ፖሊስ ጣብያዎች ከደንብ ማስከበር ጋር በመሆን ገንዘብ በመቅጣት ገቢ እንዲያስገቡ መታዘዛቸው ተሰማ
- "እያንዳንዱ የፖሊስ ጣብያ በቅጣት የሚያስገባው የገንዘብ ኮቴ ተጥሎበታል፣ በዛሬው እለት ብቻ 4.2 ሚልየን ብር ተሰብስቧል"
(መሠረት ሚድያ)- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የፖሊስ አባላት ከደንብ ማስከበር ጋር በመሆን ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን ገንዘብ በመቅጣት ገቢ እንዲያስገቡ መታዘዛቸው ታውቋል።
ለመሠረት ሚድያ የደረሰው ጥቆማ እንደሚያሳየው የየክፍለ ከተማው ስራ አስፈፃሚዎች በየጊዜው የፖሊስ አዛዦችን እየሰበሰቡ ገንዘብ በተለይ ከነጋዴዎች እና ድርጅቶች በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲሰበስቡ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል።
"በእያንዳንዱ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ከላይ የተወሰነ ኮታ አለ፣ ያንን በተሰጠን ጊዜ ገደብ ሰብስበን ማስገባት ግዴታችን ነው" ብለው ቃላቸውን የሰጡ አንድ የፖሊስ ኢንስፔክተር በዚህ ምክንያት ፖሊስ መደበኛ ስራውን ጥሎ ቤት ለቤት እና በየድርጅቱ ገንዘብ ሲጠይቅ ይውላል ብለዋል።
ሌላኛው ደግሞ "ገንዘብ ከምንሰበስብባቸው መንገዶች መሃከል ከደንብ ማስከበር ጋር በመሆን ገንዘብ መቅጣት፣ አስገዳጅ የህዳሴ ኩፖን ማስገዛት፣ ለኮሪደር ልማት በሚል ከነጋዴዎች መዋጮ መጠየቅ ናቸው ያልተስማማ ካለ የንግድ ፈቃድ እስከመታገድ ይደርሳል" በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል።
ከሰሞኑ በርካታ የመንግስት ሚድያዎች ፍሳሽ የለቀቁ፣ መንገድ ያበላሹ፣ እና ያልተፈቀደ ስራ የሰሩ በማለት ድርጅቶች ከአስር ሺዎች እስከ መቶ ሺህ ብሮች እንደተቀጡ መዘገባቸው ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዛሬ ባወጣው አንድ መግለጫ በዛሬው ቀን ብቻ ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን 4.2 ሚልዮን ብር እንደቀጣ አስታውቋል።
ባለስልጣኑ እንዳለው በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ 1.3 ሚልዮን ብር፣ በአቃቂ ክ/ከተማ 800 ሺህ ብር፣ በየካ ክፍለ ከተማ 600 ሺህ ብር፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ 600 ሺህ ብር፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ 500 ሺህ ብር በዛሬው እለት ብቻ ከቅጣት ተሰብስቧል።
መረጃን ከመሠረት!
@MeseretMedia