የተዘለለ የታሪክ ገጽ
(በእውቀቱ ስዩም )
ግዙፉ ጎልያድ፥ ያህዛብ ጀግና አስገመገመ
ዳዊትም ሰምቶ ፥ጎንበሰ አለና ጠጠር ለቀመ፤
እናም በእለቱ
ገበጣው ቀርቦ፤ ገጥመው ሁለቱ
ከግድግዳው ላይ፥ ሳይወርድ ወንጭፉ
ከየሰገባው፥ ሳይወጣ ሰይፉ ተሸናነፉ;;
የቆፈሩትን፥ ጉድጓዱን ደፍነው
የገበጣውን ፥ጠጠር በትነው
ያወጁት አዋጅ ፥ አንድ ላይ ሆነው፥
ይሄ ነው ቃሉ ፦
“ የተከተልኸኝ ሰራዊት ሁሉ
ዋንጫህን አንሳ ፤ጦር ጋሻህን ጣል
የትኛው ሀገር
የትኛው ሀሳብ
ከህይወት በልጦ አንገት ያሰጣል?