Meseret Media


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: Новости и СМИ


መሠረት ሚድያ በኢትዮጵያ ለበርካታ አመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የሰሩ ባለሙያዎች ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝብ ለማድረስ በማለም ያቋቋሙት ዲጂታል ሚድያ ነው።

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
Новости и СМИ
Статистика
Фильтр публикаций


የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአርማውን ቀለም የመቀየር ፍላጎትና እቅድ እንደሌለው ለመሠረት ሚድያ አሳወቀ

- የድርጅቱ አዲስ አጥር ላይ በአረንጓዴ ቀለም ብቻ የሰፈረው አርማ መልሶ ሊቀባ መሆኑ ታውቋል

(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ በርካታ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ በቪ አይ ፒ መግቢያ አካባቢ ባሰራው አጥር ላይ የሚታወቅበት አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለም ቀርቶ በአረንጓዴ ቀለም ብቻ አርማው (ሎጎው) ተቀብቶ በመመልከታቸው የተለያየ አስተያየት ሲሰነዝሩ ተስተውሏል።

አንዳንዶች አየር መንገዱ ቀስ በቀስ የአርማውን ቀለም እየቀየረ እንደሆነ የገመቱ ሲሆን ድርጊቱን በተለያየ መልኩ ሲገልፁት ታይቷል።

መሠረት ሚድያ በዚህ ዙርያ አየር መንገዱን ያነጋገረ ሲሆን ተቋሙ አርማውን የመቀየር ፍላጎትና እቅድ እንደሌለው አሳውቋል።

"ይሄ የእኛ እቅድም፣ ፍላጎትም አይደለም" ያሉን አንድ የአየር መንገዱ ሀላፊ አዲሱ አጥር በአረንጓዴ ብቻ የተቀባው ገፅታውን 'ቀለል ያለ' እንዲሆን ለማድረግ ነው ብለዋል።

"በዚህ ዙርያ ተወያይተንበታል፣ ብዙ ግርታም እንደፈጠረ አስተውለናል። ወደቀደመው እና ወደ ኦፊሴላዊው የአርማ ቀለሞች መልሶ በቅርቡ ይቀባል" በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

አንድ ሌላ የዘርፉ ባለሙያ በሰጠን አስተያየትም አንዳንድ ግዜ ባለ ቀለም ሎጎዎች ቀለል ያለ መልክ እንዲኖራቸው ሲፈለግ ቅርፃቸውን ጠብቀው ቀለማቸው ሊቀየር እንደሚችል ጠቁሟል።

"ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታላቁ ሩጫ ቲሸርቶች ላይ ያለውን ሎጎ ብናይ ወይ ነጭ ወይ ሌላ ቀለም ነው፣ አላማው ዲዛይኑ የማይረብሽ እና ቀለል ያለ እንዲሆን ነው። ይህ አሰራር እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት በጣም የተለመደ አሰራር ነው" በማለት ሙያዊ አስተያየቱን ሰጥቷል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

8.8k 0 12 13 161

"ጠበቃዎችን እያነጋገርኩ ነው፣ በአቪዬሽን ህግ ሊከለክሉኝ እንደማይችሉ ተነግሮኛል"- አቶ ልደቱ አያሌው ለመሠረት ሚድያ

(መሠረት ሚድያ)- ዛሬ ጠዋት ከአሜሪካ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ለመጓዝ በአትላንታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቢገኙም እንዳይሳፈሩ የተደረጉት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ጉዳዩን በህግ ሊይዙት እንደሚችሉ ተናገሩ።

"አየር ማረፊያው ስገኝ ሰራተኞቹ የ boarding pass ማውጣት እምቢ አላቸው፣ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ያሉኝ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲን አነጋግሬ የተለየ ፈቃድ ካልተሰጠኝ በስተቀር ወደ ኢትዮጵያ መጓዝ እንደማልችል ነው" ብለው ለመሠረት ሚድያ የተናገሩት አቶ ልደቱ ዋሽንግተን ወደሚገኘው ኤምባሲ ስልክ ቢደውሉም ጥሪ የሚያነሳ ማሽን እንጂ የኤምባሲው ሰራተኖችን ማነጋገር እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል።

"ወደ ሀገሬ መሄድ ማንም ሊከለክለኝ አይችልም፣ ሀገሬ ከሄድኩ በኋላ ግን ማሰር ይችላሉ። በአሸባሪነት ወንጀል ሊከሰኝ እንደሚፈልግና በቁጥጥር ስር እንድውል ከኢንተር-ፖል ጋር ጭምር እየተነጋገረ እንደሆነ ሲገልፅ የነበረው የኢትዮዽያ መንግስት ዛሬ በራሴ ፈቃድ ወደ አገሬ ለመመለስ ስሞክር በእኔ ላይ ህገ-ወጥ ክልከላ ማድረጉ አስገርሞኛል" ያሉት ፖለቲከኛው ከአመታት በፊት ለህክምና ከሀገር ሲወጡ ከልክሏቸው እንደነበር፣ አሁን ደግሞ ሊመለሱ ሲፈልጉ መከልከሉ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ጨምረው ተናግረዋል።

"መሄድ አለብኝ፣ በመብቴ ጉዳይ አልደራደርም። ጠበቆችም እያነጋገሩኝ ነው፣ በአቪዬሽን ህግ ሊከለክሉኝ እንደማይችሉ ተነግሮኛል" በማለት ወደ ሀገር ቤት በመመለስ በሀገራቸው የፖለቲካ ምህዳር ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው ለሚድያችን ተናገረዋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia


በዱባይ በተደረገው የፖሊስ SWAT ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ 101ኛ መውጣቱ ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- ላለፉት ጥቂት ቀናት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ዱባይ ከተማ በተካሄደው እና የ103 ሀገራት የSWAT ፖሊስ ቡድን አባላት በተሳተፉበት ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ 101ኛ መውጣቱ ታውቋል።

ይህ Special Weapons And Tactics (የልዩ መሳርያዎች እና ታክቲኮች) የቡድን ውድድር ላይ የቻይና B ቡድን በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፣ የካዛክስታኑ ሱንካር ፖሊስ ሁለተኛ እንዲሁም የቻይና C ቡድን ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል (ሊንክ: https://uaeswatchallenge.com/?page_id=11727)

በ SWAT ውድድሩ ላይ ሲወዳደር የቆየው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ቡድን ከሁለት ቀን በፊት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ስትራቴጂክ አመራሮች አቀባበል ተደርጎለታል።

በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፤ እንደ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የፖሊስ ተቋም በተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች SWAT ውድድር ላይ መሳተፉ ለሀገራችን ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ጠቀሜታ ከማስገኘቱም ባሻገር ዓለም አቀፍ የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነትን ለማዳበር ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የፖሊስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ መቻላችን ልምድና ተሞክሮ እንድናገኝ ያስቻለን ነው ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም እ.ኤ.አ 2026 በሚካሄደው ውድድር ላይ አስፈላጊውን ስልጠና በመውሰድ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትጋት እንሠራለን ሲሉም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወደ ስፍራው ሲጓዝ እና ውድድሩን አጠናቆ ወደ ሀገር ሲመለስ በስፋት በመንግስት ሚድያዎች ቢበገብም ያስመዘገበው አነስተኛ ውጤት ግን ለህዝብ አልተገለፀም።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

21.2k 0 109 84 949



በኢቢሲ ውስጥ ያለውን የአንዳንድ ሰራተኞች የፎርጅድ ዶክመንት ያጋለጠው ሰራተኛ የሽብር ክስ ቀረበበት

(መሠረት ሚድያ)- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) አንዳንድ ሰራተኞች ፎርጅድ ወይም እውቅና የሌለው የትምህርት ማስረጃ እንዳላቸው ያጋለጠው የተቋሙ ሰራተኛ ሌላ የሽብር ክስ ቀርቦበት ለእስር ተዳርጎ እንደነበር ታወቀ።

አቶ ወገን አበበ የተባለው የቀድሞው የተቋሙ ሰራተኛ ክሱ ቀርቦበት 52 ቀን ታስሮ ጥር 26/2017 ዓ/ም መለቀቁን ለመሠረት ሚድያ ተናግሯል።

"የተያዝኩት ተወልጄ ባደግኩባት ዲላ ከተማ ነው፣ ከላይ በመጣ ትእዛዝ ተብሎ ቤቴ ተበረበረ። ዲላ 5 ቀን ከታሰርኩ በኋላ ወደ ወላይታ ሶደ ተወሰድኩ፣ 3 ቀን ታስሬ ወደ ሀዋሳ የፌደራል ምርመራ ተወሰድኩ፣ ከዛም አንድ ሳምንት ሀዋሳ ታስሬ ወደ አዲስ አበባ ፌደራል ምርመራ ሜክሲኮ ተወሰድኩ" በማለት ያለፈበትን የእስር ሂደት አስረድቷል።

መሠረት ሚድያ የተመለከተው የክስ ወረቀት እንደሚለው አቶ ወገን በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ቡድን አባሎች ጋር በመቀናጀት እና ቡድኑን በመምራት መጠርመሩን ይገልፃል።

ክሱ አክሎም "በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት ለማድረስ ተልእኮ በመቀበል እና ቡድኑን በገንዘብ በማገዝ" እንዲሁም "በመላው ሀገራችን ሰላም እንደሌለ በማስመሰል ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳሳና ለሽብር ተግባራት የሚቀሰቅሱ የሀሰት ቪድዮ እና የድምፅ መልዕክት በማዘጋጀት እና በማህበራዊ ሚድያ በማሰራጨት" የሚሉ ውንጀላዎችን አካቷል።

ይሁንና አቶ ወገን ከ52 ቀን እስር በኋላ በ40 ሺህ ብር ዋስ ተለቀዋል።

"እኔ አማራ ክልል ሄጄ እንኳን አላውቅም፣ ዘመድም የለኝም" የሚለው አቶ ወገን እንኳን ለተለያዩ ቡድኖች የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግ ኢቢሲ ከስራው ካባረረው በኋላ ስራ እንኩዋን እንደሌለው ገልጿል።

ግለሰቡ ከወራት በፊት የአንዳንድ የኢቢሲ ሰራተኞች የፎርጂድ ዶክመንትን በተመለከተ ካጋለጠ በኋላ ተቋሙ መረጃውን ያወጣብኝ የቀድሞ ሰራተኞዬ "ተአማኒነቴ እንዲቀንስ አድርጓል" በማለት 10 ሚልዮን ብር ካሳ ይክፈለኝ ብሎ ክስ መስርቶ ነበር።

ይሁንና ራሱ ኢቢሲ ከወራት በፊት በተቋሙ ሰራተኞች ላይ ባደረገው የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ ሂደት የ400 ሰራተኞቹ ሰነድ ፎርጂድ/ሀሰተኛ መሆኑን እንዳረጋገጠ አንድ ሾልኮ የወጣ ዶክመንት ጠቁሞ ነበር።

ይህ ሆኖ እያለ የተቋሙ ሀላፊዎች እርምጃ እንዳይወሰድ ይህን መረጃው እንደደበቁ፣ በጥቆማ አቅራቢዎች ላይም ዛቻ እና ማስፈራርያ እያደረሱ እንደኮነ በወቅቱ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ለጠቅላይ አቃቤ ህግ የፃፈው ደብዳቤ አሳውቆ ነበር።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

25.8k 0 46 13 552



#የህዝብድምፅ ከህዝብ በጥቆማ መልክ ደርሰውን ትክክኝነታቸው የተረጋገጡ 5 መረጃዎች

1. በቅርቡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የታሪፍ ማሻሻያ እንዲሁም የቫት (VAT) ክፍያ መጀመሩን ተከትሎ በተለይ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ አስደንጋጭ ክፍያ እየተጠየቁ እንደሆነ አንዳንድ ዜጎች እየተናገሩ ይገኛሉ። ደምበኞች እንደሚሉት ለምሳሌ በቅድመ ክፍያ ካርድ የሚጠቀም አንድ ሰው 1,000 ብር ቢሞላ ቆጣሪዉ ላይ የሚታየዉ የተሞላዉ የብር መጠን 353.3 ብር ነው። የድርጅቱን ሰራተኞች ለማጋነር ጥረት ሲደረግ የቫት ክፍያ ነዉ እንደሚሉ፣ ቫቱ እንዴት እና በምን ስኬል እንደሚሰላ ግን ማስረዳት እንደማይችሉ ታውቋል። በሀገራችን የቫት አዋጅ መሰረት የቫት ስኬሉ የአገልግሎቱ 15% መሆኑ ይታወቃል፡፡

2. በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ውሳኔ ምክንያት የኤችአይቪ ክትትል የሚያደርጉ ከ 500,000 በላይ ኢትዮጵያውያን አደጋ እንደተጋረጠባቸው ታውቋል። ውሳኔው ኤችአይቪን እንደማይመለከት ተገልፆ የነበረ ቢሆንም የጤና ሰራተኞች ግን መድሀኒት እና ቁሳቁስ ለማዘዋወር እንደተቸገሩ ተሰምቷል። ገና ከአሁኑ ለበሽታው የሚወሰደውን መድሀኒት በህገወጥ መልኩ ለመሸጥ ሙከራዎች እየታዩ እንደሆነ ታውቋል። የኢትዮጵያ የጤና እና የሰብአዊ እርዳታ ሴክተሮች ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ እርዳታ ባስተላለፉት ውሳኔ ክፉኛ መጎዳቱ እየታየ ነው።

3. የኢትዮጵያ ማሪታይም ትሬኒንግ ኢንስትትዩት ተማሪዎች ትምህርቱን ተከታትለው ከጨረሱ በኋላ 36,000 ዶላር እየጠየቀ እንደሆነ ታውቋል። መርከበኞችን አሰልጥኖ ማስቀጠር ከጀመረ ከአስር አመት በላይ የሆነው ተቋሙ በ Marine Engineering and Electrotechnical Officer አስተምሮ ወደ ስራ የሚያሰማራቸው ዜጎችን የሚጠየቀው የገንዘብ መጠን በጣም የተጋነነ እና ከሌሎች ሃገራት አንፃር ሲታይ በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ታውቋል። ለምሳሌ በተመሳሳይ ትምህርት የተማሩ ሰዎች በህንድ 5,000 ዶላር እንዲሁም በፊሊፒንስ 10,000 ዶላር ብቻ ይጠየቃሉ።

4. በሸገር ከተማ አስተዳደር ለመንግስት ቢሮ ማሰርያ ብር አምጡ እየተባሉ እንደሆነ ዜጎች ለመሠረት ሚድያ ጠቁመዋል። "በተጨማሪም ቤት ለቤት እየዞሩ የቴሌቪዥን ግብር ክፈሉ ይላሉ፣ የቴሌቪዥን ግብርን በተመለከተ EBC   ከመብራት አገልግሎት ጋር ደረስኩት ባለው ስምምነት ላለፋት 3 ዓመታት መብራት ስንሞላ የቴሌቪዥን እየተቆረጠብን ነው የኖርነው፣ አሁን ሸገር ከተማ ከነቅጣቱ ክፈሉኝ እያለ ነው" ብለው ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ። አክለውም የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ከውሀና ፍሳሽ ጋር በመሆን ከነዋሪዎች የቆሻሻ ቢሰበስብም የወረዳ አስተዳደሩ የራሱን ማህበር አደራጅቶ በየወሩ ከነዋሪው በድጋሜ እንደሚያስከፍል ታውቋል።

5. በመጨረሻም፣ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ቤታቸው ፈርሶባቸው ወደሌላ ቦታ የተዛወሩ ሰዎችን በፈረሰው ቤት ስም የቤት ግብር እንዲከፍሉ የቴክስት መልዕክት እየላከላቸው እንደሆነ ታውቋል። "ቤቴ ካዛንችስ ነበር፣ ቤቴም ሰፈሩም ከፈረሰ 3 ወራት አለፉ። ለፈረሰው ቤቴ ነው ግብር ክፈል የተባልኩት" ያሉት አንድ ግለሰብ "መሬት እና የቤት መስሪያ ወደፊት እንሰጣችኋለን ስላሉን የምንጠብቀው እሱን ነበር። በአሁን ሰአት ከነቤተሰቤ  ቱሉ ዲምቱ ኮንዶሚንየም ተከራይተን እየኖርን ነው። ዛሬ ታድያ ላፈረሱት ቤቴ ግብር ክፈል ይሉኛል!" በማለት ለሚድያችን ተናግረዋል።

መረጃን ከመሠረት!
 
 @MeseretMedia

27.8k 0 97 41 772



በኮሪደር ልማት የተሳተፉ ከ400 በላይ ኮንትራክተሮች መንግስት ክፍያ ሊፈፅምላቸው እንዳልቻለ ተናገሩ

(መሠረት ሚድያ)- በኮሪደር ልማት ምክንያት እንደ ካዛንችስ ካሉ ቦታዎች ለተነሱ ሰዎች በፍጥነት የተዘጋጁ የጋራ መኖርያ ቤቶችን ያዘጋጁ ከ400 በላይ ኮንትራክተሮች ክፍያቸውን መንግስት እንደያዘባቸው ገልፀው ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ ተናገሩ።

ኮንትራክተሮቹ ለመሠረት ሚድያ በሰጡት መረጃ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ኮንትራክተሮቹ በግዴታ ከ3 ሺህ በላይ ቤቶችን ለኮሪደር ተነሺዎች እንዲገነቡ ካደረገ በኋላ ክፍያ መፈፀም አልቻለም።

"በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጀን እኛ ኮንትራክተሮች ከ3 ሺህ በላይ የ40/60 የጋራ መኖርያዎች ውስጥ ያሉ ለንግድ ተብለው የተሰሩ ክፍሎችን ወደ መኖርያነት ቀይረን ገንብተን ብንጨርስም መንግስት ክፍያችንን ከልክሎናል" የሚሉት ኮንትራክተሮቹ አብዛኞቹ በብድር ወስደው ስራውን ቢሰሩም አሁን ትርፉ ቀርቶ ብድራቸውን ለመክፈል ተቸግረው እንዳሉ አብራርተዋል፣ አንዳንዶቹ ብድሩን ለመክፈል የግል ንብረታቸውን ለመሸጥ እየተገደዱ እንደሆነ ተናግረዋል። 

እነዚህ ለተነሺዎች በኮንትራክተሮቹ የተዘጋጁ  ቤቶች በአያት፣ አራብሳ፣ ቡልቡላ እና አስኮ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

"ቤቶች ልማት እና ፋይናንስ ቢሮዎችን ስንጠይቃቸው ምላሻቸው ገንዘብ የለንም ነው፣ ታድያ ገንዘብ ከሌላቸው ለምን እኛን አሰሩን?" የሚል ጥያቄ የሚያነሱት እነዚህ አነስተኛ እና ጥቃቅን ኮንትራክተሮች አንዳንዶቹ ቤተሰባቸው ጭምር ችግር ላይ እንደወደቀ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ከኮንትራክተሮቹ ጋር መረጃ ይለዋወጥበት የነበረ የቴሌግራም ግሩፕን ስራው ካለቀ በኋላ ሰው መረጃ እንዳይቀያየርበት መቆለፉን ለማየት ችለናል።

የቤቶች ልማት ኮንትራክተሮቹን ወደ ስራ ሲያስገባ ምንም አይነት ቅድመ ክፍያ እንዳይጠይቁ አስፈርሞ እንደነበር መሠረት ሚድያ የተመለከተው አንድ ሰነድ ያሳያል።

"ወደን ሳይሆን በግዴታ ነው ካለ ቅድመ ክፍያ ተስማምተን የገባነው፣ እንደዛ ካልተስማማን ወደፊት ምንም ስራ ከተማ ውስጥ መስራት አትችሉም ተብለን ማስፈራርያ ተሰጥቶን ነበር" ያሉት ግለሰቦቹ አሁን ላይ ለሁሉም ስራ ሳይከፈል የተከማቸው ገንዘብ 4.4 ቢልዮን ብር ገደማ እንደሆነ ጠቁመዋል።

መሠረት ሚድያ በዚህ ዙርያ ባደረገው ተጨማሪ ከ3 ሚልዮን ብር እስከ 42 ሚልዮን ብር የተያዘባቸው ኮንትራክተሮች እንዳሉ የተረዳ ሲሆን ከነዚህ ኮንትራክተሮች ውጪም በኮሪደር ልማት ዙርያ የመንገድ ግንባታ የተሳተፉ አቅማቸው ከፍ ያለ ኮንትራክተሮችም ክፍያ ተነፍጓቸው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችላል።

መረጃን መሠረት!

@MeseretMedia

31.2k 0 228 27 516



#የምርመራዘገባ አለም ባንክ በዲጂታል ፋውንዴሽን በኩል ለኢትዮጵያ የሰጠው 200 ሚልዮን ዶላር ምን ላይ እየዋለ ነው?

- በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ስር በግል አማካሪነት በአመት 120 ሺህ ዶላር የሚከፈለው ግለሰብ አለ

(መሠረት ሚድያ)- በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ይፋ ተደርጎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተጀመረው በ2013 ዓ/ም ነበር። በዚህ ወቅት ነበር የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት ብሄራዊ ኮሚቴ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር ሆኖ መንቀሳቀስ የጀመረው።

ፋውንዴሽኑ ዋና አላማው የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎትን ማስፋፋት፣ የህዝብ ተቋማት ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ዝርጋታ፣ የብሄራዊ መታወቂያ ስራ፣ የግል የቴክኖሎጂ ተቋማትን አቅም መገንባት በስራው ውስጥ የተካተቱ ነበሩ።

እንቅስቃሴው ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ በመንግስት በይፋ ቢገለፅም አንዳንድ አነጋጋሪ ድርጊቶች ግን መታየት ጀምረዋል።

ለምሳሌ የአለም ባንክ የዛሬ አራት አመት 200 ሚልዮን ዶላር መድቦለት ስራ በጀመረው የዲጂታል ፋውንዴሽን ውስጥ በአማካሪነት ተቀጥረው እየሰሩ ከሚገኙት መሀል ዶ/ር ስሜነው ቀስስ ሲሆኑ የትምህርት መስካቸው የእንስሳት ህክምና ቢሆንም በዚህ የዲጂታል ዘርፍ በአማካሪነት ተቀጥረው በአመት 130,000 ብር በአማካሪነት እንደሚከፈላቸው ለመሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ያሳያል።

በሌላ በኩል አቶ ሰለሞን ካሳ፣ ወይም ኢቢኤስ ቴሌቭዥን ላይ 'ቴክ ቶክ' በሚል ስያሜው የሚታወቀው ግለሰብ በተመሳሳይ በማማከር ቅጥር በአመት 120,000 የአሜሪካ ዶላር መቀጠሩ አነጋጋሪ እንደሆነባቸው ጉዳዩን የሚያውቁ ምንጮች ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል፣ ሰለሞን በአመት በርካታ ወራትን በአሜሪካ የሚያሳልፍ መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚ እንደሚያደርገው ይገልፃሉ።

ይህ ብቻ ሳይሆን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር "Internet Exchange Point" በተባለ ፕሮግራም የኢንተርኔት ፍሰት በሀገር ውስጥ የዳታ ማእከል እንዲያልፍ የሚያደርገው ፕሮጀክት በጀት ተይዞ የነበረ ቢሆንም ስራውን ይዞ የነበረው ተቋም ከቢሮው እንዲለቅ ተደርጎ በሌላ እንዲተካ እንደተደረገ እና ይህም ከገንዘብ ጥቅም ጋር የተያያዘ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

"አይቲ ፓርክ" ተብሎ በሚጠራው ማእከል ውስጥ በዶላር እየከፈሉ የተከራዩ በርካታ ተቋማት እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ገቢ ግን ወደየት እየገባ እንደሆነም እንደማይታወቅ እነዚህ ምንጮች ያስረዳሉ።

"በሸገር ከተማ ቡራዩ ውስጥ ለሚገኝ አንድ የአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች 'የቴክኖሎጂ ክህሎት ስልጠና ለመስጠት' በሚል ፋሪስ ለተባለ ድርጅት 21 ሚልዮን ብር በዲጂታል ፋውንዴሽን በኩል ተከፍሏል" የሚሉት እነዚሁ ምንጮች ይህም የተከናወነው በጨረታ ስም ሆኖ ሌሎች አቅም ያላቸው ተቋማት ገለል ተደርገው መሆኑን ጠቁመዋል።

የፋሪስ ድርጅት ባለቤት በቅርቡ የቴስላ 'ሳይበርትራክ' መኪና ካለቀረጥ ወደ ሀገር በማስገባቱ የሚታወቅ ሲሆን የዚህን መኪና ወደ ኢትዮጵያ መግባት ባለቤቱ አቶ ኤልያስ ይርዳው ማህበራዊ ሚድያ ላይ ለሀገሪቱ ትልቅ "የኢኖቬሽን" እምርታ ብሎ የገለፀበት መንገድ ብዙዎችን አነጋግሮ ነበር።

በዚህ ዙርያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩን ዶ/ር በለጠ ሞላን እንዲሁም የዲጂታል ፋውንዴሽን ሀላፊውን አቶ ተሰማ ገዳን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

45.3k 0 300 42 851



#Update ሰመረ ካሳዬ (ሰመረ ባርያው) በዛሬው እለት መፈታቱን መሠረት ሚድያ አረጋግጧል

@MeseretMedia

55.1k 0 24 25 727

ማህበራዊ ሚድያ ላይ ትችት በማቅረብ የሚታወቀው ሰመረ ካሳዬ (ሰመረ ባርያው) ታሰረ

(መሠረት ሚድያ)- በቅርብ አመታት ማህበራዊ ሚድያ ላይ የሚለቀቁ ቪድዮዎችን መነሻ በማድረግ ትችት እና ሽሙጥ በማቅረብ የሚታወቀው ሰመረ ካሳዬ (ሰመረ ባርያው) በትናንትናው እለት በፀጥታ አካላት አዲስ አበባ ውስጥ ተይዞ እንደታሰረ ታውቋል።

የመሠረት ሚድያ ምንጮች እንደጠቆሙት ሰመረ ትናንት እኩለ ቀን ገደማ ምሳ ከጓደኞቹ ጋር በልቶ እየወጣ በነበረበት ወቅት በፀጥታ አካላት ተይዞ ተወስዷል።

ሰመረ ብዙውን ግዜ ትችት የሚያቀርበው በማህበረሰቡ ዘንድ ጥያቄ በሚያስነሱ እና አነጋጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሆኖ ሳለ ለእስር መዳረጉ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው። ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ስራዎቹን በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል።

በተመሳሳይ መልኩ ገጣሚ እና የጦቢያ ግጥም በጃዝ ፕሮግራም አዘጋጅ ምስራቅ ተረፈ ከትናንት በስቲያ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በፖሊስ ለጥያቄ ትፈለጊያለሽ ተብላ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንደተወሰደች መሠረት ሚድያ መዘገቡ ይታወሳል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

62.1k 0 75 22 623

በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጂቡቲ ድንበር አቅራቢያ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት ሰዎች ተገደሉ

(መሠረት ሚዲያ)- ሐሙስ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እና ጂቡቲ ድንበር አቅራቢያ በደረሰ የድሮን ጥቃት ሰዎች መሞታቸውን እና መቁሰላቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ 

ጥቃቱ መጀመሪያ በሁለት አርብቶ አደሮች ላይ የተፈፀመ ሲሆን አንዱ ሲሞት አንዱ መትረፉ ታውቋል። በተጨማሪም 2 ሴቶች እና 5 ወንዶች በሌላ ጥቃት መገደላቸውን የመረጃ ምንጫችን ገልጸዋል፡፡

በኤሌዳአር ወረዳ ሂሉ እና ቲኪቦ ቀበሌ ሲያሪ ጣቢያ ሟቾችን ወደ ቤተሰብ ይዘው ሲመጡ በድጋሜ ህዝብ በተሰበሰበበት ጥቃት ተፈጽሟል ተብሏል።

"ባለን መረጃ መሰረት ጥቃት የፈጸመው የጅቡቲ መንግስት እንደሆነ እናምናለን" ብለው ለመሠረት ሚድያ የተናገሩት የመረጃ ምንጫችን ከዚህ ቀደም በጣቢያው ያሉ አርብቶ አደሮችን ከቦታው ለማስለቀቅ የጅቡቲ ወታደሮች ነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ተኩስ ይከፍቱ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ በአሜሪካ የሚኖሩ የአፋር ዲያስፖራ ማሕበር አባላት ባወጡት መግለጫ ድርጊቱን "ጨካኝ" በማለት አውግዘውታል።

የዲያስፖራ ማህበሩ ጥቃቱ የተፈጸመው በጂቡቲ መከላከያ ሀይል ድሮን መሆኑን ገልጾ በጥቃቱ ሲያሮ እና ኤሊዳር በተባሉ ቦታዎች 2 ወንድማማቾችን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውንና 3 ሰዎች ደግሞ በከፋ ሁኔታ በጽኑ መቁሰላቸውን በመግለጽ ድርጊቱን አውግዞ የሰላማዊ ዜጎች ግድያ እንዲቆም በመጠየቅ አለም አቀፍ ማህበረሰብ ማህበረሰብ፣ የሰብአዊ መብት ተሟቾችና መገናኛ ብዙሃን ትኩረት እንዲሰጡት ጠይቋል፡፡

በጉዳዩ ላይ በኢትጵያም ሆነ በጂቡቲ መንግስት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡

የሰሜኑ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት የሱዳን ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ መሬት ዘልቀው ገብተው ይገባኛል የሚነሳበትን መሬት መያዛቸው የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ ከደቡብ ሱዳን ዘልቀው የሚገቡ የሙርሌ ታጣዊዎችም ድንበር ጥሰው በመግባት በተደጋጋሚ ዝርፊያ እንደሚፈጽሙ ይታወቃል፡፡

የኤርትራ ጦርም ወደ ትግራይ ገብቶ ከፈጸመው ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰት በተጨማሪ ትንሽዋ አገር ጂቡቲም በኢትዮጵያ ምድር በሰላማዊ ዜገች ላይ የፈጸመችው ወታደራዊ ጥቃት አነጋጋሪ ሆኗል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

59.3k 0 21 34 453



ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ለአፍሪካ ህብረት ስብሰባ አዲስ አበባ እንደሚገኙ ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ከሁለት ሳምንት በኋላ በአዲስ አበባ በሚጀመረው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

ከስብሰባው አዘጋጆች ለመሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ እንደሚጠቁመው ዶ/ር ቴድሮስ ከበርካታ የአፍሪካ መሪዎች ጋር በመገናኘት እንደ ወባ፣ ቲቢ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ እና መሰል በሽታዎች ዙርያ የተሰሩ ስራዎችን ይገመግማሉ።

ዶ/ር ቴድሮስ የአለም ጤና ድርጅት ሆነው የዛሬ ሰባት አመት ገደማ ሲመረጡ በወቅቱ የነበረው መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎላቸው የነበረ ቢሆንም የዛሬ አራት አመት የትግራይ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የመንግስት ሚድያዎች እና አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት ዘመቻ ከፍተውባቸው ነበር። ዶ/ር ቴድሮስም በጦርነቱ ሲደርሱ ስለነበሩ ጤና ነክ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች በተደጋጋሚ ሲፅፉ እና ሲናገሩ ነበር።

ከዛም አልፎ የዛሬ ሁለት አመት ተኩል ገደማ የአለም ጤና ድርጅት ግለሰቡን ለሁለተኛ ግዜ በዳይሬክተር ጀነራልነት ሲመርጥ የኢትዮጵያ ተወካይ በግልፅ ተቃውሞ አሰምተው ነበር።

የአለም ጤና ድርጅት ሀላፊው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይህ ከአምስት አመት ወዲህ የመጀመርያቸው ይሆናል።

በዚህ ጉዟቸው ከኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር አመራሮች ጋር ተገናኘተው እንደሚመክሩ ቢጠበቅም ከጠ/ሚር አብይ አህመድ ጋር ውይይት ያደርጉ እንደሆን እስካሁን ማረጋገጫ አልተገኘም።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

48.3k 0 24 40 374

ገጣሚ እና የጦቢያ ግጥም በጃዝ ፕሮግራም አዘጋጅ ምስራቅ ተረፈ ለእስር ተዳረገች

(መሠረት ሚድያ)- ገጣሚ እና የጦቢያ ግጥም በጃዝ ፕሮግራም አዘጋጅ ምስራቅ ተረፈ ትናንት ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በፖሊስ ለጥያቄ ትፈለጊያለሽ ተብላ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንደተወሰደች ታውቋል።

የመሠረት ሚድያ ምንጮች እንደጠቆሙት ምስራቅ ዛሬ ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ፖሊስ ምርመራ ለማጣራት ጊዜ እንዲሰጠው ፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አቅርቧት ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ምርመራውን አጣርቶ እንዲያቀርብ 7 ቀን በመስጠት  ለጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጠሮ ሰቷል፣ ምስራቅ ተረፈ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተመልሳለች።

ምስራቅ የኪነጥበብ ምሽቶችን በሀገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ ሀገራት በማዘጋጀት እንዲሁም የራሷን ግጥሞች በማቅረብ በብዛት ትታወቃለች።

እንደ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ እና ገጣሚ ትእግስት ማሞ ያሉ የደመቁባቸውን ዝግጅቶች በማሰናዳት የምትታወቀው ግለሰቧ ግጥም፣ መነባንብ፣ ዲስኩር እንዲሁም ጥበብ እና ጥበብ ነክ ስራዎች ይበልጥ እንዲለመዱ እንደለፋች ብዙዎች ይናገራሉ።

ገጣሚ ምስራቅ አሁን ላይ የታሰረችበት ምክንያት ምን እንደሆነ ግልፅ እንዳልሆነ ታውቋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

40.8k 0 110 25 678

በዛሬው እለት የታጠቁ ግለሰቦች መቐለ ኤፍኤም 104.4 ሬድዮን ለመቆጣጠር ሙከራ አርገው ነበር ተባለ

(መሠረት ሚድያ)- በትግራይ ክልል ባለስልጣናት መሀል እየተካረረ የመጣውን ውዝግብ ተከትሎ በዛሬው እለት የታጠቁ ግለሰቦች የመቐለ ኤፍኤም 104.4 ሬድዮን ለመቆጣጠር ሙከራ አርገው እንደነበር ታውቋል።

ሙከራው የተካሄደው በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በሚመራው ቡድን አባላት መሆኑን ምንጮቻችን ጠቅሰው ሙከራው ግን ያልተሳካ ነበር ብለውታል።

"ታጣቂዎቹን ወደ ሬድዮ ጣቢያው ይዞ የገባው በእነ ዶ/ር ደብረፅዮን የተሾመ ዘመንፈስ ቅዱስ ፍስሃ የተባለ ግለሰብ ነው" ያሉት ምንጫችን ድርጊቱ ሲከሽፍ የኤፍኤም ሬድዮ ጣቢያውን ማህተም ይዘው ሲወጡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመዋል።

ምን ያህል ታጣቂዎች ወደ ሬድዮ ጣብያው እንደገቡ እንዲሁም አላማቸው ምን እንደነበር እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

51.5k 0 58 49 353

ከመንግስት ጋር ለመደራደር የተዘጋጀው የፋኖ ክንፍ ንግግሩ በአሜሪካ ወይም በአውሮፓ እንዲሆን ጠየቀ

(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ ታዛቢዎች በተገኙበት ከመንግስት ጋር ውይይት እንዳደረገ እና ለድርድር ዝግጁ እንደሆነ የገለፀው በእስክንድር ነጋ የሚመራው የፋኖ ክንፍ ድርድሩ በውጭ ሀገራት እንዲሆን እየጠየቀ መሆኑ ታውቋል።

የመሠረት ሚድያ ምንጮች እንደተናገሩት ታጣቂ ክንፉ ድርድሩ በአውሮፓ አልያም በአሜሪካ እንዲደረግ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።

መንግስት በዋናነት በእስክንድር ከሚመራው የፋኖ  ክንፍ  ጋር በቅርቡ በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ እንደተወያየ እስክንድር ከኢትዮ 360 ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ገልፆ ነበር። አክሎም በድርድሩ ላይ የኢጋድ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የአሜሪካ ተወካዮች መገኘታቸውን ገልፆ ነበር።

በውይይቱ ላይ በፋኖ ክንፉ በኩል የተነሱ ነጥቦች መከላከያ አካባቢውን በግዜያዊነትም ቢሆን ለቆ መውጣት፣ ክልሉን ማስተዳደር፣ በፌደራል መንግስቱ በስልጣን መወከል፣ የድሮን ጥቃት ማቆም፣ ለተጎዳው ህዝብ ለህይወት ሳይቀር ካሳ መክፈል እና የመሳሰሉት ናቸው ተብሏል።

በመንግስት በኩል ደግሞ ትጥቅ በመፍታት ወደ ማሰልጠኛ መግባት፣ ጎጃም አካባቢ ላይ ያለውን ነገር ማስተካከል፣ በየከተማው ያለውን አደረጃጀት መረጃ መቀበል፣ ተጠያቂ የሚሆኑ አባላቱን አሳልፎ መስጠት እንዲሁም በምክክር ኮሚሽኑ ውስጥ መካተት ናቸው ተብሏል።

"በመንግስት ዝግ ስብሰባ ላይ ሲያጨቃጭቅ የነበረው የነእስክንድር ክንፍ አቅም ጉዳይ ሲሆን ግምገማውም በሀገር ውስጥና በውጭ ተቀባይነትን ለማግኘት መነጋገሩ እንደ  አማራጭ ተወስዷል" ያሉን ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ምንጫችን ሸዋ ላይ ድርጅቱ የተሻለ አቅም እንዳለው፣ ነገር ግን ጎጃም ላይ የለም የሚባል ደረጃ ላይ እንደደረሰ መረጃ ቀርቦ ንግግር ተደርጎበታል ብለዋል።

"ቢያንስ ሸዋን ማቃለሉ እንደ ጥሩ እድል በመታየቱ እና የድርድር ዝርዝር መረጃም የሚቀበሉ አለም አቀፍ ተቋማትም በመንግስት የንግግሩ ቦታ ስለተጓጓዙ ውይይቱ ተደርጓል" በማለት ሂደቱን አስረድተዋል።

"ነገር ግን አሳሳቢው ጉዳይ አሁንም ልክ እንደነ ጃል ሰኒ እንዳይሆን ነው፣ ሙሉ ሰላም ለማምጣት የተወሰነ ቡድን ሳይሆን ሁሉንም አካታች መሆን አለበት" ያሉን ደግሞ በጉዳዩ ዙርያ አስተያየት የሰጡን ተንታኝ ናቸው።

"መንግስት ነገሮችን ያቀሉልኛል ብሎ እየሄደበት ያለው ይህ ነው። ሁሉም ወደ ንግግሩ መግባት አለበት፣ አልያ እንደ  ኦሮምያ አይነት ሁኔታ ይፈጠራል፣ ይባስ ብሎም በቀረው ፋኖ ታጣቂ እና በመንግስት መካከል የሚኖረው ሁኔታ ይባስ ሊካረር ይችላል" በማለት ለሚድያችን ተናግረዋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

65.7k 0 160 190 673
Показано 20 последних публикаций.