እየፀደቁ ያሉ አዋጆች ለሕዝብና ለአገር የሚኖራቸው ፋይዳ ይታሰብበት!
በ ሪፓርተር
መንግሥት በስኬት አገር ለማስተዳደር ሕጎችን ሲያወጣም ሆነ ፖሊሲ ሲነድፍ፣ የሚቀርቡለትን ምክረ ሐሳቦች በአግባቡ ማስተናገድ ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም፡፡ ቀደም ሲል በነበሩ ዓመታት የተለያዩ ሕጎች ተረቀው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲቀርቡ የሕዝብ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ዕድሉ ቢኖርም፣ ነገር ግን በምክር ቤት አባላትም ሆነ በሌሎች ተሳታፊዎች የሚሰጡ ሐሳቦች ወደ ጎን ተገፍተው ብዙ ችግሮች መፈጠራቸው አይዘነጋም፡፡ በአንድ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይቀር ጥራት የሌላቸው ሕጎች እየወጡ እንደገና ማሻሻያ ረቂቆች ሲቀርቡ ትችቶች መሰንዘራቸው ይታወሳል፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ አፋኝ የተባሉት የሚዲያ፣ የፀረ ሽብርተኝነትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጆች አገር እንደሚጎዱ ብዙዎች በልመና ሳይቀር ተማፅነው አሻፈረኝ ተብሎ ያደረሱት በደል የሚረሳ አይደለም፡፡ የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ በቅድሚያ እነዚህን አፋኝ አዋጆች የመለወጡ ምክንያትም ይታወቃል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከታታይ የተለያዩ ሕጎች እየተረቀቁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢቀርቡምና የሕዝብ አስተያየት መድረኮች ቢዘጋጁም፣ አሁንም በግብዓትነት የሚቀርቡ የሕዝብ አስተያየቶች በአግባቡ ባለመደመጣቸውና በቂ ክርክሮች ባለመደረጋቸው ቅሬታዎች እየተሰሙ ነው፡፡ ሰሞኑን ለፀደቁት የንብረት ታክስና የንብረት ማስመለስ አዋጆች ቀደም ሲል በተከታታይ በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶችም ሆኑ የምክር ቤት ውሎዎች በርካታ ግብዓቶች ቢሰባሰቡም፣ እንደ ወረዱ ነው የፀደቁት ተብሎ የተቃውሞ ድምፆች እየተሰሙ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው በሕገወጥ መንገድ የተፈራ ንብረት ጥያቄ ሊነሳበት ይገባል እንደማይል ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ንብረት ወደኋላ አሥር ዓመት ተሂዶ ጥያቄ ለምን እንደሚነሳበት በቂ ማብራሪያ ያስፈልገዋል፡፡ ንብረቱ ላይ ትኩረት ተደርጎ የወንጀል ተጠያቂነት አለመኖሩም ሌላው የሚነሳ ነጥብ ነው፡፡ አፈጻጸም ላይ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥያቄ ሲነሳ በቂ ምላሽ ይፈልጋል፡፡ የንብረት ታክሱም ጉዳይ ቢሆን ኑሮ እንደሚያከብድ አያጠራጥርም፡፡
ነገ ተነገ ወዲያም እንደ ሚዲያ ነፃነት የመሳሰሉ ሕጎች በባለድርሻ አካላት የቀረቡባቸው ጠቃሚ ግብዓቶች ተካተው ካልቀረቡ፣ የሕዝብ አስተያየቶችም ሆኑ የሕዝብ ውክልና ያላቸው የምክር ቤት አባላት ድምፅ አለመደመጥ ተጨማሪ ችግሮች ከመጥራት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሕግ አውጭው፣ ሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው አካል ሚዛናዊ የእርስ በርስ ቁጥጥር እያደረጉ ካልሠሩ ዞሮ ዞሮ የምትጎዳው አገር ናት፡፡ ትናንት ሲፈጸሙ የነበሩ ስህተቶች አንዳችም ለውጥ ሳያደርጉ ዛሬም የሚደገሙ ከሆኑ፣ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ እንኳንስ ተነጋግሮ ለመግባባት ዓይን ለዓይን መተያየት ያዳግታል፡፡ መንግሥት የሚያወጣቸው ሕጎችም ሆኑ የሚነድፋቸው ፖሊሲዎች ለሕዝብ አስተያየት ከመቅረባቸው በፊት ግራና ቀኙን በሚገባ ያማተሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድም በሁሉም መስኮች ካሉ በዕውቀትና በልምድ ከዳበሩ ባለሙያዎች ጋር መመካከር ብዙ ችግሮችን በቀላሉ ይቀርፋል፡፡
ዜጎች በአገራቸው ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩ መንግሥት ከማንም የበለጠ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሕጎች ሲወጡ ከምንም ነገር በላይ የዜጎችን አማካይ ፍላጎት መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕጎች ጥቂቶችን ተጠቃሚ እያደረጉ ብዙኃኑን እንዳያስከፉ መንግሥት መጠንቀቅ አለበት፡፡ በዜጎች መካከል ልዩነት እንዳይፈጠርና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲኖር፣ ሕጎች ሚዛናዊና የሁሉንም ወገኖች ፍላጎት ያካተቱ እንዲሆኑ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሕጎች ከማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ጫና ነፃ ሆነው ሲወጡ አተገባበራቸው አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ የፖለቲካ ጫና ሲበረታ ግን ከሕግነት ይልቅ የጉልበት አጀንዳ አስፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ቀደም አወዛጋቢ የነበሩ ሕጎች ያስከተሉት ጥፋትና ጉዳት እየታሰበ፣ እንደገና ወደ እዚያ ዓይነቱ መራር ትውስታ ላለመመለስ ይታሰብበት፡፡ በሕግና በሥርዓት መተዳደር ለአገር ህልውናም ሆነ ለሕዝብ ደኅንነት በጣም ጠቃሚ ስለሆነ፣ ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ለሚለው ሥጋት ሲባል ጥንቃቄ ይደረግ፡፡
ከሕግ አወጣጥና ከፖሊሲ ቀረፃ በተጨማሪ መንግሥት በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚና በሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች የተለያዩ ውሳኔዎችን ሲያስተላልፍም ሆነ ዕርምጃ ሲወስድ በሚገባ የተጠኑ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ በውሳኔዎቹ ወይም በዕርምጃዎቹ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ በሰከነ መንገድ መመርመር ተገቢ ነው፡፡ ድጋፍ ሲገኝ በደስታ መቀበል እንዳለ ሁሉ ተቃውሞ ሲሰማም ሥርዓት ባለው መንገድ ማስተናገድ የመንግሥት አንዱ ኃላፊነት ነው፡፡ ለምሳሌ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተደርጎ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጉርምርምታ ሲሰማ የጠላት ወይም የከሃዲ ድምፅ ማስመሰል ተገቢ አይደለም፡፡ መንግሥትን መልካም ሥራ አከናውነሃል በማለት ተደስተው የሚያመሠግኑትን ያህል፣ በተከናወነው ሥራ ወይም በተላለፈው ውሳኔ ደስተኛ ያልሆኑ የተቃውሞ ድምፅ ቢያሰሙ ሊገርም አይገባም፡፡ ይልቁንም ለምክንያታዊ የሐሳብ ልውውጥ የሚረዱ መድረኮችን ማመቻቸት ይጠቅማል፡፡ ከፋይዳ ቢስ ጭብጨባ ይልቅ ምክንያታዊነት ላይ የተመረኮዘ ትችት ማስተናገድ ያስከብራል፡፡
ባለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ እያለፈችባቸው ያሉ ከባድ ችግሮች ጥለዋቸው የሚያልፉ ጉዳቶች ይታወቃሉ፡፡ በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተካሄዱና እየተካሄዱ ያሉ አውዳሚ ጦርነቶች በአገርና በሕዝብ ላይ ያደረሱት ጉዳት ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶችና ውጊያዎች የተፈጠሩ ጉዳቶች የፈጠሩት ቁርሾ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ መከራዎች በደረሱባት አገር ውስጥ ለዘለቄታዊ ሰላም የሚያግዙ ንግግሮች እንዲደረጉ መድረኩን ማመቻቸት፣ እንዲሁም በውጊያ ውስጥ ካሉና በተለያዩ ምክንያቶች ካኮረፉ ወገኖች ጋር ተቀራርቦ ለመወያየት የሚያስችሉ አማራጮች ላይ ትኩረት አልተደረገም፡፡ ይልቁንም ከዛሬ ነገ የተሻለ ነገር የሚጠብቁ ወገኖችን ጭምር ለአመፅ የሚጋብዙ ድርጊቶች ሲስተዋሉ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል፡፡ ሕጎች ሲረቀቁ ከሥጋትና ከጥርጣሬ ይልቅ ተስፋ ይጫሩ፡፡ ለሕግ አወጣጥም ሆነ ለፖሊሲ የሚጠቅሙ ሐሳቦችም ይደመጡ፡፡ በተለይ እየፀደቁ ያሉ አዋጆች ለሕዝብ ጥቅምና ለአገር ህልውና የሚኖራቸው ፋይዳ ይታሰብበት!
እርስዎስ ምን ይላሉ?