+ ልጅሽ ደጅ ላይ ቆሟል +
ከመስከረም 26-እስከ ሕዳር 6 ባሉ አንድ ቅዳሜ ማታ ከ3 ሰዓት በኋላ ማሕሌተ ጽጌን ለመቆም ወደየካ ደብረ ሳሕል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እየሄድኩ ነው . . . መንገዱ ጭር ብሏል፤ አንድ ሱቅ ላይ ግን ደምበኛ (ገዢ) ቆሟል፤ እኔ መንገዴን እየቀጠልኩ ነው፡፡ ደንበኛው ቀጥ ብሎ ወደኔ መጣ እና ‹‹አባ ይበርኩኝ?›› አለኝ። ‹‹ካህን አይደለሁም›› አልኩት፣ በለበስኩት ነጠላ ጋቢና በእጄ የያዝኩት የጸሎት መጽሐፍ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደምሄድ አውቆ ነው፡፡ ‹‹አውቃለሁ›› አለኝ እና ‹‹ወደየትኛው ቤተ ክርስቲያን ነው የምትሄደው?›› ጠየቀ መለስኩለት፤ ‹‹እባክህን ልሸኝህ?›› አለኝ አዲስ ቪ 8 መኪና እያሳየኝ፣ ‹‹ብዙም ሩቅ ስላልሆነ በእግሬ ነው የምሄደው›› አልኩት . . .
ግለሰቡ የጠጣ ይመስላል፣ በእርግጥም የመጠጥ ሽታ ሸትቶኛል፤ በእጁ ፓኬት ሲጋራ ይዟል፣ ከሱቁ ሲመጣ ከፓኬቱ ውስጥ አንዱን አውጥቶ ከንፈሩ ላይ አድርጎ ነበር ሲቀርበኝ በጣቶቹ መሃል ያዘው፣ ምልከታዬን አስተውሎ ነው መሰለኝ የያዘውን ሲጋራ በሙሉ ጣለና በእግሩ ረጋገጠው፡፡ ‹‹አክሊለ ጽጌ ማርያም ቀጸላ መንግሥቱ ለጊዮርጊስ ልትል ነው አይደል?›› አለኝ
ከዚህ ንግግር በኋላ ስካሩ ሙሉ ለሙሉ ሲጠፋ በግልጽ ይታያል፡፡ ሁሉንም የመኪናውን በሮች ከፈተና ‹‹እንዲናፈስ ፈልጌ ነው . . . በሲጋራና በመጠጥ ሽታ የታጠነ መኪና ውስጥ እንዳትገባ›› አለኝ፤ በግርምት ቆምሁ፤
‹‹እባክህ አሁን እንሂድ?›› የጋቢናውን በር ብቻ ትቶ ሌሎቹን ዘጋጋና መኪናውን ለመንዳት ተዘጋጀ፤ በእምነት ገባሁና ተቀመጥኩ። መንገድ ስንጀምር በጣም ባዘነ ድምጸት
‹‹ሽሮ ሜዳ ነው ያደግሁት . . . ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን . . . ጽጌን በፍቅር ቆሜ ነው ያደግኩት . . . ለረጅም ዓመታት . . . አክሊለ ጽጌ ብዬ . . . ክበበ ጌራ ወርቅ ብዬ ›› ዓይኖቼን ከመንገዱ ነቅዬ ወደርሱ ሳዞር መንታ መንታ ሆነው የሚወርዱ እንባዎቹን ይጠርጋል፤ ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም መስማት ብቻ
‹‹ዲግሪዬን ከያዝኩ በኋላ አንድ ዓለም አቀፍ ኤን ጂ ኦ ገባሁ . . . በከፍተኛ ደመወዝ በቃ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተለያየሁ. . . አልሳለም፣ ኪዳን አላደርስ፣ አላስቀድስ፣ አላድር፣ አላነግስ ከሀገር ሀገር መዞር ከጓደኞቼ ጋር መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ . . . ይኸውልህ ሚስትና ልጆች እያሉኝ ነው እዚህ ያገኘኸኝ፣ የመጠጥና የሲጋራ ጓደኞቼ በልጠውብኝ ነው ያገኘሁህ. . . ውስኪአቸውን ይዘው እየጠበቁኝ ነው ›› ያለቅሳል፣ እንባዎቹን ይጠርጋል፤ ግን በሥርዓት ረጋ ብሎ ይነዳል፤ መናገሩን ይቀጥላል
‹‹ተረጋግቼ ማሰብ አልፈልግም . . . ምክንያቱም ከተረጋጋሁ ልጅነቴን ማሰብ እጀምራለሁ . . . ልጅነቴን ማሰብ ከጀመርሁ ቤተ ክርስቲያንን ማሰብ እጀምራለሁ . . . ደጀ ሰላሟን ማሰብ እጀምራለሁ. . . መቅደሷን ማሰብ እጀምራለሁ፣ . . . የዕጣኑን ሽታ ማሰብ እጀምራለሁ . . . ማልቀስ እጀምራለሁ . . . ፍቅሯን አስባለሁ . . . የጸናጽሉ፣ የከበሮው ድምጽ ይሰማኛል፣ በመሃል ሰይጣኔ ይመጣና እውነቴን ነው ስጠራው ነዋ የሚመጣው. . . ለጓደኞችህ ደውል ይለኛል . . . በመጠጥ ራስህን ደብቅ ይለኛል እታዘዘዋለሁ ልጆቼንና ሚስቴን ጥዬ እወጣለሁ››
አሁን ወደ ቤተክርስቲያን ታጥፈናል፤ ወደ ግቢው የሚያስገባ በር ጋር ስንደርስ ቆመ፣ ወደውስጥ ለመግባት በሮቹ የተከፈቱ ቢሆንም አልገባም፤
‹‹ወደውስጥ ገብተህ ትንሽ ቆይተህ አትሄድም?›› አልኩ ሀዘኑ ተጋብቶብኝ ‹‹አልገባም ግን ድሮ የሚወድሽ ልጅሽ ደጅ ቆሟል በላት›› አለና ሳግ ተናንቆት መሪውን ተደግፎ ድምጽ አሰምቶ አለቀሰ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ለምን እንዳለቀሰ፣ እንዴት እንዳለቀሰ በዓይኔ ያየሁ መሰለኝ፤
‹‹እባክህን ግባና አልቅስ›› አልኩ፣ የቻለውን ያህል አልቅሶ እንዲወጣለት ፈለግሁ፣
‹‹ማን . . . እኔ? አልገባም ግን ንገርልኝ አሁንም ይወድሻል በልልኝ . . . እዚህ በር ላይ ቆሟል በልልኝ›› አለኝ፣ እያለቀሰ ወረድሁ
ቅዱስ ዳዊት ‹‹በኃጥአን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ›› መዝ 84፣10 ያለው ለምን እንደሆነ ይበልጥ ገባኝ። ሳላውቀው የእኔም እንባ መንገዱን ጀምሯል፤ ‹‹ማን ስለሆንኩ ነው እንዲህ በፍቅርህ የተሸከምከኝ››አልኩ አምላኬን፣
በላዔ ሰብዕ ትዝ አለኝ በልጅነቱ የሚያስታውሳትን የድንግልን ድንቅ ስሟን ሲሰማ ከክህደት እንደተመለሰና ለመዳን ምክንያት እንደሆነችው፡፡ እናም ‹‹በልጅነቱ ይወድሽ የነበረውን ልጅሽን አስቢው ከልጅሽ ዘንድ አሳስቢለት›› አልኳት
ዲ/ን አብርሃም ይኄይስ
የቴሌግራምና ዩቱብ ቻናሌ ቤተሰብ መሆን የምትሹ
ዩቱብ
https://www.youtube.com/@1tewahdo
ቴሌግራም
https://t.me/tsidq