አንዳንዶች ፤ " አሁን ባለው ስርዓት በከፍተኛ ጫና ውስጥ ወድቀው ነው እየሰሩ ያሉት ፤ በተለያዩ ጉዳዮች አለመግባባት ውስጥም እንደነበሩ ብዙ ጊዜ በሚዲያ ይሰማ ነበር ፤ ለመናገር እንኳን እድል የላቸውም ፤ ባገኙት አጋጣሚ ግን በገደምዳሜው ስሜታቸውን ስለ ሀገራቸው ይናገሩ ነበር ፤ አሁንም ቦታውን ሲለቁ ስለዚህ ስርዓት ብዙ የሚናገሩት ይኖር ይሆናል " የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
አንዳንዶች፤ " በዚህ ልክ ትልቅ የስልጣን እርከን ይዘው ህዝብን ግራ የሚያጋባ ድፍንፍን ያለ ፅሁፍ በገጻቸው መጋራቱ ሳያንስ እውነትም እሳቸው መሆናቸውን በግልጽ አለማብራራታቸው ትክክል አይደለም ፤ ችግር ካለም እውነታውን ለህዝብ ማሳወቅ አለባቸው እንዲህ የዘፈን ግጥም ከሚያስቀምጡ " ብለዋል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ " የ6 ዓመት የስልጣን ዘመናቸው ሲያበቃ ይህን አይነት ነገር በገጻቸው መፃፋቸው የህዝብ ተቀባይነት ለማግኘት ነው እስከዛሬ በሀገሪቱ ብዙ ነገር ብዙ ግፍ ሲፈጠር ባላየ ሲያልፉ ነበር ፤ አንዳንዱን ደግሞ እየመረጡ ሲናገሩ ነበር ፤ ለምን አሁን ? በዚህ ስልጣን እንደማይቀጥሉ ስለሚያውቁ ነው ፤ ስልጣንም መልቀቅ ከነበረባቸው ቀድሞ ተናግሮ እንጂ አሁን ላይ ይህን አጀንዳ ለህዝብ መስጠት ትክክል አይደለም ፤ ጊዜያቸው አብቅቷል ይሰናበታሉ ፤ እሱንም ስለሚያውቁ ነው " ሲሉ ፅፈዋል።
በኢትዮጵያ የፕሬዜዳንት ስልጣን ዘመን 6 ዓመት ሲሆን ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ወደ ስልጣን የመጡት ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ/ም ላይ ነበር።
ሌሎች ደግሞ " እንዲያው በደፈናው ድምዳሜ ላይ ከመድረስ የእሳቸውን ሙሉ ሀሳብ በትዕግስት ጠብቆ መስማት ይገባል " ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ ግን ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬዝዳንትነት የስልጣን ድርሻው ምንድነው ? ፕሬዝዳንት የሚኮነው እንዴት ነው ? ምን ምን ይሰራል በዝርዝር ? ሲሉ የጠየቁ አሉ።
ለዚህ ምላሽ ይሆን ዘንድ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ህገ መንግስቱ ስለ ፕሬዜዳንቱ የሚለውን ከዚህ በታች አቅርቧል።
የኢፌዲሪ ህገ መንግስት ስለ ሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ስልጣንና ተግባር ምን ይላል ?(የኢፌዴሪ ህገ መንግስት)
ምዕራፍ ሰባት
ስለ ሪፐብሊኩ ኘሬዚዳንት
አንቀጽ 69
ስለ ኘሬዚዳንቱ
ኘሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ርዕሰ ብሔር ነው፡፡
አንቀጽ 70
የፕሬዜዳንቱ አሰያየም
1. ለፕሬዜዳንትነት ዕጩ የማቅረብ ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።
2. የቀረበው ዕጩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ከተደገፈ ፕሬዜዳንት ይሆናል።
3. የምክር ቤት አባል ፕሬዜዳንት ሆኖ ከተመረጠ የተወከለበትን ምክር ቤት ወንበር ይለቃል።
4. የፕሬዜዳንቱ የሥራ ዘመን 6 ዓመት ነው። አንድ ሰው ከሁለት ጊዜ በላይ ለፕሬዜዳንትነት ሊመረጥ አይችልም።
አንቀጽ 71
የኘሬዚዳንቱ ሥልጣንና ተግባር
1. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑን ምክር ቤት ዓመታዊ የጋራ ስብሰበባ ይከፍታል፡፡
2. በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቃቸው ሕጐችና ዓለምአቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ ያውጀል፡፡
3. ሀገሪቷን በውጭ ሀገሮች የሚወክሉትን አምባሳደሮችና ሌሎች መልክተኞች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ይሾማል፡፡
4. የውጭ ሀገር አምሳደሮችንና የልዩ መልዕክተኞችን የሹመት ደብዳቤ ይቀበላል፡፡
5. በሕግ መሰረት ኒሻኖች እና ሽልማቶችን ይሰጣል፡፡
6. በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕግ በተወሰነው መሰረት ከፍተኛ የውትድርና ማዕረጐችን ይሰጣል፡፡
7. በሕግ መሰረት ይቅርታ ያደርጋል፡፡
-TikvahEthiopia
@variety_ethiopia