ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት እና እምዬ ምኒልክ
ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት የውጫሌ ውል ፈርሶ ዳግማዊ ምኒልክ የክተት አዋጅ ሲያውጁ "ሞቴን ከምኒልክ ያስቀድመው!" ብለው ነበር የጎጃምን ሰራዊት አሰልፈው ዓድዋ የደረሱ። የአጼ ምኒልክ እና የንጉሥ ተክለ ሀይማኖት ፍቅርና መተማመን በጣም ጥብቅ እንደነበር በታሪክ ተጽፏል፡፡ ሁለቱን መሪዎች ያቀራረባቸው እና አንድ ያደረጋቸው ደግሞ እርስ በእርስ ያካሄዱት የእምባቦ ጦርነት ነበር፡፡
የእምባቦ ጦርነት ዳግማዊ ምኒልክ ከመንገሳቸው በፊት ከጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት ጋር ባለመግባባት ያካሄዱት ጦርነት ነው፡፡ በጦርነቱ ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት ቆስለው በንጉሥ ምኒልክ እጅ ይወድቃሉ፡፡ ምኒልክም የንጉሥ ተክለ ሀይማኖትን ቁስል ራሳቸው እያጠቡ አንድ ጥያቄ ንጉሡን ጠየቋቸው፡፡
“እኔን ብትይዘኝ ምን ታደርገኝ ነበር?”
“እገልህ ነበር!” በማለት ንጉሠ ተክለ ሀይማኖት ይመልሳሉ፡፡ ምኒልክም የንጉሡን ግልጽነት እያደነቁ ከህመማቸው እስኪያገግሙ በመንከባከብ ወደ ጎጃም ከሰራዊታቸው ጋር ይመልሷቸዋል፡፡
በዚህ የዳግማዊ ምኒልክ እንክብካቤ ልባቸው የተነካው ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት ምኒልክን "እምዬ" ብለው ስም አወጡላቸው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮም ምኒልክ የእናትነት ርህራሄ ማሳየ በሆነው መጠሪያ "እምዬ ምኒልክ" ተብለው እየተጠሩ ዛሬን ደርሰዋል።
ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረሩ የክተት አዋጅ ሲታወጅ "ሞቴን ከምኒልክ ያስቀድመው!" ያሉትም ከዚህ መውደዳቸው የተነሳ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት በዓድዋ ጦርነት ወቅት የዘመቻ ዋና የጦር መሪ እና የንጉሠ ነገሥቱ የቅርብ አማካሪ ነበሩ። በጦር መሪያቸው ራስ ወርቄ የሚመራው ሰራዊታቸውም በተሰለፈበት ግንባር ሁሉ ጣሊያንን ድባቅ በመምታት በዓድዋ ተራሮች ለተመዘገበው ድል ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
✅ዓድዋ