዩ የሰራው ቤት ባለቤት ይሆናል በሚል እሳቤ ነው ሊባል አይችልም። በተከራዩ በኩልም በውል በያዘው ይዞታ ላይ ወደፊት በፍ/ሕ/ቁ.1179 በተደገነገገው የህግ አግባብ ባለቤት የሚሆንበት ቤት የመስራት ሀሳብም ሆነ ለዚህ ሀሳብ መሰረት የሚሆን ሁኔታ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም። በመሆኑም ከላይ በተጠቀሰው በሰ/መ/ቁ. 189608 (ቅጽ 25) በተሰጠው ውሳኔ ላይ በተቀመጠው ተመሳሳይ ምክንያት በተከራየው ይዞታ ላይ ቤት የሰራ ሰው ቤቱን ስሰራ ተቃውሞ አልቀረበብኝም በማለት የቤቱ ባለቤት ለመሆን ጥያቄ ማንሳት አይችልም። የፍ/ሕ/ቁ.1179 ድንጋጌም ለዘህ ተከራይ ተፈጻሚነት የለውም።
#አብሮ የመኖር ስምምነት
አሁን አሁን ህንጻ መገንባት የማይችሉ ባለመሬቶች መሬታቸውን ህንጻ ለሚሰራ አልሚ ይሰጡና በመሬታቸው ላይ በተሰራው ህንጻ ላይ በአንዱ ቤት ለመኖር ስምምነት ሲያደርጉ ማየት የተለመደ ሆኗል። እንደዚህ መደበኛ በሆነ መንገድ ባይሆንም አቅም የሌለው መሬት አቅርቦ አቅም ያለው ደግሞ ቤቱን አቁሞ አብሮ ለመኖር የሚደረጉ ስምምነቶች አልፎ አልፎ የታዩ ማህበራዊ ሁነቶች ናቸው።
ይሁን እንጂ ግንኙነቱ እንከን ቃሉ ደግሞ ክህዴት ይገጥመውና አለመግባባቶች ይነሳሉ። ባለመሬቱ መሬቴን ለቀህ ውጣ ሲል ቤት ሰሪው ደግሞ እንዲያውም ቤቱን ሳትቃወመኝ ስለሰራሁ የግል ንብረቴ ነው ያዝከቅን ቤት ለቀህ ውጣልኝ ይላል። ይህ ክርክር በሰ/መ/ቁ.219783 የቀረበለት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ የፍ/ሕ/ቁ.1179 ተፈጻሚ ለማድረግ ቤቱ ለገንቢው የግል ጥቅም ብቻ ተብሎ ተሰራ መሆን አለበት። የባለመሬቱ ዝምታም ይህንን እያወቀ የተደረገ መሆን አለበት። ቤቱ የተሰራው በሰሪው በተሰራው ቤት ላይ አብሮ ለመኖር በተደረገ ስምምነት ከሆነ በስምምነቱ መሰረት ይፈጸማል እንጂ
በፍ/ሕ/ቁ.1179 መሰረት የገንቢ የግል ንብረት አይሆንም በማለት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ ውስጥ በፍ/ሕ/ቁ.1179 መሰረት ባለመብት የሚያደርገው በራስ ገንዘብና ጉልበት ተቃውሞ ሳይቀርብ መስራት ብቻ ሳይሆን ባለይዞታው ሳይቃወም እና ሌላ ስምምነት ሳይኖር ብቸኛ ባለመብት ለመሆን ታስቦ መሰራቱ ነው በማለት ለሕጉ ተጨማሪ ትርጉም ሰጥቶታል። በመሆኑም ቤቱ የተሰራው በእንዲህ ዓይነት ግንኙነት ከሆነ ይህ ሕግ ተፈጻሚነት አይኖረውም።
https://t.me/LawStudentsUnion
https://t.me/LawStudentsUnion
https://t.me/LawStudentsUnion