የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚታወቅ፣ የምንረዳው ነው። ለመረዳት ግን የታደሰ አእምሮ ይጠይቃል፤ ፈቃዱ ከመረጃ ያለፈ ነውና። መንፈሳዊ ስለሆነም ልብ ብቻ የሚሳተፍበት አይደለም፤ የተለወጠና የጠራ አእምሮ ይፈልጋል ፤ "መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ" (ሮሜ 12፥2)። ፈቃዱ ከመልካምነት ፈጽሞ የማይጎድል፣ የውስጥ ደስታ—ርካታ—ያለበት፣ እንዲሁም ፍጹም (እንከን አልባ) ነው። ይህን ለመረዳት ነው እንግዲህ የተለወጠ፣ በቃሉም ሁልጊዜ የሚታደስ አእምሮ የሚያስፈልገው። ፈቃዱን በዓለም ካለው አሠራር ጋራ እያነጻጸርን ወይም እየተነተንን የምንረዳው አይደለም፤ አእምሮን የሠራው ራሱ አዳሽ ስለሆነ፣ በርሱ እየታገዝን የምንረዳውና በተረዳንበት አቅም የምንፈጽመው እንጂ!