መንገድ ብርሃን ይፈልጋል፤ መንገደኛ ያለ ብርሃን—በቀን ያለ ፀሐይ በሌሊት ደግሞ ያለ ጨረቃ ወይም ሰው ሠራሽ ብርሃን—መጓዝ አይችልምና። የሰማዩ ጕዞም ሰማያዊ ብርሃን ይፈልጋል፤ ይህም ከእግዚአብሔር የሚመነጭ ነው—በቃሉ፤ “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” (መዝ 119፥105)። ሕጉን (ቃሉን) የያዙ፣ ብርሃን የያዙ ናቸው። ቃሉን ዕለት ዕለት እያነበቡ የሚያሰላስሉም እግዚአብሔር በልባቸው ያበራው ብርሃን እየጨመረ፣ ጉዟቸውም እየሰመረና እየፈጠነ ይሄዳል። ክርስቲያን የጨለማ፣ ያም ድንብርብር ያለ፣ ጕዞ የለውም። ለእግሩ መብራት፣ ለመንገዱም ብርሃን የሆነውን ቃል አጥብቆ ሲይዝም በዘመን ጨለማ መካከል ወደ ግቡ መገስገስ ይችላል።