ክፍል ፪
ክርስቶስ
ክርስቶስ በዕብራይስጥ ማስያስ፣ በዐረብ መሢሕ፣ በግሪክ ክርስቶስ፣ በግእዝ ቅቡዕ ማለት ነው። ቅቡዕ ማለትም የተቀባ ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነ አምላክ፣ አምላክ የሆነ ሰው ነው። ወልደ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም የነሣውን ሥጋ ሲዋሐድ በአምላክነት አከበረው። ሥጋም ቃልን ስለተዋሐደ ከብረ። ስለዚህም ቅቡዕ ተባለ። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መባሉ በሰውነቱ እንደሆነ ሁሉ ቅቡዕ መባሉም በሰውነቱ ነው። በአምላክነቱ ክብርን (ቅብዕን) የሚሻ አይደለምና። ክርስቶስ ለተዋሐደው ሥጋ ክብር የሆነውም ራሱ ቃል ነው። እንጂ የቅባት እምነት አራማጆች እንደሚሉት መንፈስቅዱስ ቅብዕ (ክብር) አልሆነውም። በሥላሴ ዘንድ ቅብዕ፣ ተቀባዒ፣ ቅቡዕ የሚል አካላዊ ግብር የለምና። በማክበር፣ በክብር አንድ ስለሆኑ አብ አከበረው፣ ወልድ አከበረው፣ መንፈስ ቅዱስ አከበረው ቢል አንድ ነው። ለሥጋ ክብር የሆነው በተለየ አካሉ ቃል ነው። ምክንያቱም ሥጋ ቃልን ሆነ እንጂ ልብን ወይም እስትንፋስን አልሆነምና ነው። ሥጋ ከበረ መባሉ እንኳ ቃልን ሆነ ማለት ነውና።
ክፍል ፫ ይቀጥላል።