፩ኛ፦ ጠንቅቀን በማናውቀው ጉዳይ ላይ መናጆ/አንጃ ሆነን አስተያየት አለመስጠት መልካም ነው።
፪ኛ፦ የዕውቀታችንን ምንጭ መመርመር መልካም ነው። ከልምድ ነው? ከመጽሐፍ ነው? ከመምህር ነው? ከመሰለኝ ነው? ከምንድን ነው?
፫ኛ፦ የሰውን አለማወቅ እንደ Advantage ተጠቅሞ ማታለል አይገባም። ለምሳሌ ማንኛውም ክርስቲያን ንስሓ ገብቶ ሥጋውን ደሙን መቀበል ይገባዋል። ወደ ገጠር ስንሄድ ግን ወጣት አይቆርብም እያሉ አንዳንድ ሰዎች ሲከለክሉ ይስተዋላል። ይህ ስሕተት ነው። አንዱ መምህር ሄዶ ንስሓ እየገባችሁ ሥጋውን ደሙን ተቀበሉ ቢል ሰው ከልምዱ ተነሥቶ ሊጠላው ይችላል። የተናገረው ግን እውነት ነው። ሌላ እወደድ ባይ መምህር አዎ ወጣት መቁረብ የለበትም ብሎ ሕዝቡ የሚያቀርባቸውን አመክንዮዎች ቢያቀርብ ሕዝቡ ደስ ሊለው ይችላል። ሕዝቡም የዚህ ደጋፊ ሊሆን ይችላል። መማር እንደዚህ ነው ሊልህ ይችላል። እውነታው ግን የላይኛው ነው። በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ የሐሰት ፈጠራ ይልቅ እግዚአብሔራዊውን እውነት ተናግሮ ከመሸበት ማደር ይገባል።
፬ኛ፦ ፈሪሳዊነትን እናስወግድ። ፈሪሳውያን በእግዚአብሔር ቃል ላይ የራሳቸውን ወግ እየጨመሩ ያስተምሩ ነበር። ለወጋቸው መጽሐፋዊ ወይም ቅዱስ ትውፊታዊ የሆነ ማስረጃ የላቸውም። ግን ሕዝቡ ወጋቸውን እንደ ጽጽቅ እንዲያይላቸው ይጥሩ ነበር።
፭ኛ፦ ክፉ ነገሮችም፣ መልካም ነገሮችም በትውፊት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፉ ይችላሉ። እኛ ቅዱስ ትውፊትን መቀበል አለብን። ቅዱስ ትውፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ የተመሠረተ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ የሚቃረን ከሆነ ትውፊት ቢሆንም እንኳ ቅዱስ ትውፊት ስላልሆነ አንቀበለውም።
፮ኛ፦ እግዚአብሔር ልብን የሚመረምር ስለሆነ ከእያንዳንዱ ሐሳባችን፣ ንግግራችን፣ ተግባራችን ጀርባ ያለውን ጉዳይ መመርመር ይገባናል። ከፍቅር ተነሥተን ነው? ከጥላቻ ተነሥተን ነው? ለሃይማኖታችን ከማሰብ ነው? ከአንጃነት ነው? ከምቀኝነት ነው? ከቅንዐት ነው? እግዚአብሔርን ከመውደድ ነው? በጠቅላላው ልባችንን እንፈትሽ። በእያንዳንዱ ንግግራችን፣ በእያንዳንዱ ሐሳባችን፣ በእያንዳንዱ ተግባራችን በእግዚአብሔር ፊት እንመዘንበታለንና።
፯ኛ፦ አንዳንዱ ሊሳደብ፣ ክፉ ስም ሊሰጥ ይችላል። አንዳንዱ ደግሞ ሊዋሽ ይችላል። በዚህ ጊዜ ስድቡን ቸል ብሎ ጉዳዩ ላይ ማተኮር መልካም ነው። ታግሠው ሲቀበሉት የበረከት ምንጭ ነውና። (አንዳንዱ የማስረዳት አቅም ሲያጥረው ስድብን እንደ አማራጭ ሊጠቀም ይችላል። ስለዚህ የሰውየውን ድክመቱን መረዳትና ንቆ መተው መልካም ነው)።
፰ኛ፦ ንግግሮችን፣ ጽሑፎችን ከነዐውዳቸው ለመረዳት መጣር ይገባል።
፱ኛ. ሟች መሆናችንን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም። መቼ እንደምንሞት ስለማናውቅ ከመሞታችን በፊት መሥራት አለብን ብለን ያሰብነውን ጉዳይ ለመፈጸም መትጋት ይገባናል።
፲ኛ፦ አጥፍተን ከነበረ ይቅርታ ማለትን እንልመድ። ትሑት ልቡናን ገንዘብ እናድርግ። ፈሪሀ እግዚአብሔርን እናስቀድም።
© በትረ ማርያም አበባው
@EotcLibilery @EotcLibilery @EotcLibilery