የከተማው ሁሉ መነጋገሪያ ሆኑ፤ በገበያ የነርሱ ወሬ፣ በአምልኮ ሥፍራ የነርሱ ወሬ፣ በየቤቱ የነርሱ ወሬ በቤተ መንግሥት የነርሱ ወሬ፣ በየፍርድ ቤቱ የነርሱ ወሬ፣ በየሰዉ ልብ የነርሱ ወሬ፡፡ ምን ዐይነት ሰዎች ናቸው? አንዴ ጌታ ይሉታል፤ አንዴ መሲሕ ይሉታል፤ አንዴ አዳኝ ይሉታል፤ ሌላ ጊዜ ዳኛ ይሉታል፤ ወዳጅም፣ እረኛም፣ መድኃኒትም ንጉሥም፤ የማይሉት ነገር የለም፡፡ ስለ እርሱ ሲናገሩ ቢውሉ አይደክሙም፡፡ ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመው ስሙን ያነሣሉ፡፡ ሲናገሩ እዚያው አጠገባቸው ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ዋና ከተማቸውን ኢየሩሳሌምን ባጭር ጊዜ በትምህርታቸው ሞሉአት፡፡ ብዙ ሳይቆይ ወደ አጎራባች ከተሞች ገሠገሡ፤ ሠማርያ፣ ደማስቆ፣ ኤፌሶን፣ አንጾኪያ፣ አቴና፣ ልስጥራ፣ ቆጵሮስ፣ ቆሮንቶስ፣ መቄዶንያ፣ ሶርያ፣ ሠላሳ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ትንሹን እስያና ደቡብ አውሮጳን አጥለቀለቁ፡፡
በሄዱበት ሁሉ በታላቅ ደስታና ፍቅር የሚናገሩት ስለአንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ በየደረሱበት ቦታ ከዚህ ሰው ስም የተነሣ፣ ብዙ ነገር ተለወጠ፤ ተስፋ ያጡ ተስፋቸው ለመለመ፤ የታመሙ ዳኑ፣ የታሠሩ ተፈቱ፣ ከተሞች በታላቅ ደስታ ተሞሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ እንቅስቃሴ በተሰናዳ ቦይ እንደሚወርድ ውሃ በቀላሉ አልተስፋፋም፡፡ እነዚህ ሰዎች ዐይናችሁ ለዐፈር ተባሉ፡፡ ከፍተኛ ስም ማጥፋት ደረሰባቸው፤ ተከሰሱ ተንገላቱ፤ ተደበደቡ ተዘረፉ፤ በየጎዳናው ላይ ተጎተቱ፤ በእሥር ማቀቁ፤ በሰይፍ ተቀሉ፤ በዘይት ተቀቀሉ፡፡ ይህን ሁሉ የሚያዩት ግን በሚያስደንቅ የድል ስሜት ነበረ፡፡ ከነርሱ መሐል አንዱ እንዲህ ብሏል፡-
“ … በክርስቶስ ሁልጊዜ በድል አድራጊነት እያዞረ ለሚመራን፣
የዕውቀቱንም መዐዛ በእኛ አማካይነት በየሥፍራው ለሚገልጥ አምላክ
ምስጋና ይሁን ምክንያቱም
በሚድኑትና በሚጠፉት መካከል ለእግዚአብሔር
የክርስቶስ መዐዛ ነን፤ ለሚጠፉት ወደ ሞት የሚወስድ
የሞት ሽታ፣ ለሚድኑት ግን ወደ ሕይወት የሚወስድ
የሕይወት ሽታ ነን፤ …” (2ቆሮ 2፡14-16)
የብርታታቸው ምሥጢር ምን ነበረ? በተቃውሞ መካከል እሳታቸው ያልበረደው እንዴት ሆኖ ነው? በቅኝ ግዛት ውስጥ በነበረችው ይሁዳ ውስጥ ከአንድ ትንሽ መንደር ስለ ተነሣው ወጣት ነቢይ ቁብ የማይሰጠው “ሥልጡን” ዓለም እንዴት ሊሰማቸው ቻለ? የሮማና የግሪክ ፍልስፍና በተንሰራፋበት ትንሹ እስያና አውሮጳ፣ ዓለማዊነት በገነነባቸው በሜድትራኒያን ወደቦች ዙሪያ እጅግም ትምህርት የሌላቸው እነዚህ ሰዎች ለጌታቸው ብዙ ተከታዮች ያፈሩት እንዴት ሆኖ ነው?
ለኔ የሚታየኝ ቁልፍ ታላቅ የፍቅር ኃይል ነው፡፡ ንጉሣቸውንና አዳኛቸውን በዘይቤ አባባል ሳይሆን በእውነት ነፍሳቸው እስኪወጣ ይወዱት ነበር፡፡ የወረደባቸው መንፈስ ኢየሱስን እስከ ሞት የሚያስወድድ ዓለምን እስከ ሞት የሚያስንቅ ብርቱና ንጹህ መንፈስ ነበረ፡፡ በደረታቸው ውስጥ የሚንተገተገው የማይበርድ ጽኑ ፍቅር ለራሳቸው ሳይሳሱ የእርሱን ብቸኛ ጌትነት እንዲሰብኩ አበቃቸው፡፡ ማንም ምን ያስገደዳቸው አልነበረም፡፡ እነርሱ ራሳቸው እንዳሉት፡-
“የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ ምክንያቱም አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ ርግጠኞች ሆነናል፡፡ ከዚህ የተነሣ ሁሉ ሞተዋል፤ በሕይወት ያሉትም ለሞተላቸውና ከሙታን ለተነሣላቸው እንጂ ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ፡፡” (2ቆሮ 5፡14-15)
በራሳቸው አፍ እንደ ተናገሩት ክርስቶስ የሞተላቸው እንዲድኑ ብቻ ሳይሆን እንዲሞቱም ነው፡፡ ለራስ ፍላጎት፣ ለዓለም ምኞት፣ ለተራው ነገር ሁሉ እንዲሞቱ፡፡ ለተነሣው ጌታ ለሕያው መድኅን እንዲኖሩ፡፡ ይህ ታላቅ የሕይወት ፍልስፍና፣ ይህ ጥልቅ የፍቅር ግንኙነት ዕድሜያቸውን ለተትረፈረፈ ፍሬ አበቃው፡፡ አያስቀኑም?
እኛን ምን ፍሬ ቢስ አረገን፣ ምን ወና አደረገን? ምን ባካና ደንባራ አደረገን? ምን ፍዝ አደረገን? የማንለማ የማንሰማ፣ የማናለማ የማናሰማ ለምን ሆንን ያልን እንደ ሆነ እኔ የሚታየኝ ከእነርሱ ለየት ያለው የልባችን ሁኔታ ነው፡፡ ከዚያ ኢየሱስ ከሚሉት ሰው ጋር ፍቅር “ጥቅስ” አድርጎ አልያዘንም መሰለኝ፡፡ በደግነቱ በቸርነቱ እያባበለን፣ በስሙ ጥላ ሥር መኖር ያስከብራል፤ ያተርፋል ብለን ስለምናስብ ብቻ ለየጉዳያችን ማስፈጸሚያነት ዙሪያ ዙሪያውን እንሄዳለን እንጂ የቀንና የሌሊት ሕልማችን አልሆነም፡፡ ወይም አንድ ጊዜ ወድደነው ነበር፤ እያደር ልባችንን ሌሎች እያክነፈነፉት አሁን የሺህ ወዳጆች ማጎሪያ ሆኖ ይሆናል፡፡ ወይም አንገሽግሻን የነበረች ይህች ዓለም አሁን ተቀባብታ እንደ ገና አማልላናለች፡፡
“ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና” እንደ ተባለው፡፡ (2ጢሞ 4፡10) ስለዚህ ከባድ የፍቅር ሽሚያ ላይ ወድቀናል፡፡ ዓለማዊነት የልብ ጉዳይ ነው፡፡ በክርስቶስ መቅደስ “ሰዓታት ቆመን” ልቦናችን እሸሸ ገዳሜ ሊያድር ይችላል፡፡ ሃሌ ሉያን በተለያየ ቅላጼ እያወጅን በነፍሳችን ውስጣዊ አመጽ ልንቀፈደድ እንችላለን፡፡ የክርስቶስ ፍቅር ሳይሆን ይሉኝታ ግድ እያለን ልንከላወስ እንችላለን፡፡ እንዴት ታላቅ ፍዳ ነው! የልብ ምርመራ ለሚያደርግ ሰው የፍቅር ተሐድሶ የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ የዚህም መነሻው ምንም የአስመሳይነት ቅብ የሌለው ልባዊ ጸሎት ነው፡፡
ጌታ ሆይ ካንተ ጋር ያገናኘን ፍቅር ነው፤
አንተ ስለወደድኸኝ ብቻ ነው፤
ስለወደድኸኝ አዳንኸኝ፡፡
ያን ጊዜ እኔም ወደድሁህ፤
እየቆየ ሲመጣ ግን የፍቅሬ ግለት ወረደ፤
ብዙ ነገር ልቤ ውስጥ ሲገባ ትኩሳቱ በረደ፤
ድምቀቱ ወየበ፤
ፏፏቴው ነጠበ፡፡
ጌታ ሆይ የኔ ፍቅር ብርሃን ቢደበዝዝ
ያንተ ፍቅር ኃይል የደከመ አይመስለኝም፡፡
እባክህ ተጠጋኝና አሙቀኝ
ፍዝ ነፍሴን አንቃልኝ፡፡
የግዴን እንዳልኖር፣ ብርቱ ጸጋህ ይድረስልኝ፡፡
ለሕያው ፍቅርህ ምላሽ ስሰጥ፣
ዓለም በብርሃን እንደሚጥለቀለቅ አውቃለሁ፡፡
እና እባክህ ርዳኝ፡፡
አሜን፡፡
ጋሽ ንጉሤ ቡልቻ