«ለአደም ስገዱ»
በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
2፥34 ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ አስታውስ፡፡ وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ
አምላካችን አሏህ ለመላእክት«ለአደም ስገዱ» በማለት አዘዛቸው፦
2፥34 ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ አስታውስ፡፡ وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ
የአዳም እና የሔዋን ታሪክ ላይ ሚካኤልም ወጥቶ መላእክቱን ሁሉ ጠራ፡- "ጌታ አምላክ እንዳዘዘው ለአምላክ መልክ ለአዳም ስገዱ" አለ፦
"ሚካኤልም ወጥቶ መላእክቱን ሁሉ ጠራ፡- "ጌታ አምላክ እንዳዘዘው ለአምላክ መልክ ለአዳም ስገዱ" አለ።
Life of Adam and Eve Chapter XIV(14) Number 1
ቀሌምንጦስ ዘሮም"Clement of the Rome" ከጴጥሮስ የተቀበለው ንግግር ተብሎ በሚታመነው መጽሐፍ ላይ እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ ወደ አዳም ራሳቸውን አዘንብለው ለአዳም እንደሰገዱ ይናገራል፦
ቀሌምንጦስ 1፥41 አራዊት፣ እንስሳት፣ ወፎች እና "እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ" ወደ አዳም ተሰበሰቡ ከፊቱም ቁመው ራሳቸውን አዘነበሉ "ለ-"አዳም ሰገዱ"።
"እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ" ማለት መላእክትን ይጨምራል፥ ምክንያቱም መላእክት ፍጡራን ኑባሬዎች ናቸውና፥ ፍጥረት ሁሉም ለአዳም ይታዘዝ እና ቃሉንም ይጠብቅ ነበር፦
ቀሌምንጦስ 1፥42"ፍጥረት ሁሉም ለአዳም "ይታዘዝ" እና ቃሉንም ይጠብቅ ነበር።
አምላካችን አሏህ ለመላእክት«ለአደም ስገዱ» ሲል ለኢብሊሥ "ስገድ" አለማለቱን አያሳይም፥ ምክንያቱም አሏህ «ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ?» ብሎታልና፦
7፥12 አላህ፦ «ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ?» አለው፡፡ قَالَ مَا مَنَعَكَ أَلَّا تَسْجُدَ إِذْ أَمَرْتُكَ
“ባዘዝኳችሁ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ" ሳይሆን “ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ" አለው፥ “ባዘዝኩህ” የሚለው ኃይለ ቃል "ለአደም ስገድ" ብሎ አዞት እንደነበር ቁልጭና ፍንትው አድርጎ ያሳይል። ለምሳሌ፦ ፈጣሪ አዳምን "መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ" ብሎት ነበር፦
ዘፍጥረት 2፥17 ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ።
ጥቅሱ ላይ "አትብላ" እንጂ "አትብሉ" አላላቸውም፥ ነገር ግን ሔዋን፦ "እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም" ያህዌህ ብሎናል ብላለች፦
ዘፍጥረት 3፥3 ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ ያህዌህ አለ፦ "እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም"።
ለሁለቱም ግን "አትብሉ" ያለበት ትእዛዝ አለመገለጹ ግን "አላላቸውም" እንደማንል በተመሳሳይ "ስገድ" ያለበት ጥቅስ አለመኖሩ "ስገድ አላለውም" አያሰኝም። ሲቀጥል "መላእክት" በሚል ቃል መነሻ ቅጥያ ላይ "ለ" የሚለውን መስተዋድድ "ብቻ" በሚል መረዳት የለብንም፦
7፥179 ”ለ”እነርሱ ልቦች አሏቸው፥ ግን አይገነዘቡበትም፣ “ለ”እነርሱም ዓይኖች አሉዋቸው፥ ግን ዐያዩበትም፣ “ለ”እነርሱም ጆሮዎች አሉዋቸው ግን አይሰሙበትም፡፡ لَهُمْ قُلُوبٌ لَّا يَفْقَهُونَ بِهَا وَلَهُمْ أَعْيُنٌ لَّا يُبْصِرُونَ بِهَا وَلَهُمْ آذَانٌ لَّا يَسْمَعُونَ بِهَا
"እነርሱ" የተባሉት ከሰው እና ከጂኒ ያመጹ ከሓድያን ሲሆኑ "እነርሱ" በሚል ቃል መነሻ ቅጥያ ላይ "ለ" የሚለውን መስተዋድድ ስላለ "ልቦች" "ዓይኖች" "ጆሮዎች" ያሉአቸው ኩፋሮች ብቻ ናቸው እንደማንል ሁሉ "ለመላእክት" የሚለውም ለኢብሊሥ እንዳልተባለ ማስረጃ አይሆንም፦
2፥34 ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፥ ኢብሊሥ ብቻ ሲቀር። "እምቢ" አለ ኮራም ከከሓዲዎቹም ኾነ፡፡ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ أَبَىٰ وَاسْتَكْبَرَ وَكَانَ مِنَ الْكَافِرِينَ
“ኢብሊሥ ብቻ ሲቀር” በሚለው ኃይለ ቃል ላይ “ሲቀር” የምትለዋን ይዘን "ኢብሊሥ ከመላእክት ነበር" ማለት አሁንም የቁርኣንን ሰዋስው ካለመረዳት የሚመጣ ጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ነው፦
26፥77 «እነርሱም ለእኔ ጠላቶች ናቸው፡፡ ግን የዓለማት ጌታ ሲቀር እርሱ ወዳጄ ነው»፡፡ فَإِنَّهُمْ عَدُوٌّ لِّي إِلَّا رَبَّ الْعَالَمِينَ
ኢብራሂም፦ “ለእኔ ጠላቶች ናቸው። ግን የዓለማት ጌታ ሲቀር” ማለቱን አስተውል! “ሲቀር” የሚለውን አፍራሽ ቃል ይዘን ከዓለማቱ ጌታ ውጪ ለኢብራሂም ሁሉም ጠላት ነውን? አማንያን፣ ነቢያት፣ መላእክት፣ እንስሳትስ ጠላት ናቸውን? አይ “በቀር” የሚለው በአንጻራዊ ደረጃ የአሏህን ወዳጅ ለመሆን የገባ እንጂ “ሁሉን ጠላት ናቸው ከአሏህ በቀር” ማለቱን አያሳይም ከተባለ እንግዲያውስ “በቀር” የሚለው በአንጻራዊ ደረጃ ኢብሊሥ ብቻ አለመታዘዙን እንጂ መላእክት ውስጥ መካተቱን አያሳይም።
ዲያብሎስ ክሣደ ልቡናውን በማጽናት እና ራሱን በማኩራት ፈጣሪው ለፈጠረው ለአዳም መስገድን "እምቢ" ብሏል፦
2ኛ መቃብያን 9፥3 ክሣደ ልቡናውን በማጽናት እና ራሱን በማኩራት ፈጣሪው ለፈጠረው ለአዳም መስገድን እምቢ ብሏልና።
ዲያብሎስም ከማዕረጉ የወረደው "ለአዳም አልሰግድም" በማለቱ እንደሆነ በጸጸት ተናግሯል፦
3ኛ መቃብያን 1፥15 "ለአዳም አልሰግድም በማለቴ እግዚአብሔር ስለ አባታቸው ስለ አዳም ከማዕረጌ አዋርዶኛልና።
አሏህ ለመላእክት«ለአደም ስገዱ» ማለቱን አክብሮቱን ያሳያል እንጂ "አደምን አምልኩ" የሚለውን አያሲዝም። እንደዛማ ቢሆንማ ፈጣሪ በኢየሱስ ለፊላድልፍያ ጉባኤ ኤጲስ ቆጶስ ለሆነው ሰው እንደሚያሰግድ ይናገራል፦
ራእይ 3፥9 እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት "ይሰግዱ" ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ። ἰδοὺ ποιήσω αὐτοὺς ἵνα ἥξουσιν καὶ προσκυνήσουσιν ἐνώπιον τῶν ποδῶν σου, καὶ γνῶσιν ὅτι ἐγὼ ἠγάπησά σε.
እዚህ አንቀጽ ላይ "ስግደት" ለሚለው የገባው ቃል "ፕሩስኩኔኦ" προσκυνέω ነው፥ እና ፈጣሪ ኤጲስ ቆጶሱን እያስመለከ ነው? "ኸረ በፍጹም" ካላችሁ እንግዲያውስ ከላይ ያለውን እሳቤ በዚህ መልክ እና ልክ መረዳት ቀላል ነው። አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይወፍቀን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcomወሠላሙ ዐለይኩም