የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ነው ያዘዙት በሚል 6 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮች ለፋኖ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የባህርዳር በረራ መሳሪያ ልካችኋል በሚል እንዲታሰሩ መደረጉ ተሰማዘንድሮ ከፋኖ እና ከመከላከያው ውጊያ ጋር ተያይዞ በየእስር ቤቱ በሚፈረበረከው የክስ ዓይነት የሚታሰሩ ዜጎች ጉዳይ ይገርማል ይላሉ የዘ-ሐበሻ የደህንነት ምንጮች። ስማቸው እንደ ሸዋንግዛው የመሳሰሉ ሰዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ እንኳን ጭምር መንቀስቀስ የማይችሉና በመታወቂያቸው እየተለየ በኮማንድ ፖስቱ እንደሚታሰሩ ከዚህ ቀደም የዘገብን ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ የደህንነት ምንጮች ያደረሱን መረጃ ከማስገረምም አልፎ የደረስንበትን አደገኛ ሁኔታ የሚያሳይ ሆኖ አግኝተነዋል።በኢትዮጵይ አየር መንገድ በተለያየ ኃላፊነት የሚሰሩ ስድስት አመራሮች እና እንዲሁም የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ሹፌር ከፋኖ ጋር ተጠጥርጥረው በሃሰተኛ ክስ አዋሽ 7 እና አዋሽ 40 እየማቀቁ እንደሆነ የደህንነት ምንጮች ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት የአየር ኃይሉ አዛዥ ጀነራል ይልማ መርዳሳ ናቸው ያዘዙን በሚል የአየር መንገዱ የግሩፕ ሴክዩሪቲ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሄርጳ አዱኛ እና የአየር መንገዱ የሴኩሪቲ ኢንቨስቲጌሽን ማኔጀር አቶ ግርማ በኬ በብሔራቸው አማራ የሆኑ ስድስት የአየር መንገዱን የሥራ ሃላፊዎች ለፋኖ በባህርዳር በረራ የጦር መሳሪያ ልካችኋል በሚል ሃሰተኛ እና ;አስቂኝ; በተባለ ክስ አስረዋቸው አዋሽ አርባ እና አዋሽ 7 በእስር እንደሚማቅቁ የደህንነት ምንጮቹ ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል።የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ሹፌር የሆነው ደምስ፣ አለበል ሁነኛው፣ የኔሰው አረጋ፣ አቤል አላምረው፣ አበራ ተገኔ፣ ስንታየሁ ደምሴ እና ሌሎችም ከታሰሩት መካከል ሲሆኑ ወ/ሮ ፋሲካ የተባለችው የደረሰች ነፍሰ ጡርም እንዲሁ በፋኖ ሰበብ ወደ ባህርዳር በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ጦር መሳሪያ አዘዋውረዋል በሚል የመንግስትን የኤርፖርት ሴኪውሬቲ በሚያዋርድ መልኩ ሃሰተኛ ክስ ተመርቶባቸው መታሰራቸን የደህንነት ምንጮች ገልጸው፤ ወ/ሮ ፋሲካ ትፈታ አትፈታ ባያረጋግጡም ሌሎቹ ግን አሁንም በአዋሽ አርባ እየማቀቁ እየተሰቃዩ ይገኛሉ ብለዋል።እነዚህ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች የቦርዱ ሊቀመንበር ጀነራል ይልማ መርዳሳ አዘውን ነው በሚል በሄርጳ አዱኛ እና በአቶ ግርማ በኬ ፋኖ ናቸው በሚል እንዲታሰሩ የተደረገው ቦታቸውን ለሌላ ለመስጠት እንጂ በድርጊቱ ተሳትፎ ኖሯቸው አይደለም የሚሉት የደህንነት ምንጮች፤ በአሁኑ ወቅት የአየር መንገዱ ሠራተኞች በሰራተኞች ላይ እየደረሰ ባለው እንዲህ ያለው ሃሰተኛ ክስ መማረር ውስጥ ወድቋል ብለዋል። በተለይም እነዚህን የታሰሩ ሰዎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ለመጠይቅ በሄዱበት ወቅት ስማቸው ተመዝግቦ ማስፈራሪያ ጭምር እንደደረሰባቸው የሚገልጹ ሠራተኞች የአየር መንገዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹፌር ያሰሩትም አቶ መስፍንን በጫና ሥራውን እንዲለቅ እነ ጀነራል ይልማ መርዳሳ ካላቸው ፍላጎት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ጀነራል ይልማ መርዳሳ አዞናል የሚሉት ሄርጳ አዱኛ እና ግርማ በኬ በአየር መንገዱ ሃሰተኛ ክስ በመፍጠር ሰራተኞችን እያጎሳቆሉ ነው የሚሉት የደህንነት ምንጮች በተለይ የአማራ ተወላጅ የሆኑ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ተማረው ሥራ እንዲለቁ የማይቆፍሩት ድንጋይ የለ ይላሉ። ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከማዳከም ውጭ ሌላ ተልዕኮ ሊኖረው እንደማይችል ነው እየተገለጸ ያለው። በጉዳዩ ላይ ዘ-ሐበሻ ሄርጳ አዱኛ እና አቶ ግርማ በኬን አግኝቶ ምላሻቸውን ለማካተት ያደረገው ጥረት ስልካቸው ባለመነሳቱ አልቻለም።የታሰሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ካለምንም ፍርድ በአዋሽ 7 እና በአዋሽ 40 በስቃይ ላይ ሲሆኑ አዳንዶቹም ህመም ላይ መሆናቸውን የደህንነት ምንጮቹ አክለዋል።