ረመዳን አመታዊ የዒባዳ ጉዞ በቁርአን ከቁርአን ጋር
ወሰን የሌለው ምስጋና በረመዳን ወር ቁርአንን ላወረደልን ለአላህ (ሱብሃነሁ ወተአላ) ይሁን፤
ሂባውን በቁርአን ለሰጣቸውና ባህሪያቸው ቁርአን ለነበረውና ለተሞገሱት ነቢዩ ሙሐመድ ( ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም )
ብሩሁን የተሟላውን የኢስላምን ስርአተ ህግ ለአለም ላዳረሱና እነርሱን እስከ መጨረሻ ለተከተሉ (አላህ ስራቸውን ይውደድላቸው) እላለሁ!
በየዓመቱ በሂጅራ ቀመር አቆጣጠር በዘጠነኛ ወር የሚነግሰው የቁርአን ወር የሆነው ረመዳን ሙስሊሙን ብቻ ሳይሆን የሚያነቃው ሌላውንም የእምነት ተከታይ ህብረተስብ በደመነፍስ የሚያኗኗር ፈጥኖ ገብቶ ፈጥኖ ከስራችን ጋር የሚሰወር ወር ነው፡፡
ይህ በረመዳን የሚደረገው የሩሃኒያ የቁርአን ጉዞ በሁሉም አቅጣጫ በግል ይሁን በጋራ በማታ በለው በቀን ጾመንም ይሁን ካፈጠፈርን በኋላ ከመጀመሩ እስኪያበቃ ድረስ ነዳጁ የፍጡር ማእድ ሳይሆን የአላህ ቃል የሆነው ቁርአን ሲሆን መጓጓዣው ረመዳን የሆነና ተሳፋሪው ፣ ደጃፉ ረያን ወደ ሆነው ጀነት የሚያቀኑት አንተና የቁርአን ቤተሰቦች ብቻ ናቸው፡፡
እዚህ ላይ አንድ በማህበራዊ ድረ ገጽ ከሰማሁት ምርጥ አባባል የደስታህ መጠን እንዲበዛ ከፈለግክ ቁርአንን መቅራት አብዛ የሚል ነበር!
የረመዳንም የአይን ማረፊያ እርካታ መለኪያው ይብዛም ይነስም የተለመደው የፍጡር ማእድ ሳይሆን በአንደበታችን የምንቀራው ወይም በጆሮዋችን በጥሞና የምናዳጠው የአላህ ቃል የሆነው ቁርአን ነው፡፡ በዚህ ወር በተለምዶ የሚሰራው ዋናው ተግባር ከጠዋት እስከ ማታ ከምግብ ፣ ከመጠጥ ከስጋ ግንኙነት መታቀብ ሲሆን ብታውቅም፣ ባታውቅም፣ በትረዳውም፣ ባትረዳውም፣ መንገድህን የሚያበራልህ ነገ አማላጅ የሚሆንልህ ቁርአንና እርሱን ተከትለው የሚመጡ ተግባራት ናቸው ፡፡
አላህም ( ሱብሃኑ ወተዓላ) በቁርአኑ ሲያስታውስህ፡-
شَهْرُ رَمَضَانَ الَّذِي أُنزِلَ فِيهِ الْقُرْآنُ هُدًى لِّلنَّاسِ وَبَيِّنَاتٍ مِّنَ الْهُدَىٰ وَالْفُرْقَانِ ۚ
(እንድትጾሙ የተጻፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲኾን ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው፡፡(አል በቀራህ ፡ 185)
በእርግጥ የአላህ (ሱብሃኑ ወተኣላ) ቁርአን በሁሉም ወራት እንደቅርበትህ ይዘህ ወይም ሃፍዘህ የምትቀራው ህይወትህን ህያው የሚደርግልህ ሲሆን በረመዳን ደግሞ የበለጠ ደረጃህን ከፍ የሚያድግ ነው፡፡
አላህ (ሱብሃኑ ወተኣላ) በረመዳን የቀን ሰአት ከምግብ ፣ ከመጠጥ ከስጋዊ ግንኙነት እንድንታቀብ ሲያዝ ነፍሳችንን በቁርንና በርሱ ነጸብራቅ በሆኑት ተግባራት እንድንሞላ ፣ በቁርአን ከመቸውም በበለጠ እንድኖር የበለጠ የነቢዩ ሙሐመድ ( ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) አጭር የህይወት ገጽታ ይነግረናል፡፡
ነቢዩ ሙሐመድ ( ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) በህይወታቸው አስተማሪያቸው ጂብሪል (ዓለይሂ ሰላም) የተለመደው የዋህይ ማስተላለፍ ዚያራ ያደርጋቸው እንደነበረና በረመዳን ጊዜ የሚደርገው ዚያራ ቁርአንና ስለ ቁርአን ብቻ ነበር፡፡
እንዲህም ሲዘይራቸው ልግስናቸው ዝናብ ከሚያመጣው ንፋስ የበለጡ ፈጣን ነበሩ ይባላል፡፡ምን ያህል ቢደሰቱ ነው ? ድሮም ሲለግሱ ድህነትን የማይፈሩ ሆነው ነበር የሚለግሱት!
ይህ ታላቅ ወር ሲገባ ከጂብሪል(ዓለይሂ ሰላም) ጋር በቁርአን መማማር ብቻ ነበር ስራቸው ወይም በመስጊድ ዒእቲካፍ (በመስጊድ ውስጥ ለኢባዳና በኢባዳ) መቆየት ነበር፡፡እድሜህ አብቅቷልና በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅም ብሎ አላዘዛቸውም ፤ግን እንደማይረሱት ማንም ሊበርዘው እንደማይችል ቃል የተገባላቸው ነበር፡፡
ለዚህም ነው የነቢዩ ሙሀመድ( ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) ብዙው ትኩረት አብዛኞቻችን ስለምንዘጋጅለት የፍጡር አይነት ሳይሆን የተለያዩ የዒባዳ አይነቶችና በቁርአን ስለምናደርገው የዒማን ጉዞ ነው፡፡
የቁርአን ጉዞ ምንዳው ቁጥር ስፍር የሌለው በአንድ ፊደል እስከ አስር ምንዳ የሚያስገኝ ሲሆን ፣በረመዳን ግን "እኔ ነው የምመናዳው "
በእርግጥም ይህ መለኮታዊ ቃል ኪዳን ልክ የሌለው እንደ እዝነቱ ወሰን የለሽ ነው፤ ከሰው መረዳት በላይ ነው!
ይሁንና ይህ የተቀደሰ ጉዞ ብዙ መሰናክሎች ፣ፍጥነቱን የሚቀንሱ ውጣ ውረዶች እና ችግሮች የተከበበ ለመሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ካልተፈለገ የረመዳን ገበያ መውጣት ባሻገር የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች(በተለይ በውድድር ስም ፣በሽልማት የታጀበ ) ፣ በእጃችን የሚገኘው ሞባይል እና መሰል መገልገያዎችና አፕሊኬሽንስ ከአላማችን እንዳያዘናጉን ልንጠቀቃቸው እና መስመር ልናስይዛቸው የሚገቡ ናቸው!
የረመዳን በቁርአን ጉዞዬ ለመሆኑ ስለ እኔ አላህ ምን ብሏል ብል ማንም እናቴም ትሁን ወይም አባቴ ያላሉኝን ቀድሞ ገልጾኛል !….ከሙታን እንደነበርኩ ፣ በፍትወት ጠብታ ህይወት እንደሰጠኝ ገልጾኛል፡፡
ከዚያም በተጠበቀ ጠባብ የእናቴ ማህጸን ለተወሰነ ጊዜ እንዳቆየኝ ከዚያም እርቃኔን ተወልጄ ነውሬ እንዲሸፍኑና ስም እንዲሰጡኝ እና የምድርን ሃላል እንድመገብ ፣ ከእናቴ ጡት ወይም ከሌላ አጥቢ ቢያንስ ሁለት አመት እንድጠጣ አዞ ፣ አድጌ እድማር ፣ እርሱን እንድገዛ ወላጆቼን እንዳከብር ፣ ዘመድ እንድ ጠይቅ ፣ ለጎረቤት ፣ለእንግዳ መልካም እንድውል ፣ እንዳገባ ቤተሰብ እዳፈራ ፣ከሰጠኝ ልጆችን ባግባቡ እንደሳግድ እንዳስተምር ፣ ሌላውን በምችለው እንድጠቅም በቁርአኑ ጉዞዬ የነገረኝ ነው፡፡
መኖር እንዳለም መሞት ለነቢዩም( ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) እንዳልቀረ ቀብር የሚባል ጊዚያዊ መቆያ የአኪራ መሸጋገሪያ እንዳለ ፣ከዚያም መቀስቀስ ብሎም በአላህ ፊት መቆምና መጠየቅ ጀነት ወይም ጀሃነም እንደተዘጋጀ መሃል ሰፋሪ እንደሌለ በቁርአን ጉዞዬ የተነገረኝ ነው ፡፡
ሁሉም በረመዳን የቁርአን ጉዞው ስለራሱ ብዙ ማለት ይችላል ፤ባለው የቁርአን ግንኙነት የህይወትን ቀና መንገድ ያስቀምጣል ፣ጠማማውንም ያስጠነቅቃል ፡፡
እንዲህ እያለ ቁርአን በህይወት ጉዞህ ይመሰክርልሃል ወይም ይመሰክርብሃል!
መልካም የቁርአን ወር
ወሂብ ኩርቱ
ረመዳን 1446
ከዶሃ -ቀጠር
https://t.me/MuhammedSeidAbx