🔖
ኢብኑ ጀሪር እና የረሐብተኛው ሼኽ ገጠመኝ✔️
✍ የታሪኩ ዘጋቢ ታላቁ ሙፈሲር ኢብኑ ጀሪር አልጠበሪ ናቸው። ጊዜው 240 ዓመተ ሂጅራ ቦታውም መካ ነው። ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል ከኹራሳን የሆነ ሰው:-
👉"ሁጃጆች ሆይ! አንድ ሺ ዲናር ጠፍቶኛልና ያገኘ ሰው ካለ ለአላህ ሲል ይመልስልኝ ምንዳውን ከአላህ ያገኛል" ሲል ይጮሀል።
👌ይህን የሰማ አንድ አዛውንት:- " አንተ ኹራሳኒይ ሆይ ጊዜው ቸነፈር የበዛበት ነው። የአካባቢው ነዋሪም ደሀ ነው። ምን አልባት ገንዘብህ ሀላልን እንጂ ሀራምን የማይሻ ሰው አጅ አርፎ ሊመልስልህ ቢመጣ ወሮታውን በምን ትከፍለዋለህ?! " በማለት ጠየቀው።
👉ኹራሳኒዩም:- " ምን ያህል ይጠይቀኛል?" ሲል መልሶ ጠየቀ።
አዛውንቱም:- "አንድ መቶ ዲናር!" አለ።
✍ኹራሳኒዩም:- " አልሰጠውም። ነገ አላህ ፊት እፋረደዋለሁኝ። ሀቄን አሳልፌ አልሰጥም" በማለት ቁርጥ ያለ መልስ ሰጠ። በዚህ መልኩ ተለያዩ።
✔️ዲናሩ አዛውንቱ ጋር እንደሆነ በመጠርጠር ሲከታተሉት ነገሩ እንደጠረጠሩት ሆኖ አገኙት።
☑️አዛውንቱም አቡ ጊያስ ይባላል። በጣም ደሀ እና ብዙ የቤተሰብ አባላትን የሚያስተዳድር ሰው ነው። ቤቱ በመግባት ለሚስቱ "ባለ ዲናሩ ተገኝቷል ልመልሰው ነው" ይላታል።
👌 "አቡጊያስ ሆይ! ለሀምሳ ዓመታት በችግር ኖረናል። 4 ሴት ልጆች፣ 2 እህቶች፣ እናትህ እና እኔ እንዲሁም አንተ ዘጠነኛ ሆነህ ችግር እየተፈራረቀብን ነው። እባክህን አትመልሰው። አብላን፣ አጠጣን በደንብ አድርገህ አልብሰን። ሀብታም ስትሆን ብድሩን ትመልሳለህ" በማለት ትማጸነዋለች።
👌አቡ ጊያስም:- "የሰማንያ አራት ዓመት ሽማግሌ ከሆንኩ በኋላ ሀራም በልቼ አካሌን ለጀሀነም እሳት ማጋለጥ አልፈልግም" በማለት ይመልስላታል።
👉በንጋታው እንደተለመደው ኹራሳኒው:-
"ሁጃጆች ሆይ! አንድ ሺ ዲናር ጠፍቶኛልና ያገኘ ሰው ካለ ለአላህ ሲል ይመልስልኝ ምንዳውን ከአላህ ያገኛል" ሲል ይጮሀል።
👌 አዛውንቱ አቡ ጊያስም እንደትላንቱ
"ነግሬህ ነበር እኮ ጊዜው ቸነፈር የበዛበት ነው። የአካባቢው ነዋሪም ደሀ ነው። ምን አልባት ገንዘብህ ሀላልን እንጂ ሀራምን የማይሻ ሰው አጅ አርፎ ሊመልስልህ ሲመጣ ወሮታውን መመለስ አለብህ" ይለዋል። ኹራሳንዩ ከአቋሙ ንቅንቅ ሊል አልቻለም።
👉በሶስተኛውም ቀን ኹራሳኒዩ እንደተለመደው ሲጮኽ አዛውቱ እና ደሀው አቡ ጊያስ ጎተት አደረገውና:- "ተከተለኝ ገንዘብህን መልሼልህ በሰላም መተኛት እፈልጋለሁኝ" በማለት ዲናሩን ሊመልስለት ወደ ቤቱ ይዞት ይሄዳል።
✍የታሪኩ ዘጋቢ ኢብኑ ጀሪር አልጠበሪ ከኋላ ይከተሏቸዋል።
ቤቱ አንደደረሱ "ለኔም አላህ አለልኝ ለእስካሁኑም ይቅር በለኝ" በማለት ዲናሩን ይመልስለታል።
👌ኹራሳኒዩም ዲናሩን እየተቀበለ:- "አባቴ ሲሞት አደራህን ምንም ሳይሸራረፍ ሙሉውን መካ ካሉ ነዋሪዎች የመጨረሻ ደሀ ለሚባል ሰው ስጥልኝ ብሎ አደራ ጥሎብኝ ነበረና እነሆ መካ ላይ ካንተ የባሰ ደሀ አላየሁምና አንድ ሺ ዲናሩን ውሰድ" በማለት ያቀብለዋል።
👉 ክስተቱን በቅርብ ርቀት ይከታተሉ የነበሩት ዘጋቢያችን ኢብኑ ጀሪር አጥጠበሪም "ደሀው አዛውን ፊት ላይ የሚነበበውን ደስታ ሳይ እኔም ደስታዬ ወደር አልነበረውም" ይሉናል።
✔️ኢብኑ ጀሪር ከቦታው ለመሄድ ሲነሱ አዛውንቱ አቡ ጊያስ ተከትሎ ያስቆማቸውና "እዚህ የምታየን እኔና ቤተሰቦቼ ለበርካታ ዓመታት ሶላት እንሰግድ የነበረው ሰውነቴ ላይ የምታየውን ብቱቱ ጨርቅ ተራ በተራ እየተቀያየርን ነበር። ነገር ግን አንድም ቀን ሀራም በልተን አናውቅም። ይሀው አላህ ዛሬ ካሰን።
👌አንተም የደስታችን ተካፋይ መሆን አለብህ" በማለት አንድ መቶ ዲናር ጀቧቸው።
☑️ኢብኑ ጀሪርም "ይህ አንድ መቶ ዲናር ለሁለት ዓመታት ዒልም በመፈለግ ሂደት ላይ በቂ ወጪ ሆኖኛል።
👉ከአስራ ስድስት ዓመታት በኋላ ወደ መካ ስመለስ አዛውንቱን አፈላለግኩኝ። አዛውንቱም ሆነ ቤተሰቦቹ በሙሉ ሞተው ሁለት ሴት ልጆቹ ብቻ እንደቀሩ ሰማሁኝ።
👌ነገር ግን ሁለቱም ታላላቅ ሰዎች አግብተዋቸው መልካም ኑሮ እየኖሩ አገኘኋቸው" ይላሉ።
🔖ምንጭ: ታሪኽ በግዳድ 4/323 እንዲሁም
አልሙንተዘም 11/289/ ላይ ተዘግቧል
🔗
https://t.me/mesjidalsunnah/17170