ሚያዝያ ፳፯ /27/
በዚች ቀን የከበረ ቅዱስ ፊቅጦር በሰማዕትነት አረፈ።
የዚህም ቅዱስ አባት ጣዖት አምላኪና የዲዮቅልጥያኖስ የሠራዊቱ አለቃ ነበር። ጣዖት ስለ ማምለኩም አባቱን ዘወትር የሚገሥጸው ሆነ አባቱም ወደ ንጉሥ ከሰሰው እንጂ አልሰማውም።
መኰንኑም ወደርሱ አቅርቦ ብዙ ሸነገለው ባልሰማውም ጊዜ ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ በብዙም አሰቃዩት ከሚነድ እሳት ውስጥ ጨመሩት ሙጫ አደሮ ማርና ዘይትን አፍልተው በላዮ ደፉበት በማበራያም አበራዩት አፉንም በአሞትና በእሬት አመረሩት ዐይኖቹንም አወለቁት ደግመውም ዘቅዝቀው ሰቀሉት።
የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ተገልጾለት አዳነው።
አንዲት ዓሥራ አምስት ዓመት የሆናት ብላቴና ቅዱስ ፊቅጦርን ሲአሠቃዩት በቤቷ መስኮት ታየው ነበር።
መላእክትንም በእጆቻቸው አክሊሎችን ይዘው እነርሱም በቅዱስ ፊቅጦር ራስ ላይ ሲያኖሩአቸው አይታ እንዴት እንዳየች ለአሕዛብ ነገረቻቸው እጅግም አደነቁ። ከእርሳቸውም ብዙዎች በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት አረፉ።
ያቺም ብላቴና በጌታችን አመነች መኰንኑም ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። የሕይወት አክሊልንም ተቀበለች ሁለተኛም የአመኑትን ሁሉ ራሳቸውን እንዲቆርጡአቸው አዘዘ የሕይወትንም አክሊል ተቀበሉ።
ከዚህም በኋላ የከበረች የቅዱስ ፊቅጦርን ራስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ተጋድሎውንም ፈጽሞ የሕይወትና የድል አክሊልን ተቀበለ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
@sebhwo_leamlakne
🦋🦋🦋🦋🦋🦋🦋🦋🦋🦋🦋🦋🦋🦋🦋