#ጾመ_ገሃድ(#ጋድ)
ጥር አስር በዚች ዕለት ምንም ምን መብልን ሳይቀመሱ ምዕመናን ሁሉ እስከ ምሽት ይጾሙ ዘንድ ከእኛ አስቀድመው የነበሩ ታላላቅ ሊቃውንት የቤተ ክርስቲያን መምህራን ሥርዓትን ሠሩ በምሽትም ቢሆን በታላቁ ጾም ከሚበላው በቀር ጥሉላትን እንዳይቀምሱ።
በዚች ዕለት ምዕመናን እስከ ምሽት እንዲጾሙት ያዘዙበት ምክንያቱ ይህ ነው የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕ ወይም በዐርብ ቀን ቢብት በበዓለ ሃምሳ የሚበላውን የጥሉላት መብል በጠዋት በመብላት ምዕመናን ሁሉ በዓሉን እንዲያከብሩ የከበሩ አባቶቻችን ሐዋርያት አዝዘዋል እሊህ ሁለቱ የእግዚአብሔር ታላላቅ በዓሎቹ ናቸውና።
እኛ በዚህ በኃላፊው ዓለም ተድላ ደስታ ደስ የሚለን ለሌሎች እንዳይመስላቸው እንደ አይሁድና እንደ አረማውያን በዓል በመብልና በመጠጥ ብቻ እንዳናደርግ ስለዚህ ከልደትና ከጥምቀት በዓል ዋዜማ ያሉትን ሁለቱን ዕለታት እንድንጾም አዘዙን
የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕና በዐርብ በሚብትበት ጊዜ በሁለቱ ዕለታት ፈንታ ሌሎች ተለዋጭ ዕለታትን እንድንጾማቸው ይገባል በዚህም ሁለት ሥራ ይፈጸምልናል የጾም ሥራና የበዓል ማክበር ሥራ ነው እንዲሁም በግብጻውያን አብያተ ክርስቲያን የተሠራ ነው።
በይረሙን( በዓለ አስተርዕዮ ወይም ከተራ) በእሑድ ወይም በአይሁድ ሰንበት ቀን(ቅዳሜ) ቢብት ይህም ጌታ የተገለጸበት ጥር ዐሥር ቀን ነው በዋዜማው ዐርብ እስከ ምሽቱ ይጹሙ አስቀድመን እንደተናገርን ጥሉላት አይብሉ የልደትና የጥምቀት በዓልም ሰኞ ቀን ቢሆን በሰንበት ቀን ይጾሙ ዘንድ አይቻልም ነገር ግን ጥሉላትን ከመብላት ይጠበቁ።
በጥምቀትም ዕለት ከእኩለ ሌሊት በፊት ተነስተው በውኃው ላይ ይጸልዩና ይጠመቁ ሕፃናትም በሚጠመቁ ጊዜ በውኃ እንዳይገድፉ ካህናቱም ከመንጋቱ በፊት ቀድሰው ቁርባኑን ያሳርጉ እጅግም ማልደው በጥዋት ከቤተ ክርስቲያን ይውጡ በከበረ ሥርዓታቸው ጌቶቻችን ሐዋርያት እንዳዘዙ።
የመለካውያን ወገኖች ግን የልደትና የጥምቀት ዋዜማ በቅዳሜ ቀን ወይም በእሑድ ቀን ቢሆን በሦስት ሰዓት ይቀድሳሉ ከወደዱም የተባረከ ኅብስት ተመግበው ውኃ ይጠጣሉ ከዚህም በኋላ ካህናቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው በየሰዓቱ በመጸለይ ለበዓሉ የሚገባውን የነቢያትን ትንቢቶች ያነባሉ በዚያም ቀን በምሽት ይኸውም ጥር ዓሥር ነው በውኃው ላይ ይጸልያሉ ይህም አባቶቻችን ሐዋርያት እንዳዘዙት አልሆነም።
እርሳቸው የኤጲፋንያን በዓል እንዲያከብሩ አዘዋል ይኸውም መድኀኃኒታችን የተገለጠበት ካኑን በሚባል በሮም ሁለተኛ ወር በሰባት ይህም ጥር ዐሥራ አንድ ቀን ነው።
መለካውያን ግን የከበሩ አባቶች የቤተ ክርስቲያን መምህራን ያዘዙትን ይተላለፋሉ በልደትና በጥምቀት በዓል ዐርብም ረቡዕም ቢሆን አስቀድመው በርሱ ፈንታ ሳይጾሙ በጥዋት ተነሥተው ይበላሉና።
እኛንም ከበደላችን ያነጻን ዘንድ በዮረዳኖስም ወንዝ እንደ ተገለጸ የጌትነቱን ክብር በልቡናችን ይገልጥልን ዘንድ የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው ጌትነት ክብር ስግደት ለእርሱ ይገባልና ከቸር አባቱ ጋር ይቅር ባይ ከሆነ መንፈስ ቅዱስም ጋር ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን።
መጽሐፈ ስንክሳር
#ማስታወሻ
#አልሰማንም_አላየንም_እንዳትሉ_ነገ_እስከ_ምሽቱ_12_ሰዓት_ነው_የሚጾመዉ።
#ቅዳሜ_ከጥሉላት_ምግብ_ብቻ_ነው_የምንቆጠበዉ_እንጂ_ከመብል_አንከለከልም
#ይኽ_ትምህርት_ለሁሉም_የተዳረሰ_ይሆን_ዘንድ_ሼር_ላይክ_ኮመንት_እናድርገዉ_ቻናሉንም_ለብዙዎች_ተደራሽ_እያደረግን_የሚሰጡ_ትምህርቶችን_በማዳረስ_ሐዋርያዊ_አገልግሎት_እንስጥ!