የሰይጣን ድንፋታ
ባየህ ጊዜ፡-
የኔዎቹን ክንብንቤ
የኔዎቹን ሽፍንፍኔ
ባየህ ጊዜ፡-
የኔዎቹን ጅቡንቡኔ
የኔዎቹን ዝይንይኔ፤
ለምን ይሆን- አራስ ነብር እንዳየ - አይንህ የሚፈጥ?
ለምን ይሆን - እንጥልህ እስኪወርድ - የም'ደነግጥ?
ለምን ይሆን - በቁጭትህ ማእበል - የምትናወጥ?
እንስቶችህ ሆነው - ለእርቃን ሩብ ጉዳይ
ውብ ገላቸው ሆኖ - የጎዳና ሲሳይ፤
ሆና እያለች ሚስትህ - በግድ የለበሰች
ሆና እያለች እህትህ - ለብሳ ያልለበሰች
ሆና እያለ አማትህ - ለብሳ እንዳለበሰች
ሆና እያለች ልጅህ - ለብሳ እንዳወለቀች፤
አክስት፣ እናቶቼ - ስለተከናነቡ
ሚስት፣ እህቶቼ - ስለተሸፋፈኑ
እንስት፣ ልጆቼ - ስለተጀቧቦኑ
በኒቃብ ተውበው - ስለተዘየኑ፤
ለምን ይሆን የምትለኝ፡-
"ባህላችን - በዶዘር ፈንጅ ተናደ
"እሴታችን - በ'ቶን እሳት ነደደ
"ትውፊታችን - አገር ጥሎ ተሰደደ"?
ከዚህ ወዲያ ምን አለ?
የጋኔን ሹክሹክታ
የሰይጣን ድንፋታ፡፡
ካይን፣ ከከንፈር ላይ - የሚሰነቀሩ
ከፊት፣ ከጡት ላይ - የሚቸነከሩ
ከፀጉር፣ ዳሌ ላይ - የሚተከሉ
ከባት፣ ተረከዝ ላይ - የሚቸከሉ
የዝሙት ቀስቶች
ያመንዘራ ጦሮች
የሰይጣን አረሮች
መክነው ውለው - መክነው ስላደሩ
ከስረው ሰንብተው - ከሽፈው ስለቀሩ?
እንዴት ትለኛለህ፡-
"ባህላችን - በዶዘር ፈንጅ ተናደ
"እሴታችን - በ'ቶን እሳት ነደደ
"ትውፊታችን - አገር ጥሎ ተሰደደ"?
ከዚህ ወዲያ ምን አለ?
የጋኔን ሹክሹክታ
የሰይጣን ድንፋታ፡፡
እንስቶችህ ሆነው - እትዬ እርቃን ቀረሽ
- ያልለበሰች ለባሽ
ውብ ገላቸው
- እንደ ሳልባጅ ጨርቅ - ክፉኛ ተረካክሶ
- እንደ መኸር ገለባ - በየቦታው ተልከስክሶ
ውብ ገላቸው - ሜዳው አንሶት
- አደባባይ ጠቦት
- ጎዳናው ተፍቶት
በየቀዬ - በየስርጣስርጡ ሲመናሽ
በየጢሻ - በየጉራንጉሩ ሲፍነሸነሽ፤
ለምን ትለኛለህ፡-
"ባህላችን - በዶዘር ፈንጅ ተናደ
"እሴታችን - በ'ቶን እሳት ነደደ
"ትውፊታችን - አገር ጥሎ ተሰደደ"?
ከዚህ ወዲያ ምን አለ?
የጋኔን ሹክሹክታ
የሰይጣን ድንፋታ::
በዶክተር ጀማል ሙሃመድ
የባህር ዳር አህለሱና መሻይኾች ገፅ
https://t.me/alateriqilhaq
كن على بصيرة