የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: не указана


በዚህ Channel ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ ፤ ቀኖና እና ትውፊት የጠበቁ ትምህርቶች ይተላለፉበታል፡፡
ለአስተያየት: ጥቆማና ጥያቄ በዚህ ያግኙን ☞ @Ethiopian_Orthodox_bot
Buy ads: https://telega.io/c/Ethiopian_Orthodox

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
не указана
Статистика
Фильтр публикаций


"ዘወረደ"
በእርሱ ፍቃድ በአባቱ ፍቃድ
በመንፈስ ቅዱስ ፍቃድ
ከሰማያት ወረደ ከድንግል ማርያም ተወለደ።

ዓለሙን እንዲሁ ወደደና
ከሰማያት በላይ ወረደና
በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት
ተወሰነ አምላከ አማልክት

  ከሰማያት የወረደው ፍቅር ስቦት የመጣዉ
  ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ፈራጅ ነዉ
               አዝ===
ቅድመ ዓለም ተወልዶ ያለ እናት
ድህረ ዓለምም ያለ አባት
የእግዚአብሔር ልጅ በእርግጥም ሰው ሆነ
ሁሉ በእርሱ ይኸው ተከናወነ

  ከሰማያት የወረደው ፍቅር ስቦት የመጣዉ
 ወልደ አብ ወልደ ማርያም ክርስቶስ አምላክ ነዉ
               አዝ===
የማይታይ ታየ በምድር
ረቂቁ ገዘፈ ስለፍቅር
ሥጋን ተዋሕዶ ሆነልን ፈውሥ
አማኑኤል የነገስታት ንጉሥ

ከሰማያት የወረደው ፍቅር ስቦት የመጣዉ    
ወልደ አብ ወልደ ማርያም እግዚአብሔር እርሱ ነዉ

©በዲያቆን ዘማሪ ቀዳሜጸጋ ዮሐንስ
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox




ዘወረደ
የዐብይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት

የመጀመሪያ የዐብይ ጾም መግቢያ እሁድ ዘወረደ ይባላል። በዚህ ቀን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወደ ምድር መውረድ ይሰበካል ይዘመራል። ሰውም በታላቅ ፍርሃት ወደ አምላክ መቅረብ እንዳለበት ይነገርበታል።

ደግሞም ጾመ ሕርቃል ይባላል። ስያሜውም በ614 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱንም አሸክሞ ሌላውን ንዋየ ቅዱሳን ዘረፈ: 60 ሺ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3 ሺ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማውንም አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል።
በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተስብሰበው ከ14 ዓመት በኃላ በ628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲያኑ የሮም ንጉስ ሕርቃል ይነግሩታል። እርሱም "ሐዋሪያት ሰው የገደለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው?" አላቸው "እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን እንጾማን" ብለን አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን በሚገባ ጾመውታል።

ምስባኩም:- መዝ ፪፥፲፩
"ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሰዩ ሎቱ በረዓድ አፅንእዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐፅ"
"ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ በርአድም ደስ ይበላችሁ ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቆጣ"

በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡት ጥቅሶች:
-ዕብ ፲፫፥፯-፲፯
-ያዕቆብ ፬፥፮ እስከ ፍጻሜ
-የሐዋ ሥራ ፳፭፥፲፫ እስከ ፍጻሜ

ወንጌሉም:- ዮሐ ፫፥፲-፳፭
"¹⁰ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?
¹¹ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም።
¹² ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?
¹³ ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።
¹⁴-¹⁵ ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል።
¹⁶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።
¹⁷ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።
¹⁸ በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።
¹⁹ ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው።
²⁰ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤
²¹ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።
²² ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር።
²³ ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥
²⁴ እየመጡም ይጠመቁ ነበር ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ አልተጨመረም ነበርና።
²⁵ ስለዚህም በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ ማንጻት ክርክር ሆነ።"

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox




በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ዐብይ ጾም
-------------------------------
@Ethiopian_Orthodox
-------------------------------
ጾም ማለት "ተወ"፣ "ታቀበ" ፣"ታረመ" ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ነው። ፍቺውም ምግብ መተው ፤መከልከል፤ መጠበቅ ማለት ነው።
ጾም ማለት ሰውነት ከሚያስፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል፤ መወ'ሰን ማለት ነው። ወይም ሰውነት የሚያምረውን የሚያስጎመጀውን ነገር መተው ማለት ነው። ጾም ከሃይማኖት ጋር ዝምድና ስላለው ሃይማኖት ባለበት ሁሉ ጾም አለ።
✳️ ጾም በብሉይ ኪዳን ከፍተኛ ቦታ አለው።
ነብያት ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ወራት እህል ውሃ በአፋቸው አይገባም ነበር። (ዘፀ 30÷34-28)
✳️ በኃጢአት ብዛት የታዘዘውን የእግዚአብሔርን መዓት የሚመልሰው ሕዝቡ በጾም ሲለምኑት ሲማልዱት ነበር። (ዮሐ 2÷7-10)
✳️ በሐዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሰራሽ ህግ ሳይሆን እራሱ መድኃኒታችን በመዋዕለ ሥጋዌው የሥራ መጀመሪያ አድርጎ የሰራው ህግ ነው።
✳️ ይህ ብቻ ሳይሆን በቁራኝነት አብሮ የሚኖር መንፈስ እርኩስ ሰይጣን እንኳን በጾም የሚወገድ መሆኑን መድኃኒታችን ተናግራል።(ማቴ 17÷21)
✳️ ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የታዘዙት ሐዋርያትም ከመንፈስ ቅዱስ በየጊዜው ትዕዛዝ የሚቀበሉበት በጾም እና በጸሎት ላይ እንዳሉ ነበር።(ሐዋ 13÷2)
✳️ ለስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ ዲያቆናት ቀሳውስት የሚሾሙት በጾምና በጸሎት ነበር። (ሐዋ 13÷3)

ጾምስ በታወቀው እለት በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ መከልከል ነው።
ጾም ማለት ጥሉላት ማባልዕት ፈፅሞ መተው ሰውነትንም ከመብልና ከመጠጥ ከሌላውም ክፉ ነገር ሁሉ መጠበቅ፣ መግዛት፣ መቆጣጠር፣ በንስሐ ታጥቦ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ "ይቅር በለኝ" በማለት ቅድመ እግዚአብሔር በመንበረከክ ምሕረት ለአምላክ ለመቀበል መዘጋጀት ነው።

ፆም ነፍስን ቁስልን የምትፈውስ፣ ሀይለ ፍትወትን የምታደክም የበጎ ምግባር ሁሉ መጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጸጋን የምታሰጥ የወንጌል ስራ መጀመሪያ ፣ የፅሙዳን ክብራቸው፣ የደናግል የንፅህና ጌጣቸው ፤የንፅህና መገለጫ ፣ የጸሎት ምክንያት እናት፤ የእንባ መናኛ መፍለቂያ አርምሞን የምታስተምር፣ ለበጎ ስራ ሁሉ የምታነቃቃ፣ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትህትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት።
ከህገ ልቦና ከነበሩ አበው አንስቶ በዘመነ ኦሪት እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ በተለያዩ ጊዜያት የነበሩ ቀደምት አበው ነቢያት፣ ነገሥታት፣ ካህናት በፆምና በጸሎት ፅመድ ሆነው እግዚአብሔር አምላካቸው ከክፉ ነገር እንዲሰውራቸው በይቅርታ እንዲጎበኛቸው ሀይልም እንዲጎናፅፋቸው ተማፅነው ሀሳባቸውን ፈፅሞላቸዋል።

በሀዲስ ኪዳን ጾም ስለ ፅድቅ ተብሎ መከናወን ያለበት አብይ ተግባር ነው።// ማቴ 5÷6//
ስጋዊ ጥቅምን ለማግኘት ተድላ ሰጋን በመሻት ሳይሆን ዘላለማዊ መንግስት ለመውረስ ስለ ፅድቅ ተብሎ የሚፈፀም ነው።
ጾም እንደምን ነው ቢሉ የስጋ ምግባር ነው። ምፅዋት የገንዘብ ግብር እንደሆነች አንድም ምፅዋት ስጋን መገበር ነው።
ምፅዋት ገንዘብ መገበር እንደሆነች ~~~ ስለዚህም የሚፆም ሰው በፈቃደ ስጋው ላይ ድልን ይቀዳጃል።
በእምነት ሆኖ የለመነውን እግዚአብሔር ይሰጠዋል። ሰማያዊ የሆነውን ምስጢር ለማየት ከዓለማዊነት ነገሮች ተለይቶ ይነጠቃል። በዓለም እየኖረ ከዓለሙ ይለያል። ከዓለም አይደለምና //ዮሐ 15÷19//

🔰ዐብይ ጾምም ቤተክርስቲያናችን እንድንጾም ካወጀችልን ጾም አንዱ ነው።
አብይ ጾም የተለያዩ ስሞች አሉት:
፩. ዐብይ ጾም: ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የአርባ ቀን ጾም በመሆኑ እንዲሁም ዐብይ እግዚአብሔር ወዓቢይ ኀይሉ ዓቢይ እግዚአብሔር ወብዙኃ አኰቴቱ የተባለ ጌታ የጾመው ስለሆነ፣ //መዝ 47÷1 መዝ 146÷5//
ዐብይ ጾም መባሉ ትልቅና ታላቅ ጾም መሆን ለማሳወቅ ነው። ይህ ጾም ታላቅ መባሉም ለ55 ቀናት ያህል መጾሙና ከሌሎች አፅዋማት ጋር ሲነጻጸር በቁጥር መብለጡ ብቻ ሳይሆን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንጦስ መጾም ሳይገባው ለእኛ አርአያና ትልቅ ምሳሌ ለመሆን የጾመው ጾምም በመሆኑ ነው።

፪. ሁዳዴ ጾም: ይህም የመንግሥት እርሻ ወይም ማንኛውም የሕዝብ ብዛት ያለበት ሥራ ሁዳድ ስለሚባል ሲሆን ከአጽዋማት ሁሉ ብዙ ቀናት ስለሚጾምና ኃያሉ አምላካችን ስለጾመው ነው።፣ /አሞ 7÷1 //
፫. በዓተ ጾም : ፆም መግቢያ፣ መባቻ ወይም ጾሙ የሚሰፍርበት በዓል ማለት ነው
፬. ጾመ አርቦ: ጌታችነ ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመዉ 40// አርባ ቀን ስለሆነ ነው //ማቴ 4÷1
፭. ጾመ ኢየሱስ : ጾሞ ፣ ጹሙ ብሎ ስላዘዘን፣
፮. ጾመ ሙሴ : ቅዱስ ያሬድ በዘወረደ ሰኞ "ዕዝል ከመዝ ይቤ ሙሴ እስመ ለዓለም ፣ ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት" እያለ በጾመ ድጓ ስለ ዘመረ ነው።

🌿ዐብይ ጾም ጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የአርባ ቀን ጾም ነው። //ማቴ 4÷1
ምእመናንም ጌታቸው ያደረገውን ምሳሌ ተከትለው ይጾሙታል።
🌿ዐብይ ጾም ስምንት ሳምንታት //55 ቀኖች // አሉት። 7//ሰባት ቅዳሜ 8//ስምንት እሁድ ይገኛሉ። አስራ አምስት ቀን 55//ማለት ነው። ከጥሉላት እንጂ ከእህል ወኃ ስለማይጾሙ የጾሙ ወራት አርባ ቀን ብቻ ይሆናል።

የዐብይ ጾም ሶስት ክፍሎች
፩. ዘወረደ ( ጾመ ሕርቃል)፦ ይህም ጾሙ ከሚገባበት ሰኞ ጀምሮ እስከ እሁድ ያረሰ ያለው 7 ቀን ነው።
፪. የጌታ ጾም፦ ይህም ከቅድስት ሰኞ እስከ ሆሣዕና ዋዜማ ዓርብ ድረስ ያለው አርባ ቀን ነው።
፫. ሕማማት፦ ይህ ጌታችን በአልዓዛር ቤት ለማዕድ ከተቀመጡበት የሆሳዕና ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ሥዑር ቅዳሜ ያለው መከራን የተቀበለበት 8 ቀን ሕማማት ነው።
ይህም ፯+፵+፰=፶፭(7+40+8=55)ቀን ይሆናል።

የዐብይ ጾም ሳምንታት 8 ሲሆኑ:
፩. ዘወረደ
፪. ቅድስት
፫. ምኲራብ
፬. መጻጉዕ
፭. ደብረ ዘይት
፮. ገብርሔር
፯. ኒቆዲሞስ እና
፰. ሆሣዕና ናቸው።

ጾሙን ጾመን ድኅነት የምናገኝበት የበረከት እንዲሁም ቤተክርሰቲያናችንንና ሐገራችንን ከመዓት የምንታደግበት ያድርግልን! አሜን!

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox


"ኪዳነ ምሕረት እናቴ"
ኪዳነ ምሕረት እናቴ አማልጅኝ እኔን ከልጅሽ
የፍቅር እናት ነሽና አማልጅኝ እኔን ከልጅሽ
የሰላም እናት ነሽና አስታርቂኝ እኔን ከልጅሽ

የተገለጠው ብርሃን ከምሥራቅ የተወለደው
በፍቅር ሰንሰለት ታስሮ ዓለምን ሁሉ አዳነው(፪)

አዝ===

በረሃውን ባሰብኩት ጊዜ ያንን የአሸዋ ግለት
አንቺ ትንሽ ብላቴና ኧረ እንዴት ቻልሽው በእውነት(፪)

            አዝ===

ዝም ብዬ ይደንቀኛል የአምላክን ሥራ ሳስበበው
ምክንያት አንቺን አድርጎ ይህንን ዓለም አዳነው(፪)

            አዝ===

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox




የካቲት ፲፮
ኪዳነ ምሕረት


የካቲት ዐሥራ ስድስት በዚችም ዕለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓልን ያደርጋሉ። በዚች ዕለት መታሰቢያዋን ለሚያደርግ ስሟን ለሚጠራ ለድኆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተቀብላለችና።

ይህችም የከበረች እመቤታችን ልጅዋ ንጹሕ ሥጋዋን ተዋሕዶ ከብቻዋ ኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ፈጽሞ ስለእኛ መዳን ወዶ ያደረገውን መከራ ተቀብሎ ሙቶ ተነሥቶ ከዐረገና በአባቱ ዕሪና ከተቀመጠ በኋላ እርሷን እናቱን ማርያምን በደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ዘንድ ትቷት ነበር እነሆ ልጅሽ እርሱንም እነሆዋት እናትህ ብሎ አደራ እንዳስጠበቀው።

ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ማርያም ትጸልይ ዘንድ ያለ ማቋረጥ ወደ ልጅዋ መቃብር ሁል ጊዜ ስትሔድ ኖረች ይኸውም ጎልጎታ ነው።

አይሁድም በአዩዋት ጊዜ ቍጣንና ቅናትን ተመልተው በድንጊያ ሊወግሩዋት ወደዱ እግዚአብሔርም ከዓይናቸው ሠወራት ከዚህም በኋላ ዳግመኛ መጥታ በዚያ እንዳትጸልይ ተማክረው ከመቃብሩ ዘንድ ጠባቂዎችን አኖሩ እርሷ ግን በየዕለቱ መሔድን አላቋረጠችም ጠባቆችም አያይዋትም የልጅዋ የጌትነቱ መጋረጃ ሠውርዋታልና መላእክትም መጥተው ያገለግሏታል ጌታችንም ዘወትር ይጐበኛታል የምትሻውንም ይፈጽምላት ነበር።

ከዚህም በኋላ መላእክት ወደ ሰማይ አሳረጓትና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳዩዋት አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብም ወዳሉበት አደረሱዋት ከአዳም ጀምሮ እስከዚያ ዕለት በአካለ ነፍስ ያሉ አባቶች ሁሉ አንቺን ከሥጋችን ሥጋን ከዐፅማችን ዐፅምን ለፈጠረልን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የአምላክ ልጅ ከአንቺ ሰው በመሆኑ በአንቺ ድህነት አግኝተናል ከጥፋትም የሕይወት ወደብ ሆነሽልናልና እያሉ ሰገዱላት።

ከዚያም ወደ ተወደደ ልጅዋ የእሳት መጋረጃ ወደተተከለበት ወደ ጌትነቱ ዙፉን አደረሷት ጌታችንም እጇን ይዞ ወደ ውስጠኛው መጋረጃ አስገብቶ ከጌትነቱ ዙፋን ላይ አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጣት ያዘጋጀላትንም ዐይን ያላየው ጆሮ ያልሰማው በሰው ልቡና ያልታሰበ ተድላ ደስታን ሁሉ ነገራት።

ከጌትነቱ ዙፋንም በታች የእስራኤል ንጉሥ አባቷ ዳዊትን የነቢያትና የመላእክት ኅበር እንደ ግድግዳ ከበውት በመሰንቆ ሲያመሰግን አየችው እንዲህም ይላል "ልጄ ስሚ በጆሮሽም አድምጪ ወገንሽን የአባትሽንም ወገን እርሺ ንጉሥ ደም ግባትሽን ወዷልና እርሱም ጌታሽ ነውና።"

ዳግመኛም የሥቃይን ቦታ ያሳዩዋት ዘንድ መላእክት ከዚያ ውሰዷት ለሰይጣንና ለሠራዊቱ በእርሱ ጐዳና ለሚጓዙ ሁሉ ወደተዘጋጀ ወደጨለማው ዳርቻ አደረሷት እመቤታችን ማርያምም ወዮልኝ ወደዚያ እንዳይመጡ ለሰው ልጆች ማን በነገራቸው አለች መልአኩም አመቤቴ ቡርክት ማርያም ሆይ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይኖራልና ለአንቺም ከአንቺ በኋላም በቃል ኪዳንሽ ለሚታመኑ አትፍሪ አላት ከዚህም በኋላ ወደ ቦታዋ መለሷት።

ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ድንግል ማርያም ስለ ኃጥአን እጅግ እያዘነች ኖረች እንደ ዛሬይቱም የካቲት ዐሥራ ስድስት ቀን በጎልጎታ ቦታ ቁማ ወደ ልጇ እንዲህ ብላ ለመነች ልጄ ሆይ በእግዚአብሔር አባትህ በክርስቶስ ስምህ ከአንተ ጋርም ህልው በሆነ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ አማፅንሃለሁ ዓለም ሁሉ ሊሸከምህ የማይችል ሲሆን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በተሸከመችህ ማሕፀኔ አማፅንሃለሁ ልጄ ሆይ ያለ ሕማም ያለ ድካም ከእኔ በመውጣትህ በመወለድህ በአሳደጉህ ጡቶቼ በሳሙህ ከንፈሮቼ በአቀፉህ እጆቼ ከአንተ ጋር በተመላለሱ እግሮቼ አማፅንሃለሁ ። በውስጡ በተኛህበት በረት በተጠቀለልክበት ጨርቅ አማፅንሃለሁ የምወድህ ልጄ ሆይ በልቡናዬ ያለውን ሁሉ ትፈጽም ዘንድ የልመናዬን ቃል ሰምተህ ወደእኔ ትመጣ ዘንድ ወዳንተ ፈጽሜ እማልድሃለሁ።

የብርሃን እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲህ ብላ በጸለየች ጊዜ እነሆ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወረደ ከእርሱም ጋር አእላፍት መላእክት አሉ በዙሪያውም ሁነው ያመሰግኑታል እርሱም እናቴ ማርያም ሆይ ምን ላድርግልሽ አላት እመቤታችንም ለተወዳጅ ልጅዋ እንዲህ ብላ መለሰችለት ልጄ ወዳጄ ሆይ ጌታዬና ፈጣሪዬ አለኝታዬና መጠጊያዬ በእናቴ ማሕፀንም ሳለሁ ባንተ ጸናሁ አንተም ጠበቅኸኝ ሁልጊዜም ስም አጠራሬ አንተ ነህ።

አሁንም ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ ቃሌንም አድምጥ እኔ እናትህ እኔም አገልጋይህ የምለምንህ ይህ ነው መታሰቢያዬን ለሚያደርጉ በስሜ አቢያተ ክርስቲያን ለሚሠሩ ወይም የተራቆተውን ለሚያለብሱ የተራበውን ለሚያጠግቡ የተጠማውንም ለሚያጠጡ የታመመውን ለሚጐበኙ ያዘነውን ለሚያረጋጉ የተከዘውንም ደስ ለሚያሰኙ ወይም ምስጋናዬን ለሚጽፉ ልጆቹንም በስሜ ለሚሰይም በበዓሌም ቀን በማኅሌት ለሚያመሰግን አቤቱ ዐይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰውም ልቡና ያልታሰበውን በጎ ዋጋ ስጣቸው በአማላጅነቴም የሚታመነውን ሁሉ ከሲኦል ነጻ አድርገው ከአንተ ጋር የደረሰብኝን ረኃቡንና ጥማቱን መከራውን ሁሉ አስብ አለችው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዳልሽው ይሁንልሽ የሰጠሁሽም ቃል ኪዳን እንዳይታበል በራሴ ማልኩልሽ አላት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን ድንግል ማርያም በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox


በቀጣይ ምዕራፍ ስምንት ክፍል ሁለት:
>

ለአስተያየትና ጥያቄዎቻችሁ @Ethiopian_Orthodox_bot ተጠቀሙ።

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox


ከላይ የተጠቀሰው ቃል በገዛ ፈቃድ በንጽሕና መኖርን የሚያመለክት እንጂ አካልን ስለ መቁረጥ የተነገረ አይደለም፡፡ አካል ቢኖርም ሥራውን ካልሠሩበት የሌለ ያህል ነውና ‹ጃንደረባ› በማለት የተናገረው ስለዚህ ነው:: ንዑስ መሌሊትን (ኀፍረተ አካልን) መቁረጥ ግን ከመንግሥተ ሰማያት ያወጣል፤ ከክህነትም ያሽራል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መላ ዘመንን በድንግልና መኖር የፈቃድ ኑሮ መሆኑን ለማመልከት «ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም» ይበል እንጂ መልካም ምክርና ለጽናት ምላሌ የሚሆን ድንግልናዊ ኑሮ ግን አለው፡፡ ስለዚህ «ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁ» በማለት ተናግሯል። 1ቆሮ7፥7

ሐዋርያው ከሕይወቱ ምሳሌነት በተጨማሪ ምክሮቹ በመሉ በድንግልና መኖርን የሚያበረታቱ ነበሩ «…ከጌታ ምሕረትን የተቀበልኩ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ» ካለ በኋላ «እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው› በማለት በዘመኑ ካለው ችግር የተነሣ በድንግልና መኖር መልካም መሆኑን አስረድቷል፡፡ 1ቆሮ7፥25-26

ሐዋርያው «ስለ አሁኑ ችግር» በማለት የተናገረው ቃል ሊሠመርበት የሚገባ ነው፡፡ ሐዋርያው በነበረበት ዘመን ድንግልናዊ ኑሮን ከመንፈሳዊ ጠቀሜታው ባሻገር ክጋብቻ ኑሮ ይልቅ የተሻለ የሚያደጉት ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ ይህ እኛ ያለንበት ዘመን ደግሞ ከዚያን ጊዜ ይልቅ ድንግልናዊ ኑሮን የተሻለ የሚያደርጉት ችግሮች በመጠንም ሆነ በዓይነት የበረከቱበት ወቅት ነው:: ስለዚህ ምንም እንኳን መላ ዘመንን በድንግልና መኖር አስቸጋሪ መስሎ ቢታይም እስከ ጋብቻ ድረስ እንኳን ድንግልናን ጠብቆ መቆየት ከድንግልናዊ ኑሮ ጥቅሞች እንድንጋራ የሚያደርግ ነው::


ሰበብ አስባብ እያበዛ በራሱ ተነሣሽነት ዝሙት እንዳልፈጸሙ በመናገር ድንግል መሆን እንደ ነበረባቸው ወይም እንደ ሆኑ እንደሚናገሩ ሰዎች እግዚአብሔር የሚያፍርባቸው ስዎች የሉም።
ለሌሎች ሰዎች ያልተደረገ ገቢረ ተአምር እንዲደረግልን ማለት በራሳችን ስሕተት ያጠፋነውን ድንጋሌ ሥጋ እንዲመለስልን የምንሻ እኛ ከእነሱ የተለየ በጎ ሥራ ምን ሠርተን ነው? ይህ ሐሳብ በእውነት የትዕቢት ሐሳብ ነው በዚህ መልኩ በትዕቢት ማሰብ እንደማይገባ ደግሞ «እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ፀጋ እናገራለሁ::» ሮሜ12፥3 በማለት ሐዋርያው ምክር ለግሷል፡፡

መደንገል እስከ መቼ?

ድንግልናን ስለመጠበቅ ሲነሣ ብዙ ጥያቄዎች በሕሊና መውጣትና መውረዳቸው አይቀርም፡፡ ከእነሱም ውስጥ አንዱ እስከ መቼ? የሚል ነው:: የዚህ ጥያቄ መልስ እንደ ሰዉ የአኗኗር ዘይቤ ይለያያል:፡ ለአንዱ ጋብቻውን እስኪፈጽም ድረስ ሲሆን ለሌላው ደግሞ ለዘለዓለም ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ለሚመነኩሱ ሰዎች እስከ ዕድሜያቸው ፍጻሜ ድረስ ማለት ነው::

እስከ ዕድሜ ልክ መደንገል

ድንግልናቸውን እስከ ሞት ድረስ መጠበቅ የሚኖርባቸው በድንግልና የመነኮሱ መነኮሳት ናቸው:: ምንኩስና ከሴት ርቆ እስክ ሕይወት ፍጻሜ ለመኖር የሚደረግ ውሳኔ ነውና፡፡በእርግጥ ምንኩስና ድንግሌ ሥጋ ያላቸው ሰዎች ብቻ የሚጓዙበት ጐዳና አይደለም:: ባለ ትዳር የነበሩ ወይም ሳያገበ ለዝሙት ተጋልጠው ድንጋሌ ሥጋቸውን ያጡ ብዙ ሰዎችም በንስሐ ተመልሰው ይኖሩበታል:: ይህም ቢሆን እንደ ቀላል የሚታይ ውሳኔ አይደለም:: ነገር ግን ምንኩስና የዓለምን ኑሮ እንደ ልብ ኖረውት ሲስለች ብቻ የሚገባበት አድርጐ ማሰብ ስሕተት ነው፡፡

ምንኩስና በድንግልና ሲሆን ብዙ ጸጋና ክብር ያመጣል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ከመመንኮስ በተጨማሪ የግድ ድንግል ሆኖ መገኘትን የሚጠይቁ ብዙ ታላላቅ መንፈሳዊ የሹመት ደረጃዎችና የአኗኗር ዘይቤዎች ይገኛሉ፡፡

በድንግልና መመንኮስ ጣዕመ ዓለምን ሳይቀምሱ በመሆኑ ከምንኩስናም በኋላ ለሚኖሩት የንጽሕና ኑሮ አጋዥነት ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም ከመነኮሱበት ዓላማ ጋር የማይስማማ በልቡናቸው የሚቀር የዓለማዊ ኑሮ አሻራ ባለመኖሩ ነው:: «ያላዩት አገር አያናፍቅም» ይባል የለ?

በእርግጥ ይህን የመሰለ የምናኔ ኑሮ ለመኖር ስጦታ ያስፈልጋል፡፡ «ነገር ግን ለእያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስጦታ አለው፥ አንዱ እንደዚህ ሁለተኛውም እንደዚያ› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው መመንኮስ የተሰጠው ይኖራል፡ ማግባትም የተሰጠው ይኖራል:: 1ቆሮ7÷27

ምንም እንኳን በጋብቻም ሆነ በምንኩስና መኖር ሁለቱም የእግዚአብሔር ስጦታዎች ቢሆኑም በጋብቻ መኖር ለሁሉ የተሰጠ ሲሆን ምንኩስና ግን መመረጥና መታደል የሚጠይቅ ነው:: ይህን በተመለከተ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ይህ ነገር ለተሰጣቸው እንጂ ለሁሉ አይደለም....ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው::» በማለት ተናግሯል:: ማቴ19፥11

«ለአባታችን ለቅዱስ ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ፣ ለዮሐንስ ደግሞ ድንግልና፥ ለአባታችን ለጳውሎስም የቤተ ክርስቲያን ብርሃኗ እርሱ ነውና መልእክታትን አብዝቶ መጻፍ ተሰጠው› በማለት ሥርዓተ ቅዳሴ በስም ለተጠቀሱት ሐዋርያት የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ! በድንግልና መኖርና መልእክታትን መጻፍ ለእያንዳንዳቸው እንደ ተሰጣቸው ይገልጻል:: ከዚህም በድንግልና መኖር ለጥቂቶች የሚሰጥ ጸጋ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ሰው ሁሉ በተሰጠው ጸጋ መኖር ይገባዋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውለስ በድንግልና መኖር (ምንኩስና) የተሰጠው በድንግልና ጋብቻም የተሰጠው በትዳሩ ጸንቶ እንዲኖር «ወንድሞች ሆይ እያንዳንዱ በተጠራበት እንደዚህ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር፡፡» በማለት መክሯል:: 1ቆሮ7÷24

ድንግልናን በሕይወት ዘመን በሙሉ ጠብቆ በምንኩስና መኖር ከስጦታነቱ በተጨማሪ በፈቃደኝነት ሊደረግ የሚገባው ነገር ነው እንጃ. የሚገደዱበት ተግባር አይደለም፡፡ ሐዋረያው ድንግልናዊ ኑሮ ውዴታ እንጂ ትእዛዝ አለመሆኑን ሲገልጽ ‹‹ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም» በማለት ተናግሯል::

በድንግልና ተወስኖ ለመኖርም ሆነ ወደ ጋብቻ ለመሄድ የድንግልና መኖር አስፈላጊ በመሆኑ ድንግልናን ጠብቆ ለመኖር ስጦታችን የትኛው እንደሆነ ማወቅም አያስፈልገንም፡ በድንግልና ኖረን ከመነኮስን እሰይ ያሰኛል፡ ካገባንም ይበል የሚያሰኝ ነውና ድንግልናን ክወዲሁ ጠብቆ መኖር ይገባል፡፡

እስከ ጋብቻ ድረስ ድንግልናውን ጠብቆ ኖሮ ያገባ ሰው ሐዋርያው እንደተናገረው መልካም አደረገ:: 1ቆሮ7÷38 የታዘዘውን በሚገባ ፈጽሟልና ክበጎ ባርያዎች ጋር ይቆጠራል:: ያላገባ ወይም መላ ዘመኑን በድንግልና ለመኖር የወሰነ ደግሞ ከታዘዘው በላይ የትሩፋት ሥራ ሠርቷልና የተሻለ አደረገ፡፡ 1ቆሮ7÷38

በጎ ሎሌን ጌታው ሸማ አጥበህ፤ ማገር ቆርጠህ ና ብሎ ያዘዋል:: እርሱ ግን ጌታዬ አይችልም በማለት አዝኖልኝ ነው እንጂ
ዓሣን ለወጥ፣ ለማገር ደግሞ ልጥ ጨምሬ ይዤ ብሄድ ይከፋልን? ብሎ ልብሱን ካጠበና ማገሩን ከቆረጠ በኋላ ዓሣውንና ልጡን ጨምሮ ይመለሳል:: እንደዚሁ ሁሉ መነኮሳትም የፈጣሪ ታማኝ ባሪያዎች ናቸው:: ስለዚህ ፈጣሪ ሚስት አግብታችሁ፣ አሥራት፣ በኩራቱንና ቀዳምያቱን አውጥታችሁ፣ ሥጋውን ደሙን በሚገባ ተቀብላችሁ ኑሩ ቢላቸው ሚስት ማግባትን ተዉ፡ ይህንንም ያደረጉት ባሕሪያቸው ደካማ ነውና አይቻላቸውም ብሎ ፈጣሪያችን አዝኖልን ነው እንጂ ከሕገ ሥጋ ሕገ ነፍስ፣ ከሕገ እንስሳ ሕገ መላእክት እንደሚበልጥ የታወቀ አይደለምን? በማለት ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለው በበጎ ፈቃደኝነት ነው እንጂ ተገደው አይደለም:: በዚህ ሥራቸው የተሻለ አድርገዋልና እንደ ታማኝ ሎሌ ይመሰገናሉ አንጂ አይነቀፉም:: ማቴ13፥4-8 (ትርጓሜ)

መላ ዘመንን ከሴት ርቆ ንጽሕ ጠብቆ በድንግልና መኖር በግዴታ ወይም በትእዛዝ የሚደረግ ሳይሆን ከፍቅረ እግዚአብሔር የተነሣ በፈቃደኝነት የሚደረግ መሆኑን «በእናት ማሕፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፥ ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፥ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ» በማለት ጌታችን የተናገረው ቃል ያስረዳል:: ማቴ 19÷12

«በእናት ማሕፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አለ› ማለት አንደ ኤርምያስ እና ዮሐንስ መጥምቅ ከማሕፀን ጀምሮ በምናኔ ለምንኩስናና ለድንግልዊ ኑሮ ተመርጠው የተለዩ አሉ ማለት ነው፡፡ “በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማሕፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ› እንዳለው ማለት ነው:: ኤር1፥5

«ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ» ማለት መምህራን መክረውና አስተምረው ንጹሐን ያደረጓቸው ለድንግልናዊ ኑሮ ያበቋቸው አሉ ማለት ነው:: ለምሳሌ:- ሙሴ ኢያሱን፣ ኤልያስ ደግሞ ኤልሳዕን ቀርጸው ለዚህ ዓይነት የመዓርግ ኑሮ አብቅተዋቸዋል፡፡

«ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ» ማለት ፈጣሪያችን አይችሉትም በማለት አዝኖልን ነው እንጂ ሳያገቡ መኖር የተሻለ ነው በማለት በራሳቸው ፈቃድ ድንግልናቸውን ጠብቀው ከሴት ርቀው መንግሥተ ሰማያትን የሚጠባበቁ አሉ ማለት ነው፡፡


«ድንግል በክልኤ»

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም «ድንግል በክልኤ» እየተባለ በቅዱሳት መጻሕፍት ተነግሮላታል፡፡ ስለ ድንግልናዋ ትንቢት ተነግሯል ምሳሌም ተመስሏል:: ይህም በሁለት ወገን ማለትም በሥጋና በነፍስ ድንግል መሆኗን ለማመልከት ነው:: የደናግልም ሁሉ መመኪያቸው እርሷ ናት፡፡

እመቤታችን ቅድመ ፀኒስ፣ ጊዜ ፀኒስ፣ ድኅረ ፀኒስ ድንግል ናት:: ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድም ድንግል ናት፡፡ ቅዱሳንን ሁሉ ስለ ድንግልኗ ምስጋናና ክብር ያለ ማቋረጥ እንዲናገሩ ያደረገ ይህ ንጽሕናዋ ነው፡፡ ‹‹ስብሐተ ድንግልናኪ ወትረ ይነግር አፉየ› እንዲል:: (መልክዐ ማርያም)

የእመቤታችንን ድንግልና «ድንግልና» በመባሉ ብቻ ካልሆነ በቀር የፍጡራን ድንግልና በምንም አይመሳሰለውም፡፡ ስለ እመቤታችን ድንግልና ለመናገር ሌላ ትልቅ ጥራዝ ያለው መጽሐፍ መጻፍ ያስፈልጋል:: ስለድንግልና ለመናገር ስንፈልግ ስለ እርስዋ ከተጻፉት መንፈሳዊ ድርሰቶች አስረጅ አድርገን ብዙ ብንጠቅስም በድንግልና ፍጽምት ከመሆኗ የተነሣ የፍጡራንን ድንግልና ሕጹጽነት ለማየት እንዲረዳን ነው እንጂ ለማመሳሰል አይደለም፡፡

የእመቤታችንን ድንግልና የመላእክትም ንጽሕና አይደርስበትም፡፡ ለዚህም ማስረጃው የተአምረ ማርያም መቅድም እንዲህ ሲል ያሰፈረው ቃል ነው:: «ለመኑ ተውህቦ ተደንግሎ እለ እምውሉደ ሰብእ፣ ለመላእክትኒ ኢተክህሎሙ ተደንግሎ ሕሊና እስመ አበሱ በፍትወት ወወረዱ ምድረ በመዋዕል ዘቀዳሚ» በአማርኛ «ሥጋዊ ምኞትን የማሸነፍ ዕድል ለማን ተሰጠው? ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ለመላእክት እንኳን አልተቻላቸውም፤ በቀደመው ዘመን ያልተሰጣቸውን ሽተው በፈጸሙት በደል ከሰማይ ወደ ምድር ወርደዋልና።» (መቅድመ ተአምረ ማርያም)

ደናግላንና አለባበሳቸው!

ለዐቅመ ሔዋን የደረሱና ያልደረሱ፣ ደናግላን የሆኑና ያልሆኑ ሴቶች ተለይተው የሚታወቁበት የፀጉር አሠራር፣ አለጫጨትና የአለባበስ ሁኔታ በየሀገሩ ይገኛል:: በድሮ ጊዜ ደናግለ እስራኤል ለፍሬ -እልደረስንም ሲሉ ወርቅ እንደ አበባ የፈነዳበት ነጭ ሐር ለብሰው ይታዩ ነበር።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ አለባበስ በሚገባ ካስተማረ በኋላ ትምህርቱ ደናግልንን ብቻ የሚመለከት ለመሰላቸው ሰዎች ‹ወአኮ ዘእቤ በእንተ ደናግል ባሕቲቶን› ማለትም «ይህን ያልኩት ስለ ደናግል ብቻ አይደለም» በማለት ደናግላን ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ሴቶች በሚገባ መንገድ ብቻ ማጌጥ እንዳለባቸው ይገልጻል:: ተግ.ዮሐ28

አለባበስ በዝሙት ለመውደቅ የሚዳርግበት ሁኔታ ሰፊ ስለሆነ በይበለጥ ደናግል አለባበሳቸው ተገቢ መሆን አለበት፡፡ ደናግላን የተለየ አለባበስ እንደ ነበራቸው መጽሐፍ ቅዱስም ይመሰክራል፡፡ ትዕማር ድንግል በነበረችበት ጊዜ ‹‹ብዙ ኅብር ያለውን ልብስ ለብሳ ነበር እንዲህ ያለውን ልብስ የንገሡ ልጆች ደናግሉ ይለብሱት ነበርና።» ነገር ግን በተደፈረችና ክብሯን ባጣች ጊዜ «ብዙ ኅብር ያለውን ልብስዋን ተርትሪ› እየጮኸች ሄደች:: 2ሳሙ13÷18-19

ድንጋሌ ሥጋ አንድ ጊዜ ጠፋ በኋላ ሊመለስ ይችላል?

በግዘፍ ያለ ድንጋሌ ሥጋ አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህ ድንጋሌ ሥጋ. በሩካቤም ሆነ ያለ ሩካቤም የሚጠፋበት ጊዜ አለ፡፡ ድንጋሌ ሥጋን የሚያጠፋው ሩካቤ በመንፈሳዊው ሕግ የተደገፈ ሕጋዊ ሩካቤ ወይም ሕገ ወጥ ሩካቤ ሊሆን ይችላል:: በአጠቃላይ ድንጋሌ ሥጋ በልዩ ልዩ መንገድ ሊማስን ይችላል:: አንድ ጊዜ ጨርሶ የጠፋ ዓይን እግዚአብሔር ከሃሊነቱን ለማሳየት ሲፈቅድ ብቻ ካልሆነ በቀር ለበራ እንደማይችል ድንጋሌ ሥጋም አንድ ጊዜ ከተገሠሠ እንዲሁ ነውና አይመለስም፡፡ ድንጋሌ ሥጋ ዓይን መባሉን ከዚህ በላይ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ‹ከመ ብንተ ዓይን» ያለውን በመጥቀስ ተመልክተናል፡፡

ከላይ እንደ ተገለጸው በንስሐ ተመልሶ የሚገኘው የነፍስ ድንግልና እንጂ የሥጋ ድንግልና አይደለም፡፡ መጽሐፈ መነኮሳት «ንስሐሰ ትሬስዮ ለዘአበሰ ከመ ዘኢአበሰ ለዘማዊ ድንግለ›› ፡ «ንስሐ ግን የበደለን እንዳልበደለ ዘማዊን እንደ ድንግል ታድርገዋለች::> በማለት የተናገረው ስለ ነፍስ ድንግልና እንጂ ስለ ድንጋለ ሥጋ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ድንጋሌ ሥጋውን አንድ ጊዜ ካጣ በኋላ እንደ ገና በንስሐ ያገኘዋል ለማለትም አይደለም:: በተጨማሪም «እንደ ድንግል» ታደርገዋለች ይላል እንጂ ቁርጥ በሆነ ቃል «ድንግል ታደርገዋለች» አለማለቱን ልብ ማለት ያስፈልጋል:: ስለዚህ ስለ ድንጋሌ ሥጋ በመጀመሪያ መጠንቀቅ እንጂ ከሄደ በኋላ «ድንግል ብሆንስ?›› ማለት አጉል ተስፋ ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ግን የእግዚአሔርን ከሃሊነት መጠራጠር ሳይሆን ያለ አግባብ ተስፋ ማድረ ግን ለመንቀፍ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

የንጽሕና መርከባችን እንዳይሰበር መጠንቀቅ ያሻል:: «ብርሌ ከነቃ አይሆንም ዕቃ» እንደ ተባለው ድንጋሌ ሥጋም አንድ ጊዜ ከተወሰደ እንደ ተሰበረ የሸክላ ዕቃና እንደ ሞተ ሰው ነው:: እነዚህ ተመልሰው ይረባሉ፣ ይጠቅማሉ እንደማይባሉ ድንጋሌ ሥጋም እንዲሁ ነውና ይመለሳል አይባልም:: መዝ30፥12

የኃጢአት መጥፎነቷ ይታወቅ ዘንድ ኃጢአት ከሠራን በኋላ ቢያንስ በአንድ ነገር እንቀጣለን:: ወይም አንድ ነገር እናጣለን፡፡ ዝሙት ምክንያት ድንጋሌ ሥጋ አንዴ ከተወገደ በኋላ የማይመለስበትም አንዱ ምክንያት ይህ ነው:: ንጉሥ ዳዊት ባመነዘረ ጊዜ ምንም እንኳን ንስሐ ቢገባ በዝሙት የጸነሰው ልጁ ሊፈወስለት አለመቻሉ ኃጢአት ቢያንስ በአንድ ጐዳና ሳትጐዳ እንደ ማትቀር ያመለከታል:: 2ሳሙ12፥13-14

አንዳንድ ነገሮች አንድ ጊዜ ካመለጡ በኋላ በንስሐ እንኳን መልሶ ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ መኖሩን ማወቅ ያስፈልጋል:: ለምሳሌ:- ዔሳው ብኩርናውን ባቃለላት ጊዜ ከሱ ወደ ታናሽ ወንድሙ ወደ ያዕቆብ ተዛውራለች:: በኋላ ግን ምንም ክልብ ቢፈልጋት መልሶ ለማግኘት አለመቻሉን ቅዱስ ጳውሎስ ሲገለጽ እንዲህ ብሏል ዕብ12÷16-17 ድንግልናም አንድ ጊዜ ከተወገደ እንደ ፈሰስ ውኃ ነው።

የኃጢአት ቁስል በንስሐ መድኃኒት መፈወስ ቢችልም ትራት (ጠባሳ) ሳይተው ግን አይቀርም:: ስለዚህ እድናለሁ ብሎ በእሳት መጠበስ እንደማይገባ ንስሐ አለ ብሎም መበደል አይገባም፡፡ ኃጢአት የሚጥለው ጠባሳ ባይኖር ኖሮ ምንም ያልበደለና በድሎ በንስሐ የተመለሰ ሰው ልዩነት ባልኖራቸውም ነበር። በዝሙት የተሰነካከለ ሰው በንስሐ አማካይነት ምንም ካልተሰነካከለው ሰው ጋር በድንጋሌ ነፍስ መተካከል ቢችልም በድንጋሌ ሥጋ መበለጡ አይቀርም፡፡ ተሰብሮ በተጠገነና ምንም ባልተሰበረ ሰው መኻል ያለው ልዩነት ይህ ነውና፡፡

በንስሐ ከተመለስኩ ወዲህ እግዚአብሔር ድንጋሌ ሥጋዬን ቢመልስልኝ ምን አለበት? ማለት ተገቢ ሐሳብ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ እግዚአብሔርን መፈታተን ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ለዚያ ነገር ሳይበቁ በጎን ነገር ከመመኘት አልፎ ይገባኛል ማለት የትዕቢት ሐሳብ ነው፡፡ ሌላው ይህን ሐሳብ የተለየ የሚያደርገው ደግሞ መጀመሪያ የተሰጠንን ከጣልን በኋላ መመኘታችን ነው፡፡ ራስ አጥፊ ረስ ተቆጭ መሆን አይሆንም? እንደ ሥራዬ ድንጋሌ ሥጋን ብቻ ሳይሆን ሌላም ማጣት ይገባኝ ነበር የሚል ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ እንዴት የተወደደ ነው? በአንጻሩ ደግሞ «የኔ ውድቀት እንሌላው ሰው አልነበረም!» በማለት


እንደ ድንግልና ሁሉ በጋብቻም “አታመንዝር» የሚለው ሕግ ይጠበቃል እንጂ አይፈርስም። ስለዚህ እስከ ጋብቻ በንጽሕና ተጠብቆ ከሚኖርበት የድንግልና ሕግ ወደ ጥንድነት የሚተላለፉበት ጋብቻም ሕግ›› ይባላል፡፡ ብዙ መንፈሳዊ መጻሕፍት ባለትዳር ወይም ያገባ ለማለት «ሕጋዊ» የሚሉት በዚህ ምክንያት ነው::

ሐ. ድንጋሌ ሥጋ ዓይን ይባላል ወይም በ«ዓይን›› ይመስላል:: ለዚህም ምስክሩ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ «መሀሮሙ ለደናግል ለእለ እያውሰቡ ከመ ይዕቀቡ ድንግልናሆሙ ከመ ብንተ ዓይን›› በማለት የተናገረው ቃል ነው:: ይህም ወደ አማርኛ ሲተረጎም

«ድንግልናቸውን እንደ ዓይን ብሌን ይጠብቁ ዘንድ ላላገቡ ደናግል ምክራቸው፣ አስተምራቸው፡፡>>ማለት ነው:: ድንግልና ለምን «ዓይን› እንደ ተባለ የሚያውቅ ማን ነው? ድንግልና የአንድን ሰው ማንነት እስከ መወሰን ወይም ገልጦ እስከ ማሳየት የሚደርስ መሠረታዊ ምሥጢር እንድትይዝ ሆና በመፈጠሯ አይደለምን? ዓይን ታያለች እርሷም ትታያለች፡፡ አንቺ ሴት ከጋብቻሽ በፊት ድንግልናሽን ያጠፋሽው ከሆነ ስታገቢ ባልሽን በምን ታይዋለሽ? ድንግልና «ዓይን› ተብላለችና፡፡ ባልም ቢሆን ድንግልናውን ጠብቆ ካልኖረ ረቂቅ መነጽር (ድንግልና) የለውምና ሚስቱን በምኑ ያያታል ? ዛሬ ዛሬ ብዙ ባልና ሚስቶች በጥቃቅን አለመግባባቶች ለአንድ ቀን እንኳን ተያይተው የማያውቁ ያህል የሚሆኑትና የሚኳረፉት ምናልባት ድንግልናን መጠበቅ ስለ ቀረ ይሆን? በማለት መጠየቅ አስተዋይነት ነው፡፡ ምክንያቱም ድንግልና ባልና ሚስት በተለየ መልኩ የሚተያዩበት የማይመረመር «ዓይን»ነውና፡፡

ድንግልና ሁሉን አርቆ የሚያሳይ ከፍተኛ ቦታ ነው:: የኑሮ ደረጃቸውን በድንግልና ሆነው መርምረውና ተመልክተው ያገቡ ሰዎች አይጸጸቱም: ማለትም አንድ ስው ደረጃው ማግባትም ይሁን መመንኮስ በሚገባ ለይቶ ማወቅ የሚችለው ንጽሕናውን ጠብቆ ለመኖር ከቻለ ብቻ ነው:: ድንግልና የንጽሕናን ቅባት የተኳለ አጥርቶ የሚመለከት የሰውነት መብራት ነውና፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ «የሰውነት መብራት ዓይን ናት፡፡ እንግዲህ ዓይንህ ጤናማ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፡፡ ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ : ሁሉ የጨለመ ይሆናል» ይላል:: ማቴ6፡22-23 እንደዚሁም ሁሉ በዓይን የተመሰለች ድንግልናም በሕገ ወጥነት በዝሙት ሥሪ ከጠፋች አንድ ሰው ሰውነቱ ሁሉ እንደጨለመበት ለያምን ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ድንግልና ሃይማኖትና ምግባር መሠረታቸውን ለቀው እንዳይናጉ የሚያደርግ ጽኑ መሠረት ነውና፡፡ ማለትም አመለካከት፣ አነጋገርና አሠራር ሚዛናቸውን እንዳልሳቱ ከድንግልና አጠባበቅ አንጻር መናገር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ድንግልና «ዓይን› ቢባል ያንሰዋል እንጂ አይበዛበትም፡፡

ብዙ ጊዜ ደንግልና ለሴቶች የሚነገረው በጉልህ ምልክት የሚታወቀው በእነርሱ ስለሆነ ነው:: ነገር ግን ድንግልና ለወንዶችም ተጠቃሽ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ «ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፣ ድንግሎች ናቸው::» በማለት ከትቦ ይዟል:: ራእይ14፥4 በመሆኑም ድንግልናን የመጠበቅ ጥቅምም ሆነ ያለ መጠበቅ ጉዳት በማስተዋል ለተመለከተው በወንድም ሆነ በሴት በኩል ያለው ፋይዳ ተመጣጣኝ ነው:: ስለዚህ በዚህ ርእስ ሥር በጎላው ለመናገር ሴቶች ይጠቀሱ እንጂ ልዩ ማመልክቻ እስክ ሌለ ድረስ የሚወሳው ሁሉ ወንዶችንም ያጠቃልላል፡፡

የድንግልና ዓይነቶች

ድንግልናን በሁለት ወገን ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ በሁለት ወገን ድንግል መሆኗን ለመግለጽ ስለ እመቤታችን ስለ ድንግል ማርያም ‹‹ድንግል በክልኤ» ተብሎ የተነገረው ቃል ለእክፋፈሉ በዋቢነት ይጠቀሳል::

የመጀመሪያው የድንግልና ዓይነት ድንጋሌ ሥጋ ሲሆን ሁለተኛው ዓይነት ደግሞ ድንጋሌ ነፍስ ነው፡፡ ድንጋሌ ነፍስ በሌላ መንገድ ድንጋሌ ሕሊና ይባላል። «ድንግል በሕሊናኪ ወድንግል በሥጋኪ» * «በሐሳብሽ ድንግል ነሽ በሥጋሽም ድንግል ነሽ› እንዲል፡፡ (ጸሎተ በሰላመ ገብርኤል መልአክ)

ድንጋሌ ሥጋ ለድንጋሌ ነፍስ መገለጫ፣ ጥላ ወይም አምሳል ነው:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ «እስመ ድንጋሌ ሥጋስ አርአያ ወጽላሎት ለእንታክቲ» ብሏልና፡፡ በእውነት «ድንግልና» የምትባለው ግን ድንጋሌ ነፍስ ናት፡፡ ለዚህም ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ «ወባሕቱ ድንግልናስ አማናዊት ድንጋሌ ነፍስ ይእቲ» በማለት አስረጅ የሚሆን ቃል ተናግሯል፡፡ «ነገር ግን አማናዊት ድንግልና የምትባለው ድንጋሌ ነፍስ ናት» ማለት ነው:: ዮሐ.ተግ28 ከላይ እንደ ተጠቀሰው ድንጋሌ ሥጋ በግዘፍ የሚታይ በገሢሥ የሚታወቅ ሲሆን ድንግሌ ነፍስ ግን ረቂቅ ነው፡፡

ነፍስ ግን ድንግልናዋ በብዙ ጐዳና ነው፡፡ ከቅጥነተ ድንግልናዋ (ከድንግልናዋ ረቂቅነት የተነሣሣ) አንድ ጊዜ በኃጢአት ተግባርና ሐሳብ የተወሰደባት ድንግልና በንስሐ ይመለስላታል:: ስለዚህ ድንጋሌ ነፍስ በኃጢአት ይወገዳል በንስሐ ደግሞ ይመለሳል ማለት ነው፡፡

የነፍስን ድንግልና የሚያጠፋው የኃጢአት ሥራና ሐሳብ ብቻ ነው:: ኃጢአት ካልሆነ በቀር የሥጋን ድንግልና እስክ ማጥፋት የደረሰ ጽኑ ተግባር እንኳን ቢሆን የነፍስን ድንግልና ሊያጠፋ አይችልም፡፡ ለምሳሌ፦ በቅዱስ ጋብቻ የተወሰኑ ባልና ሚስት በሚፈጽሙት ሩካቤ. ድንጋሌ ሥጋቸው ሲጠፋ የነፍስ ድንግልናቸው ግን አይወገድም። ምክንያቱም ሕጋዊ ባለትዳሮች ሩካቢያቸው ኃጢአት ባለመሆኑ ነው:: ይህን ሲያስረዳ ቅዱስ ዮሐንስ እፈ ወርቅ እንዲህ ብሏል:- «ወሶበኒ ባቲ ምት ድንግልት ይእቲ ተደንግሎ መንክረ» ይህም ማለት ባልም ብታገባ ድንቅ በሚሆን ድንጋሌ ነፍስ ድንግል ናት ማለት ነው፡፡ ዮሐ.ተግ.28
በተጨማሪም ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ በሌላ አገባብ ብንመለከተው ይኽን ሐቅ እንረዳለን፡፡ ክህነትን አጽንቶ ዲያቆን ሆኖ ለመኖር ድንግልናን መጠበቅ ግድ መሆኑ ለማንም የተሠወረ አይደለም፡፡ ስለዚህ አንድ ዲያቆን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ድንጋሌ ሥጋውን ሲያፈርስ ክህነቱን እያፈረሰ መሆኑ ግልጽ ነው:: ነገር ግን በተገቢ መንገድ ጋብቻ ፈጽሞ ሩካቤ በማድረጉ ምክንያት ድንጋሌ ሥጋውን ሲያጣ ክህነቱን ግን አያጣም:: ምክንያቱም ሕጋዊ ሩካቤ የነፍስን ድንግልና ስለማያጠፋና ስለማያረክስ ነው፡፡

ድንጋሌ ነፍስ የሌለው ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም:: ይህም ማለት የነፍስን ድንግልና የሚያጠፋው ኃጢአት ብቻ በመሆኑ ኃጢአቱን በንስሐ ያላራቀ ወይም ንስሐ ያልገባ ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም ማለት ነው፡፡ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራእይ መጽሐፉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት የሚችሉት የነፍስ ድንግልና ያላቸው ብቻ መሆናቸውን ሲገልጽ:- «ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው ድንግሎች ናቸውና፡፡ በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉ እነዚህ ናቸው፡፡ ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኩራት እንዲሆኑ ክሰዎች የተዋጁ አነዚህ ናቸው::› ይላል፡፡ ራእይ14፥4

በተጨማሪም ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ድንጋሌ ነፍስ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ዋና ነገር መሆኑን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ «እስመ ድንጋሌ ነፍስ ይሬሲ ሱታፌ ምስለ ክርስቶስ ወያበውእ ውስተ መንግሥተ ሰማያት» ይህም በአማርኛ «ድንጋሌ ነፍስ ከመርዓዊ (ከሙሽራ) ክርስቶስ ጋራ አንድ ያደርጋል:: ወደ መንግሥተ ሰማያትም ያገባልና» ማለት ነው:: ዮሐ.ተግ.2

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox


ምዕራፍ ስምንት

ድንግልና ምንድር ነው?

ድንግል የሚለው ቃል «ተደንገለ፤ ተጠበቀ» ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ «መጠበቅ» ማለት ነው፡፡ እንደ አገባቡም ፍቺው ሊለያይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ:- ድንግል የሚለውን ቃል ለዕቃ የሰጠን እንደ ሆነ ገና ከማምረቻ የወጣ፣ ምንም ያልተሠራበት፣ ያላደፈ ያልጎደፈ፣ ያላረጀ ያላፈጀ፣ ያልተቀላቀለ ማለት ይሆናል፡፡ ድንግል መሬት ሲባል ደግሞ ለምነቱ እንደ ተጠበቀ ያለ፣ ለእርሻ ያልዋለ ወይም ያልታረሰ፣ ያልተቆፈረ፣ ዘር ያላረፈበት እንደ ተፈጠረ ያለ መሬት ማለት ነው፡፡

ድንግል የሚለው ቃል ለሰው ሲነገር ደግሞ ወንድ የማታውቅ (ከወንድ ጋር ሩከቤ ፈጽማ የማታወቅ)፣ ጥብቅ፣ ልጃገረድ ሴት ወይም ሴትን በምንጣፍ ተገናኝቶ የማያውቅ ወንድ ማለት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የተፈጥሮ ንጽሕናቸውን የጠበቁ ንጽሐ ጠባይ ያላደፈባቸው ወንድና ሴት ማለት ነው:: ዘፍ24፥16፣ ራእይ14፥4

ብዙ ጊዜ ይህ ቃል ሲፈታና በዐረፍተ ነገርም ሲገባ የምንመለከተው የመጨረሻውን አስተያየት በመያዝ ወንዶችና ሴቶች የሰው ልጆችን ወክሎ ነው፡፡ ስለዚህ ከላይ በተሰጠው ትንታኔ መሠረት ድንግልና ንዑስ ሕዋስን ወይም አካልን ብቻ ሳይሆን አንድ ድርጊት መፈጸም አለመፈጸሙን የሚያመለክት ቃል ይሆናል ማለት ነው፡፡
በተጨማሪም ይህ ቃል ለመንግሥታት፣ ለሕዝብ፣ ለሀገር፣ ለምእመናን ምሳሌ በመሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ ኢሳ 23÷12 ፣37÷22፣47÷1፣አሞ 5÷2፣ኤር 18÷13፣2ኛ ቆሮ 11÷2

ድንግልናና ማኅተመ ድንግልና

በሰው ልጆች ዘንድ ሩካቤ ካለ ዘር መቀበል፣ ማቀበልና ሰስሎተ ድንግልና (የድንግልና መወገድ) መኖሩ የታወቀ ነው:: ሆኖም ይኽ ስለ ታወቀ ብቻ ሩካቤ ከተፈጸመ ማኅተመ ድንግልና አይኖርም ድንጋሌ ሥጋ ካለ ደግሞ ሩካቤ አልተፈጸመም በማለት ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሩካቤ አድርገው ድንጋሌ ሥጋቸው ያልተወገደ እንደውም ማኅተመ ድንግልናቸው ሳይገሠሥ እስከ መፅነስ የደረሱ ብዙ ሴቶች ስላሉ ለዚህ ምስክር ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ተፈጥሮአዊ ጽንዐ ድንግልናቸው በሩካቤ ብቻ ሊገሠሥ የማይቻል እየሆነ በቀዶ ጥገና ሕክምና ማኅተመ ድንግልናቸው እንዲወገድ የሚደረግላቸው ብዙ ሴቶች አሉ፡፡

ይህ ከሆነ ድንግል የሚለው ቃል ብቻውን የአንዲት ሴትን ትክክለኛ ድንግልነት ላይገልጽ ይችላል ማለት ነው፡፡ የሚገልጽ ቢሆን ኖሮ ያለ ምንም ተጨማሪ ቃላት ለእመቤታችን በተነገረ ነበር፡፡ ነገር ግን ስለ እመቤታችን አምላክን መፅነስና መውለድ ሲነገር በድንግልና ፀንሳ ወለደችው ከማለት በተጨማሪ «ያለ ሩካቤ፣ ያለ ዘር፣ ያለ ሰስሎተ ድንግልና›› ፀንሳ ወለደችው ማለት በብዙ መጻሕፍት የተለመደ አገላለጽ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- «ወይእቲ ንጽሕት እምነ ሠለስቱ ግብራት ዘውእቶሙ ዘርዕ፣ ወሩካቤ፣ ወስስሎተ ድንግልና እለ ሥሩዓን በዕጓለ እመ ሕያው ወእሙራን ቦሙ» - «እርሷም በሰው ልጆች ዘንድ ከታወቁት ከሦስቱ ግብራት የተጠበቀች ናት እነርሱም ሩካቤ ዘር መቀበልና፣ የድንግልና መወገድ ናቸው፡፡» ይላል፡፡ (ትርጓሜ ውዳሴ ማርያም) ስለዚህ ሩካቤና ሰስሎተ ድንግልና የተለያዩና ራሳቸውን የቻሉ ተግባራት ተደርገው መታየት አለባቸው። አንዲትን ሴት ማኅተመ ድንግልና ስላላት ብቻ «ሩካቤ አድርጋ አታውቅም» ወይም ሩካቤ ስላደረገች «ማኅተመ ድንግልና ሊኖራት አይችልም» ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ አለመቻሉን እንረዳለን፡፡ እመቤታችን ግን «ድንግል» የሚለው ቃል ከሚገልጸው በላይ «ፍጽምት» መሆኗን ተያይዘው በተጠቀሱት ተጨማሪ ቃላት እንረዳለን፡፡ ድንግል ማርያም በሕሊናዋም በሥጋዋም ፍጹም ድንግል የሆነች «ምክሐ ደናግል>> ናት፡፡

ማኅተመ ድንግልና በሩካቤ ሥጋ ጊዜ የሚጠፋ እንደ መሆኑ መጠን በቀጥታ በሥጋ ድንግል ከመሆንና ካለመሆን ጋር መዛመዱ ግልጽ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግን ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ ማኅተመ ድንግልናን «ከድንግልነት» ጋር ለይተን ለመመልከት የምንገደድበት ሁናቴ ይኖራል፡፡

ለምሳሌ ወንዶች እንደ ሴቶች ተጨባጭና ጉልህ የድንግልና ምልክት ስለሌላቸው ከሴት ጋር ሩካቤ ፈጽመው የማያውቁ ሆነው ሳለ ደናግል አይደሉም ለማለት አይቻልም:: እንደዚሁም ሁሉ ሩካቤን ፈጽመው የማያውቁ ሴቶች ሲወለዱ ጀምሮ ማኅተመ ድንግልና የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ:: ወይም ከጊዜ በኋላ በክባድ የአካል እንቅስቃሴ፣ በአደጋ፣ በሕክምና ወይም በዕድሜ ብዛት ምክንያት ማኀተመ ድንግልና ሊፈርስባቸው ይችላል:: እንዲህ ያሉ ሴቶች ማኅተመ ድንግልናቸውን ቢያጡም ሩካቤ ፈጽመው እስካላወቁ ድረስ ደናግል መባላቸው የተጠበቀ ነው:: ምክንያቱም ድንግልናና ማኅተመ ድንግልና በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተለያይተው ስለሚታዩ ነው::

በሌላ አቅጣጫ ስንመለከት ወንዶች ሩካቤ ፈጽመው ሳለ እንደ ሴቶች የሚገሠሥ ማኅተመ ድንግልና ስለሌላቸው ድንግልናቸው አልፈረሰም እንደማይባል ሁሉ ሴቶች ሩካቤ ሥጋ እየፈጸሙ በልዩ ልዩ ምክንያት ማኅተመ ድንግልናቸው ባይገሠሥም መደበኛ ሩካቤ እስከ ፈጸሙ ድረስ ደናግል ሊባሉ አይችሉም:: ለምሳሌ:- የሚያይ የሚመስል ዓይን እያላቸው በመፍዘዙ ምክንያት የማያዩ ሰዎች የዓይን ምልክታቸው (ዓይን የሚባው ሕዋስ ወይም መልክ) ጨርሶ ስላልጠፋ ብቻ ዓይን አላቸው ይባላልን? እንደዚሁም ሁሉ ሩካቤ ፈጽመው ሳለ ማኀተመ ድንግልናቸው ባለመጥፋቱ ብቻ ደናግል ሊባሉ አይቻልም፡፡

አንዲትን ሴት ድንግል የሚያሰኛት ሥራዋና ዝንባሌዋ ብቻ ነው:: ማኅተመ ድንግልናዋ ስላልተወገደ ብቻ ወይም እርሷ ድንግል መሆን ስለምትፈልግ ወይም «ጳጳስ››ም ሆነ «ባሕታዊ» ጸሎት ስለ ደገመላት ድንግል መሆን አትችልም:: ከዚህ በታች የተጠቀሰው ኃይለ ቃል ይህንን ሐሳብ የሚያጎላ ነው፡፡ ‹‹ወኢያንብር ዕደ ላዕለ ድንግል አላ ምሥጢራ ባሕቲታ ትሬስያ ድንግለ›› የዚህ ዐረፍተ ነገር ትርጓሜ ‹‹ድንግል ናት ብሎ በአንብሮተ ዕድ አይሹማት (ድንግልና) ሾሜሻለው አይበላት:: ፈቃዷ ብቻ ድንግል ያደርጋታል እንጂ የሰው ፈቃድ ድንግል አያደርጋትምና፡፡» የሚል ነው፡፡ (ፍትሐ ነገሥት መንፈሳዊ)

የማኅተመ ድንግልና ስያሜዎች

ማኅተመ ድንግልና ሴት ከወንድ ጋር ሩካቤ አድርጋ አለማወቋን የሚያስረዳ የሥራዋ መገለጫ የእኗኗሯ መታወቂያ ልዩ የተፈጥሮ ምልክትና የድንግልናዊ ኑሮዋ ዘውድ ነው:: ይህ መለኮታዊ ማኅተም በሴቶች አፈ ማኅፀን ቀለበት በሚመስል ስስ ሥጋነት በጉልህ ይታወቃል፡፡ ድንግልና ጥቅሙን፣ ምሥጢሩን፤ ምሳሌውን የሚያመለክቱ ልዩ ልዩ ስያሜዎች አሉት:: በተለያዩ ቅዱሳት መጻሕፍት የተጠቀሱት እነዚህ የድንግልና መጠሪያዎች በርካታ ቢሆኑም ሦስት ያህሉ ብቻ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል::

ሀ. ማኅተመ ድንግልና «ክንፈ ድንግልና» ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ዓለም ያለ ስጋት ለመንቀሳቀስ የሚያስችል የንጽሕና ክንፍ ነውና፡፡ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ «ኦ ወለተ እስራኤል መኑ ቀረጸ አክናፈ ድንግልናኪ› በማለት የተናገረው ቃለ መጠይቅ ከላይ መኅተመ ድንግልና ‹ክንፈ ድንግልና (የድንግልና ክንፍ)» ይባላል በሚል ለተገለጸው ሐሳብ ብቁ ማስረጃ ይሆናል፡፡ ከዚህ ዐረፍተ ነገር እንጻር ለተመለከተው ድንግልናቸውን ያልጠበቁ ሰዎች በሙሉ ክንፍ የሌላትን ወፍ ይመስላሉ::

ለ. «ሕጓን ወሰደው› እንዲሉ ድንግልና ‹‹ሕግ›› ይባላል:: ሕግ የተባለበት ምክንያት «አታመንዝር» የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ መፈጸምና - አለመፈጸምን የሚያስታውቅ የሕግ ምልክት በመሆኑ ነው፡፡


ይፍቱኝ አባቴ

የዓለም ወንጀለኛ በደለኛ ነኝ
ይፍቱኝ መምህሬ ይፍቱኝ ይባርኩኝ
ይፍቱኝ አባቴ ይፍቱኝ ይባርኩኝ

እናንተ ደካሞች ሸክም የከበዳችሁ
ኑ ብሎናልና እንዳሳርፋችሁ(፪)
አምላኬ ይቅር ባይ መሆኑን አውቃለሁ
አበስኩ ገበርኩ ብዬ ቀርቤአለሁ(፪)
አዝ---
ጴጥሮስ አስተምሯል ስለ ንስሐማ
ዮሐንስም ሰብኳል ስለ ንስሐማ
ልብ ያለው ልብ ያድርግ ጆሮ ያለው ይስማ(፪)
ያለፈው ጥፋቴ በደሌ እንዲፋቅ
አምላኬን በእንባ ይቅርታ ልጠይቅ(፪)
አዝ---
ስለ በደሌማ ስለኃጢአቴ
ንስሐዬን ይስጡኝ የንስሐ አባቴ(፪)
የማሰር የመፍታት ሥልጣን በሰጠዎ
ከኃጢአት ማሰሪያ ይፍቱኝ በአምላክዎ(፪)
አዝ---
በምድር ያሰሩት ታስሯል በሰማይ
በምድር የፈቱት ተፈትቷል በሰማይ(፪)
አዝ---

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox


#ምሥጢረ ንስሓ

ንስሓ ሰውና እግዚአብሔር የሚታረቁበት፣ የእግዚአብሔር ምሕረት፣ ይቅርታና ሰላም የሚገኝበት፣ ስርየተ ኃጢአት፣ ጸጋና በረከትን የምናገኝበት ምሥጢር ነው። ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንም አንዱ ነው። አፈጻጸሙም መናዘዝ በሚችል ሥልጣነ ክህነት ባለው ካህን አማካኝነት ተነሳሒው የበደለውን በደል ተጸጽቶ በመናዘዝ ላጠፋው ጥፋት ተገቢውን ቀኖና የሚቀበልበት ነው። ንስሓ የሰው ልጆች ከአማናዊው ድኅነት ተካፋይ እንዲሆኑ እግዚአብሔር ያዘጋጀልን የጽድቅ በር ነው። ራስን ወቅሶ፣ ስሕተትን አምኖ፣ ዳግም ላለመፈጸም ወስኖ እና ተናዝዞ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው።
“ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ ትጠፋላችሁ” (ሉቃ.13፣3) ተብሎ የተነገረው ንስሓ ከጥፋት ለመዳን ዋናው መንገድ መሆኑን የሚያመለክት ነው። “ንስሓ ግቡ፤ ኃጢአታችሁ ይሰረይላችሁ ዘንድ” (ሐዋ.2፣28) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ያስተማረው የሚያስገነዝበን ይህን ነው። ከኃጢአት ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃችንም ሊያድነን የታመነ ነው” (1ኛዮሐ.1፣8) የተባለው ንስሓ ከአምላካችን የምንታረቅበት በመሆኑ ነው።
በንስሓ ጊዜ መሥዋዕትነትና መንፈሳዊ ትግል ያስፈልጋል። “ከኃጢአት እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ አልተቃወማችሁም (ዕብ.12፣4) እንዲል። ንስሓ እየገቡ ከሰይጣንና ከፈቃደ ሥጋ ጋር ታግሎ ለማሸነፍ መወሰን አማናዊውን ሰላም ያስገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ቦታዎችና በተወሰኑ ግለሰቦች ሲፈጸም የሚታየው ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ተቃራኒ ተግባር ነው። ሰውን የሚያዘናጋ፣ መንፈሳዊ ተጋድሎን ዋጋ የሚያሳጣ ነው። ተነሳሕያን ይህን ተረድተው ሥርዓተ ቤተክርስቲያን የሚያዝዘውን መፈጸም ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ከጸጋ እግዚአብሔር ያርቃልና። ንስሓ ምሥጢር መሆኑንም እንድንዘነጋ ያደርገናልና። ምሥጢረ ንስሓ በአንድ ካህንና በአንድ ተነሳሒ ምእመን አማካኝነት የሚፈጸም ምሥጢር ነው።
በንስሓና በምሥጢረ ንስሓ መካከል መጠነኛ ልዩነት አለ። ንስሓ የምንለው ከመጸጸት ጀምሮ ለካህኑ እስከ መናዘዝ ያለውን ሒደት ነው። ምሥጢረ ንስሓ የምንለው ግን በካህኑ የሚታይ አገልግሎት ቀኖና በመስጠት፣ በመናዘዝ፣ በመምከር፣ ንስሓውን በአግባቡ ሲፈጽም ሥጋ ደሙን እንዲቀበል በማድረግ፣ የመንጻቱ ማረጋገጫ የሚሆነውን ጸሎተ ፍትሐት በማድረስ፣ ማየ ምንዝህ በመርጨት የሚገለጥ ነው። የተነሳሒው ኃጢአት ሲሰረይ በዓይን አይታይም። ምሥጢር ከሚያሰኘው ጉዳይ አንዱም ይህ ነው። ንስሓ ከሚደገሙ ምሥጢራት አንዱ መሆኑም ሰዎች ኃጢአት መሥራት ስለሚደጋግሙ ደጋግመው ንስሓ በመግባት የድኅነት ተካፋይ እንዲሆኑ ነው።
ይህን ታላቅ ምሥጢር አንዳንድ “አጥማቂ ነን ባዮች” በዓመት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ በቀጠሮ ሲያከናውኑ ይታያል። ድርጊቱ ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ውጭ ነው። ለንስሓም ቀጠሮ አይሰጥም።መቼ
እንደምንሞት ስለማናውቅ ተዘጋጅተን መጠበቅ እንጅ ለንስሓ ቀጠሮ ተቀብሎ መቀመጥ አይገባም። ዕለት ዕለት የሠራነውን ኃጢአት ለንስሓ አባታችን በመናዘዝ ንጹሕ ሆነንና ተዘጋጅተን መጠበቅ ይኖርብናል እንጂ። ንስሓ ክህነት በሌለው ሰው ሊፈጸም የማይገባ ድንቅ ምሥጢር ነው። “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ራስህን ለካህን አሳይ” (ማቴ.8፣2) ተብሎ የተነገረውም ለዚህ ነው። በዚህ ዓይነት መንገድ ሲፈጸም የኖረውን ምሥጢረ ንስሓ ስመ ክርስትናን በወረቀት ጽፎ በማቃጠል “ኃጢአትህ ተሰረየልህ” እያሉ ማታለል በተነሳሕያኑም፣ በምሥጢሩም መቀለድ ነው። ድኅነትን ገንዘብ ማድረግ ከፈለግን አታላዮች ከሚፈጽሙት ኢ-ክርስቲያናዊ ድርጊት በመጠበቅ ቤተክርስቲያን የሠራችውን ቀኖና መፈጸም ይገባል።
“ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ይሰረይላቸዋል፤ ይቅር ያላላችኋቸው ግን አይሰረይላቸውም” (ዮሐ.20፣23 የተባለው የሚፈጸመው በሥርዓት ነው። አስቀድመን እንደተመለከትነው ስርየተ ኃጢአት የሚገኘው ስምን በወረቀት ጽፎ ሰብስቦ በማቃጠል ሳይሆን ሥልጣነ ክህነት ያላቸው አባቶች በሚሰጡት ቀኖና አማካኝነት ነው። ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ የተለየ የንስሓ አፈጻጸም የለም። ንስሓ ጸጸት ብቻ ሳይሆን መናዘዝም ያስፈልገዋል። በፈጸመው ኃጢአት ንስሓ ገብቶ ቀኖና አልተቀበለም እንጂ መጸጸትማ ይሁዳም ተጸጽቶ ነበር።
ንስሓ ራሱን የቻለ ጥምቀት አለው። ለዚህ ነው ሥልጣነ ክህነት ባለው አባት እንዲፈጸም ቤተክርስቲያን ሥርዓት የሠራችው። “እኔስ ለንስሓ በውሃ አጠምቃችኋለሁ” (ማቴ. 3፣11) የተባለው ሳይፈጸም የክርስትና ስምን በወረቀት ጽፎ በማቃጠል ስርየት እንደሚገኝ ቤተክርስቲያን ስላላስተማረችን የድርጊቱ ፈጻሚዎችም፣ በዚህ መንገድ ንስሓ ለመግባት የሚፈልጉ ተነሳሕያንም መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox


Видео недоступно для предпросмотра
Смотреть в Telegram
"አድኅነነ እግዚኦ"
አድኅነነ እግዚኦ አድኅነነ አምላክነ /፪/
ዘአዳኃንካ ለነነዌ ሀገር በትንብልና ትንብልና ሣህልከ/፪/
           
አድነን ጌታ ሆይ አድነን አምላካችን/፪/    
ያዳንካት ሀገር ነነዌን በይቅርታህ በአምላካዊ ይቅርታህ/፪/

©በማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox




ጾመ ሰብአ ነነዌ
የካቲት ፫-፭/፳፻፲፯
| 3 - 5/2017

‹‹ጾመ ሰብአ ነነዌ፤ የነነዌ ሰዎች ጾም›› የሦስት ቀን ጾም የጾሙት በነነዌ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከተማዋም (ነነዌ) በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ ስትኾን መሥራቿም ናምሩድ ነው (ዘፍ.፲፥፲፩-፲፪)፡፡ ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦር መነሻ የሆነች፤ እጅግ ሰፊና ያማረች፤ የቅጥሯ ርዝመትም ፲፪ ኪሎ ሜትር የሚሸፈን ነበር፡፡ በከተማዋ ንጉሡ ሰናክሬም ብዙ ሕንጻዎችን ገንብቶ ነበር (ዮናስ ፬፥፲፩)፡፡
በዚያ ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸው በዝቶ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ሲል ዮናስ የስሙ ትርጓሜ ‹ርግብ› የሆነ በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይን ቸርነትና ምሕረቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር መክሮ፣ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሐ እንዲገቡ ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ሕዝብ ላከው (ሉቃ.፲፩፥፴)፡፡ ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፤ አባቱም አማቴ ይባላል፡፡ በዚያን ጊዜ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንዲመልስ ነቢዩ ዮናስ ትንቢትን ተናገረ (፪ኛነገ.፲፬፥፳፭፤ ዮናስ ፩፥፩)፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የሰራጵታዋ መበለት ሕፃን ነቢዩ ዮናስ እንደ ሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል (፩ኛነገ.፲፯፥፲፱)፡፡ መድኃኒታችን ክርስቶስም የዮናስን ከዓሣ ሆድ መውጣት የራሱ ትንሣኤ ምሳሌ አድርጎ ነግሮናል (ማቴ.፲፪፥፲፱-፵፪፤ ሉቃ.፲፩፥፴-፴፪)፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ‹‹ሔደህ በነነዌ ላይ ስበክ›› ባለው ጊዜ ነቢዩ ዮናስ ‹‹አንተ መሐሪ ነህ፤ ልትጠፉ ነው ብዬ ተናግሬ ብትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ›› ብሎ ላለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ፡፡ እግዚአብሔርም ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧ በማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩ ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባሕሩ መጣል ሲጀምሩ ነቢዩ ዮናስ ጥፋቱን ተገንዝቦ ‹‹ማዕበሉ በእኔ ምክንያት የመጣ ስለሆነ ንብረታችሁን ሳይሆን እኔን ወደ ባሕር ጣሉኝ›› ብሎ ተማጸናቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ፣ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳይደረግብን አይሆንም›› አሉ፡፡ ወደ ባሕሩ ለመጣል ዕጣ በተጣጣሉ ጊዜም ዕጣው በዮናስ ላይ ስለ ወጣ ነጋድያኑ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን በአፉ ተቀብሎ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ወደ ነነዌ አደረሰው፡፡ እግዚአብሔር የቅል ተክልን ምሳሌ በማድረግ ቅጠሉ በመድረቁ ዮናስ ባዘነ ጊዜ ‹‹አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለ ሆኑ ያሳዝኑኛል›› በማለት ነቢዩ ዮናስም ውሸታም ላለመባል መኮብለሉ ስሕተት መሆኑን አስረድቶታል፡፡
ዮናስም ነነዌ መሬት ላይ መድረሱን ባወቀ ጊዜ ከእግዚአብሔር መሸሽ አለመቻሉን ተረዳ፤ የነነዌ ሰዎችንም ‹‹ንስሐ ግቡ›› እያለ መስበክ ጀመረ፡፡ የነነዌ ሰዎችም ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ይቅር ብሎ ከጥፋት አድኗቸዋል፡፡ ሐሰት እንዳይባልም እሳቱ እንደ ደመና ሆኖ ከላይ ታይቶአል፡፡ የታላላቁ ዛፍ ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ አድርቆ ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ ንስሐቸው በከንቱ እንዳልቀረ አስረድቷቸዋል (ትንቢተ ዮናስ)፡፡ ታኅሣሥ ፭ ቀን የሚነበበው የመጽሐፈ ስንክሳር ክፍል ‹‹ወበልዐ አሐደ ኀምለ›› በማለት ንስሐ ያልገቡ አንድ አገር ያህል ሰዎች በእሳቱ እንደ ጠፉ ይነግረናል፡፡
ጾመ ነነዌ የሦስት ቀን ሱባኤ ነው፤ በሦስት ቀናት ጾምና ጸሎት ንስሐ የገቡ የነነዌ ሰዎች ከጥፋት እንደ ዳኑ ሁሉ፣ በብሉይ ኪዳን አስቴር ሦስት ቀን ጾማ፣ ጸልያ በእስራኤል ላይ የመጣውን መቅሠፍት እንዲመለስ አድርጋለች (አስ.፬፥፲፭-፲፮)፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከበዓል ስትመለስ ሕፃኑ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ላይ ጠፍቶአት ከሦስት ቀን ፍለጋ በኋላ በቤተ መቅደስ አግኝታዋለች (ሉቃ.፪፥፵፮)፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሄሮድስ በሰጠው ምላሽ መልስ ሦስት ቀን የሱባኤ ፍጻሜ መሆኑን ገልጿል (ሉቃ.፲፫፥፴፪)፡፡
ጾመ ነነዌ የእግዚአብሔርን ቸርነትና መሐሪነት የምናስታውስበት ጾም ነው፡፡ ይኸውም እኛ ፍጡራኑ በበደልን ጊዜ ፈጽሞ ከማጥፋት ይልቅ ምክንያት ፈልጎ እንድንድን ያደርገናል፡፡ ዮናስ ለስብከት ፈቃደኛ ባይሆን እንኳን እግዚአብሔር በተለየ ጥበቡ እንዲሔድ አድርጎታል፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ሌላ የሚልከው ነቢይ አጥቶም አይደለም፤ እርሱንም ጭምር ሊያስተምረው ስለ ፈለገ እንጂ፡፡ የነነዌ ሰዎች የተነሳሕያን ምሳሌ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ሰው ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ከገባ እግዚአብሔር ይቅር ማለቱን አይተውም፡፡ ለዚህም ነው ዮናስን ‹‹አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለ ሆኑ ያሳዝኑኛል›› ያለው፡፡
ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን ይህን እና ሌሎች አጽዋማትን እንድንጾም የወሰኑልን ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሕጉ የተዘጋጀልን እንደ ነነዌ ሰዎች እኛም ጾመን፣ ጸልየን ከኃጢአታችን እንነጻ ዘንድ ነው፡፡ ዛሬ ዓለማችን በኃጢአት ማዕበል እየተናወጠች ባለችበት ወቅት እኛም እንደ ነነዌ ሰዎች ከበደላችን ብንመለስ እና ንስሐ ብንገባ ቸሩ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ይቅርታና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ ስለ ሆነ ‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ይቅር እላችኋለሁ፤›› ይለናል፡፡
ስለሆነም በነቢዩ ዮናስ ላይ የተደረጉ ተአምራትንና ካለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት ቀላል አለመሆኑን በማስተዋል፣ ለነነዌ ሰዎች የወረደውን ምሕረት በመገንዘብ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሃይማኖት አባቶች እና ለወላጆቻችን መታዘዝ ይገባናል፡፡ ስንጾምም እግዚአብሔር አምላካችን መዓቱን በምሕረት፣ ቍጣውን በትዕግሥት መልሶ በኃጢአት ለጠፋው ዓለም ይቅርታውን ይልካል፡፡ በመጾማችን ራሳችን ከመዓትና ከመቅሠፍት ከመዳናችን ባሻገር በእኛ በደል ምክንያት አገራችን፣ ዕፀዋቱና እንስሳቱም ሳይቀር ከድርቅና ከቸነፈር ይተርፋሉና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox



Показано 20 последних публикаций.