፩
የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን በእንተ ልደቱ ለእግዚእነ
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ብፁዕ የሚሆን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ድንግል ከምትሆን ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ስለ መወለዱ የተናገረው ድርሳን ይህ ነው፡፡ ጸሎቱና በረከቱ በሁላችን ላይ ጸንቶ ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
ዛሬ በፍጥረት ሁሉ ዘንድ ስለሆነው ስለዚህ ምሥጢር ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? ዛሬ ሰማያዊው አምላክ በሥልጣኑ ክብር ተገለጠ፡፡ እነሆ ዛሬ እረኞች ማወቅ የማይቻለውን ምሥጢር ሲናገሩ እሰማቸዋለሁ፡፡ የሰው ልጅ ጥበብ ሊረዳው አይችልምና፡፡
ዛሬ ይህቺ ምሥጢር የማትታወቅ ሕፀፅ ያለባት አይደለችም፤ በታላቅ ኃይል የተገለጠች ሰማያዊ ክብር ናት እንጂ፡፡ ዛሬ መላእክት ያመሰግናሉ፤ የመላእክት አለቆችም ይዘምራሉ፤ ኃይላትም እልል ይላሉ፤ ሥልጣናትም ያመሰግናሉ፤ ኪሩቤልም ይቀድሳሉ፤ ሱራፌልም ይባርካሉ፤ እረኞች የምሥራቹን ይናገራሉ፤ ሁሉም ያመልካሉ ይሰግዳሉም፡፡
ዛሬ መላእክት ስለምን በፍጥነት ይሮጣሉ? ሰማያዊውን አምላክ በምድር ላይ አይተዋልና፡፡ የሰው ልጅም ወደ ሰማያዊ ክብሩ ተመልሷልና፡፡ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ልዑሉ ዝቅ ዝቅ አለ፤ ወደ ምድርም ወረደ፤ ትሑቱም ከፍ ከፍ አለ፤ ወደ ሰማይም ዐረገ፡፡
ዛሬ ቤተ ልሔም ሰማይን መሰለች፡፡ ስለ ከዋክብት ፈንታ መላእክት እያመሰገኑ በውስጧ ታይተዋልና፤ ስለሚጠልቀው ፀሐይ ፈንታም ብርሃኑ የማይጠፋ የእውነት ፀሐይ ከእርሷ ወጥቷልና። ለፍጥረት ሁሉ የሚያበራ የእውነት ፀሐይን ስለ ወሰነችው፡፡ ስለ ቅድስት ድንግል እንናገር ዘንድ ቃል ይደክማል፤ ንግግርም መግለጥ ይሳነዋል፡፡ የሆነውን አልተረዳሁም፤ የተፈጠሩትንም አላወቅሁም። ነገር ግን አምላክ በፈቀደ ጊዜ ሰው ሆነ፡፡ ሰው ሁኖም የእጁን ሥራዎች አዳነን፡፡
ዛሬ ሁሉ ወደ እርሱ ፍቅር ፈጥኖ ይመጣል፡፡ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ የነበረ ሰማያዊ አምላክ ያለ መለወጥ ሰው ሆነ፡፡ ቀዳማዊ ቃል ያለ መለወጥና ያለመለየት ሥጋን ተዋሐደ፡፡ ዛሬ ከፍጥረት ሁሉ ሥውር የሆነ ድንቅ ምሥጢርን ዐየሁ፡፡
ዛሬ መላእክት በፍጹም ደስታ አመሰገኑ፡፡ እንዲህ እያሉ “እንዴት ሰማያዊ ንጉሥ ወደ ምድር ወረደ?” ከእርሱ ጋራም መላእክትን፣ ኃይላትን፣ መናብርትን፣ሥልጣናትን አላስከተለም፤ ይዞ አልወረደም፡፡ ማንም ሊሄድባት በማይችል ድንቅ መንገድ መጣ እንጂ፡፡ ከቅድስት ድንግል ማርያምም በሥጋ ተወለደ፡፡
በተገለጠም ጊዜ መላእክት ሰው መሆኑን አላወቁም፡፡ ሰው ከሆነም በኋላ ከመለኮቱ ክብር አልተለወጠም፡፡ የምድር ነገሥታት የኃይላት ጌታ ለሆነው ሰማያዊ ንጉሥ ሊሰግዱለት መጡ እንጂ፡፡ ሴቶች ኀዘናቸውን ወደ ፍጹም ደስታ ይለውጥ ዘንድ ከድንግል ወደተወለደው መጡ፡፡ ዛሬ ሴቶች ድንቅ ምሥጢርን ያዩ ዘንድ ወደ ተወለደው ሕፃን መጡ። ቀዳማዊ አዳምን ያድነው ከኃጢአት ቍስልም ይፈውሰው ዘንድ አምላክ ዛሬ በሥጋ ተገለጠ፡፡
ይቀጥላል......
(ድርሳነ ሠለስቱ ሊቃውንት በመምህር ቃለጽድቅ ሕግነህ የተተረጎመ ገጽ 33-53)
@mekra_abaw