በአረፈበትም ጊዜ ጌታችን ወደርሱ መጥቶ እጆቹን በላዩ ጫነ ለሥጋውም መፍረስና መበስበስ እንዳያገኘው ኃይልን ሰጠው በአባቱ በያዕቆብም መቃበር አኖሩት።
#ቅድስት_ሰሎሜ፦ አምላክን የወለደች የቅድስት ድንግል የእመቤታችን የአክስቷ ልጅ መታሰቢያዋ ነው። እርሷም የማጣት ልጅ የሌዊ ልጅ የሚልኪ ልጅ የካህን አሮን ልጅ ናት። ለማጣት ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱ ስም ማርያም ነው የሁለተኛዪቱ ስም ሶፍያ የሦስተኛዪቱም ሐና ነው ይቺም ማርያም ሰሎሜን ወለደቻት ሶፍያም ኤልሳቤጥን ወለደቻት ሐናም አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደቻት።
እመቤታችንም ድንግል ስትሆን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በወለደችው ጊዜ ይቺ ቅድስት ሰሎሜ የእመቤታችንን አወላለድ እንደ ሴቶች ሁሉ አወላለድ መስሏት ተጠራጠረች ከዚህም በኋላ የድንግል እመቤታችን ገላዋን ዳሠሠቻት ያን ጊዜ እጇ ተቃጠለ ሕፃኑን በዳሠሠችው ጊዜ ደግሞ ዳነች።
በዚህም በኅቱም ድንግልና አምላክን እንደወለደች አወቀች። ከተረገመ ኄሮድስ ፊት እመቤታችን በሸሸች ጊዜ ከዮሴፍ ጋራ በመሆን አብራ በመሰደድ የእመቤታችንን ድካሟን ተካፍላ አገለገለቻት ከስደት እስከ ተመለሱ ድረስ ሕፃኑን ታዝለዋለች የምታጥብበትም ጊዜ አለ።
መድኃኒታችን ሰው በሆነበት ወራት ሁሉ አልተለየችም በመከራውም ቀን ከእመቤታችን ጋራ ከከበሩ ሁሉ ሴቶች በትምህርቱ ወራት ከተከተሉት ጋራ እያለቀሰች ነበረች።
በተነሣባት ዕለት ወደ መቃብር ገሥግሣ ከሐዋርያት ቀድማ ያየች ናት። በኃምሳኛውም ቀን መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከባልንጆሮቿ የከበሩ ሴቶች ጋራ ሰማያዊ ሀብትን ተቀብላ በክብር ባለቤት መድኃኒታችን ስም ሰበከች ብዙዎችንም አሳመነች። ከአይሁድም ብዙ ስድብና ሽሙጥ አገኛት ከዚያም አረፈች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#አባ_ጽጌ_ድንግል_ዘወለቃ
ጻድቁ አቡነ ጽጌ ድንግል በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበሩ ሊቅና ገዳማዊ ናቸው። የዘር ሐረጋቸው ምንም ከቤተ እሥራኤል እንደሚመዘዝ ቢታወቅም ኢትዮዽያዊ ናቸው። አስቀድመው አይሁዳዊ በመሆናቸው ኢየሱስ ክርስቶስንና ድንግል እናቱን አያምኑም ነበር።
የተማሩትም ብሉይ ኪዳንን ብቻ ነበር። በጊዜውም "ክርስቶስ አልተወለደም ትክክለኛው እምነት ይሁዲ ነው" እያሉ ከክርስቲያኖች ጋር ይከራከሩ ነበሩ። አንድ ቀን ግን ከታላቁ ሊቅና ገዳማዊ አቡነ ዜና ማርቆስ ጋር ተገናኙ።
ጻድቁን ስላልቻሏቸው ተሸንፈው በክርስቶስ አመኑ። አቡነ ዜና ማርቆስም አስተምረው ክርስትና ሲያነሷቸው/ሲያጠምቁዋቸው 'ጽጌ ድንግል' አሏቸው። ሲመነኩሱም 'ጽጌ ብርሃን' ተብለዋል። ቀጥለውም በጾምና በጸሎት ሲጋደሉ እመቤታችንንም ሲለምኑ ምሥጢር ተገለጠላቸው።
የእመ ብርሃንን ስዕለ አድኅኖ በአበባ ተከባ: በብርሃንም ተውጣ ተመለከቱ። በዚህ ምክንያትም ዛሬ በጣፋጭነቱ የሚታወቀውን ማኅሌተ ጽጌን 150 ዓርኬ አድርግው ደረሱ። እስከ ዕለተ ዕረፍታቸውም እመቤታችንና ልጇን በገዳማቸው (ወለቃ አካባቢ የሚገኝ) ሲያመሰግኑ ኑረዋል። ጻድቁ ያረፉት ጥቅምት 27 ሲሆን ዛሬ የቃል ኪዳን በዓላቸው ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱስ_አባ_ፊልክስ
ዳግመኛም በዚህች ቀን የሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ፊልክስ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ክርስቲያኖች ናቸው የቤተክርስቲያንንም ትምህርት አስተማሩት የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት አንስጣስዮስም ዲቁና ሾመው ደግሞ የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ዮስጦስም ጠባዩን የጽድቁንና የትሩፋቱን ደግነት አይቶ ቅስና ሾመው።
ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዲዮናስዮስ በአረፈ ጊዜ ይህን አባት ፊልክስን መረጡት በእግዚአብሔርም ፈቃድ በሮሜ ሀገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት የክርስቶስንም መንጋዎች በመልካም አጠባበቅ ጠበቀ።
ትሩስ ቄሣርም ከሞተ በኋላ ቴዎድሮስ ቄሣር ነገሠ ። እርሱም በምእመናን ላይ ታላቅ መከራ አምጥቶ ጭንቅ በሆኑ ሥቃዮች አሠቃያቸው። ብዙዎችም በእርሱ እጅ በሰማዕትነት ሞቱ። ይህም አባት ከዚህ ከሀዲ ታላቅ መከራና ኀዘን ደረሰበት። ስለርሱም ወደ እግዚአብሔር ማለደ ክብር ይግባውና ጌታችንም ልመናውን ተቀብሎ ይህንን ከሀዲ በሁለተኛ ዘመነ መንግሥቱ አጠፋው።
ከዚህም በኋላ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠ ጊዜ ክርስቲያኖችን አብዝቶ ማሠቃየትን ጀመረ ይህም አባት ፊልክስ የክርስቲያኖችን ሥቃይ እንዳያይ ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር ጸለየ በዲዮቅልጥያኖስም በመጀመሪያው ዘመነ መንግሥቱ አረፈ።
ይህም አባት ብዙዎች ድርሳናትንና ተግሣጾችን ደርሶአል ከእርሳቸውም ስለ ውግዘትና ስለ ቀናች ሃይማኖት የተመላለሱበት አለ እሊህም ለክርስቲያን ወገን እጅግ የሚጠቅሙ በጎዎች ናቸው።
✞ ኅዳር 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም (ሚጠታ ለማርያም)
2.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
3.ቅድስት ሰሎሜ ቡርክት
4.ቅዱስ ዮሳ (ወልደ ዮሴፍ)
5.ቅዱስ ቴዎፍሎስ ሊቅ
6.አባ ጽጌ ድንግል ዘወለቃ
7.አባ ፊልክስ ዘሮሜ
✞ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከስደቱ በረከትም ያድለን። በቅዱሳኑም ጸሎቱ ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ኅዳር_ግንቦትና_ሐምሌ፣ #ከዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ እና #ከገድላት_አንደበት)