እኚህ ሰው ማን ናቸው?
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
15፥95 *"ተሳላቂዎችን ሁሉ እኛ በቅተንልሃል"*፡፡ إِنَّا كَفَيْنَاكَ الْمُسْتَهْزِئِينَ
ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከሕፃን እስከ አዋቂ፣ ወጣትም ሆነ አዛውንት ስለ እሳቸው ሲወራ "ጆሮ ዳባ ልበስ" የሚል የለም። ሁሉ ስለ እሳቸው ሲወራ አዳሜ ሆነ ሔዋኔ ጆሮውን አስግጎ ይሰማል፥ ከሁሉም ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ የሚጠሏቸው ሳይቀር እንኳን ቢሆን ስለ እሳቸው ለመስማት እና ስለ እሳቸው ለማወቅ ይፈልጋሉ። ዝም ብለህ ሰው የተሰበሰበበት መሀል ገብተህ እና ድምጽክን ከፍ አድርገህ፦ "እከሌ" ብለህ ወይም "እከሊት" ብለህ ብትጣራ ፊቱን እና ትኩረቱን ወደ አንተ የሚያዞረው የጠራከውን ስም ባለቤት ብቻ ነው፥ ከሌለም ደግሞ ማንም ፊት እና ትኩረት የሚሰጥክ አይኖርም። ነገር ግን ሰው የተሰበሰበበት ስፍራ ሄደህ የእሳቸውን ስም ጠርተህ ንግግር ብትጀምር ሁሉም ፊቱን እና ትኩረቱን ወደ አንተ ያደርጋል፥ ትኩረት የማይሰጥህ የለም ቢባል ማጋነን እና ማበል አይሆንም። ስለ እሳቸው ለማወቅ የማይሰለፍ አይኖርም፥ እኚህ ሰው፦
1ኛ. የእልፍ አእላፋት መጻሕፍት ርእስ በመሆን ብዙ ጸሐፊያን የከተቡላቸው ናቸው፣
2ኛ. በሁሉም ልብ ውስጥ በአሉታዊ ሆነ በአንታዊ በሁለት ወገን እንደተሳለ ሰይፍ ሰርስረው የገቡ ናቸው፣
3ኛ. አስተምህሮታቸው የተሟላ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ የሕይወት ዘይቤ በመሆኑ የዓለማችን ተግዳሮት ነው የተባለላቸው ናቸው፣
4ኛ. "የዓለማችን ቁጥር አንድ አውንታዊ እና አሉታዊ ተጽዕኖ አሳዳሪ" ተብለዋል፥ ለሕሩያን አውንታ ተጽዕኖ እንዲሁ ለእኵያን አሉታዊ ተጽዕኖ አሳዳሪ ናቸው፣
5ኛ. ስለ እርሳቸው ማንነት የገባው ሰው፦ "ሕይወትህን መስዋዕት አርግ" ቢባል ያለ አንዳች ማቅማማት ሕይወቱን እስከ ሞት የሚያደርግላቸው ናቸው።
6ኛ. በታሪክ ውስጥ እሳቸውን ለማነወር፣ ለማበሻቀጥ፣ ለማብጠልጠል ብዙ ጦማሪያን ጦምረዋል፣ ብዙ ኃያሲያን ኃይሰዋል፤ ብዙ ተቺዎች ተችተዋል፣ ብዙ ተሳላቂዎች ተሳልቀዋል። ቅሉ ግን የጦማሪያን ጦማር፣ የኃያሲያን ኂስ፣ የተቺዎች ትችት፣ የተሳላቂዎች ስላቅ ከሟቾች ጋር ሲያልፍ የእሳቸው ስም እና የሰዎችን ሕይወት የቀየሩበት መጽሐፍ እስካሁን አለ የተባለላቸው ናቸው።
እኚህ ሰው ማን ናቸው? አዎ! የዓለማቱ ጌታ የአሏህ መልእክተኛ እና የነቢያት መደምደሚያ ነቢዩ ሙሐመድ"ﷺ" ናቸው። በእርሳቸው ላይ የወረደው ሐቅ ለሰዎች የሚጠቅም ስለሆነ በምድር 1400 ዓመት ቆይቷል፥ ባጢል ቢሆን ኖሮ በእንጭጩ ኮረፋት ሆኖ ተግበስብሶ ይጠፋ ነበር፦
13፥17 *"እንደዚሁ አላህ ለእውነት እና ለውሸት ምሳሌን ያደርጋል። ኮረፋቱማ ግብስብስ ኾኖ ይጠፋል፥ ለሰዎች የሚጠቅመውማ በምድር ላይ ይቆያል፡፡ እንደዚሁ አላህ ምሳሌዎችን ይገልፃል"*፡፡ كَذَٰلِكَ يَضْرِبُ اللَّهُ الْحَقَّ وَالْبَاطِلَ ۚ فَأَمَّا الزَّبَدُ فَيَذْهَبُ جُفَاءً ۖ وَأَمَّا مَا يَنفَعُ النَّاسَ فَيَمْكُثُ فِي الْأَرْضِ ۚ كَذَٰلِكَ يَضْرِبُ اللَّهُ الْأَمْثَالَ
ሐዋ. ሥራ 5፥38-39 አሁንም እላችኋለሁ፦ ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም! *ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፥ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም። በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ"*።
ገማሊያ እንደተናገረው ይህ የነቢያችን"ﷺ" እሳቦት ከሰው ከሆነ ይጠፋ ነበር፥ ግን የነቢያችን"ﷺ" ግልጠተ-መለኮት ከፈጣሪ ስለሆነ ገና በእንጭጭነቱ የመካህ ቁሬይሾች፣ የመዲና በኑ ቁሬይዛህ፣ የሮሙ ባዛንታይን በዕውቀት መሞገት ሲያቅታቸው በጉልበት ሊጠፉት ሞክረው አልተሳካላቸው። ከርሞም ሆነ ዘንድሮም እሳቸው ላይ ለሚሳለቁን ተሳላቂዎች አሏህ በቅቶላቸዋል፥ በእርሳቸው ላይ የወረደውን የአሏህን ብርሃን በአፎቻቸው ለማጥፋት ቢፈልጉ እና ቢጠሉም አሏህ ብርሃኑን ገላጭ ነው፦
15፥95 *"ተሳላቂዎችን ሁሉ እኛ በቅተንልሃል"*፡፡ إِنَّا كَفَيْنَاكَ الْمُسْتَهْزِئِينَ
61፥8 *"የአላህን ብርሃን በአፎቻቸው ሊያጠፉ ይሻሉ፥ ከሓዲዎቹ ቢጠሉም እንኳ አላህ ብርሃኑን ገላጭ ነው"*፡፡ يُرِيدُونَ لِيُطْفِئُوا نُورَ اللَّهِ بِأَفْوَاهِهِمْ وَاللَّهُ مُتِمُّ نُورِهِ وَلَوْ كَرِهَ الْكَافِرُونَ
ይህንን ብርሃን ለማጥፋት እፍ ባሉ ቁጥር እያነደዱት መሆኑን ይዘነጋሉ፥ ኢሥላም በፍጥነት መጠነ-ሰፊ የእድገት መርሓ-ግብር እየታየበት ያለው በምዕራባውያን መሆኑ እፍ ባሉ ቁጥር የሚያነዱበት ውጤት ነው። አሏህ ሂዳያህ ይስጣቸው! ለእኛም ጽናቱን! አሚን።
“ፊዳከ አቢ ወኡሚ ያ ረሡሉሏህ” فِدَاكَ أَبِي وَأُمِّي يَا رَسُول اللَّه
✍ከዐቃቤ እሥልምና ወሒድ
https://t.me/Wahidcomወሠላሙ ዐለይኩም