#አሳዛኝ_ዜና
በስንዴና ገብስ ምርቱና በደግነቱ የሚታወቀው የአርሲ ምድር ዛሬ ዛሬ ደም ሲጠጣ የሚውል የሚያድር ከሆነ ሰነባበቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን፣ ሽርካ ወረዳ፣ ሶሌ ፈረንቀሳና ሶሌ ጡጃ ቀበሌ ኅዳር 19 ለኅዳር 20 አጥቢያ ከሌሊቱ 8፡00 ገደማ በአንድ ቤተሰብ ዙሪያ ያሉ 9(ዘጠኝ) ሰዎች ተገድለው አድረዋል፡፡ ከሟቾቹ መሐል 70 ዓመት ያለፋቸው ኹለት አረጋውያንን አባቶች እንዳሉ የታወቀ ሲሆን በእድሜ የገፉ እናቶችና ወጣቶችም አሉበት፡፡ ፓርቲያችን የሟቾች ስም ዝርዝር ደርሶታል፡፡
ጭፍጨፋውን በአካባቢው ሰዎች አጠራር “የጫካው ሸኔ” እንዳደረገው እርግጠኛ እንደሆኑ የሚናገሩት ነዋሪዎች ሌሊት ላይ መጥተውና እየመረጡ ወንዝ ዳር ከወሰዱ በኋላ አስተኝተው ጭካኔ በተሞላበት መልኩ እንደፈጇቸው ገልጸውልናል፡፡ ፓርቲያችን ባደረገው ማጣረት ከሟቾች በተጨማሪ አቶ ገነነ ተካልኝ፣ መ/ር ካሳሁን እሸቱ፣ አቶ አበበ አሰፋ እና አቶ ሽብሩ አሰፋ የተባሉ ግለሰቦች ታግተው እንደተወሰዱና እስከአኹኗ ሰዓት ድረስ በምን ኹኔታ ላይ እንደሚገኙ እንደማያቁ ለመረዳት ችለናል፡፡ ከሰሞኑ በዚኹ አካባቢ 2 ሰዎች ተገድለው ሌሎች 8 ሰዎች ታግተው እንደተወሰዱ የአካባቢው ነዋሪዎች የገለጹልን ሲሆን ታጋቾቹ የትና በምን ኹኔታ እንዳሉ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸውም ነግረውናል፡፡
አርሲ ውስጥ ባለፉት 5 ዓመታት በተለይ ማንነትና ሃይማኖት ተኮር ዘግናኝ ግድያዎች እንደሚፈጸሙ የገለጹልን ነዋሪዎች ሞቱ እንኳን በቅጡ እንደማይነገር ይህም እጅግ የገለልተኝነት፣ ረዳት አልባነትና ተስፋ መቁረጥ በነዋሪው ማስፈኑን ነግረውናል፡፡ በቅርብ ጊዜያት ደግሞ ‘መከላከያ ነን’ ያሉ ገብተው ከነዋሪው በግዳጅ መሣሪያ እያስወረዱ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎች ይኽም በተለይ በአካባቢው ለሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይል እጅግ ምቹ ኹኔታ እንደፈጠረለትና በቀላሉ መንደር ውስጥ ገብቶ ገድሎና ዘርፎ እንደሚወጣ ከሞላ ጎደል አካባቢውን ወደማስተዳደር እየሄደ ነው ብለው ለማመን እንደተገደዱ ተናግረዋል፡፡
ዛሬ ሌሊት ግድያ የተፈጸመበት አካባቢ በግምት 3 ኪ.ሜ ርቀት ላይ መከላከያ ሠራዊት ካምፕ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን ጥቃት የተሰነዘረባቸውን ነዋሪዎች ለመታደግ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳላደረገና ለማትረፍ ጥረት እንዳልነበረ ኹሉ ለማወቅ ችለናል፡፡
“አኹንም አልረፈደም ቢያንስ አስከሬን እንድናነሳና እንድንቀብር መደረግ አለበት፡፡ የታገቱትንም ለማስለቀቅ የጸጥታ መዋቅሩ መሥራት አለበት” የሚሉት ነዋሪዎች መንግሥት ከለላ አድርጎ ካልጠበቃቸው ለምን መሣሪያ እንዳስወረዳቸው ጥያቄ እንዲቀርብላቸውም በተስፋ መቁረጥ ተማጽነዋል፡፡
ፓርቲያችን በተደጋጋሚ እንደሚለው ተጠያቂነት ከሌለ መግደል ቀላል እንደሚሆን በሌላ በኩል ደግሞ በንጹሓን እልቂት ታጣቂዎችም መንግሥትም እኩል ተጠያቂነት እንዳለባቸው አምነው እንዲህ ካለው አገርን ወደ ሁለንተናዊ ቀውስ ከሚመራ ድርጊት እንዲታቀቡ፤ የጸጥታ ኃይሉም የፓርቲ ጉዳይ አስፈጻሚ ሳይሆን የሕዝብ ልጅነቱን እንዲህ ባለው እልቂት ፈጥኖ በመድረስና በማስቆም እንዲያስመሰክር አበክረን እናሳስባለን፡፡ አርሲ በአጠቃላይ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጎ ነዋሪው በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ካልተሠራ እልቂቱ ከዚህ የከፋ ሊሆን እንደሚችል በውል መረዳት ያስፈልጋል፡፡
በዚኹ አጋጣሚ ፓርቲያችን ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን እየተመኘ ኹኔታውን በቅርበት በመከታተል ለሕዝቡ መረጃ እንደሚያደርስ ቃል በመግባት ነው፡፡
እግዚአብሔር አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
እናት ፓርቲ
ኅዳር ፳ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ