ሞሃ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ሙሉ በሙሉ ምርት ሊያቆም መኾነን ከምንጮች ሰምቻለኹ ሲል ሪፖርተር ዘግቧል። ሞሃ፣ ሥራ ለማቆም የተቃረበው በውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደኾነና ከስምንት ሺህ በላይ ሠራተኞቹ ሥራ እንዳቆሙ መረዳቱን ዘገባው ጠቅሷል። ፋብሪካው ለረጅም ጊዜ ጠርሙሶችንና መለዋወጫዎችን ጨምሮ የተለያዩ ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ ማስገባት እንዳልቻለና ላንድ ዓመት ያህል ምርት እንዳላመረተ ተገልጧል። የሚድሮክ ኩባንያ ንብረት የኾነውና ከአዲስ አበባ ውጭ አምስት ፋብሪካዎች ያሉት ሞሃ፣ ለበርካታ ዓመታት ፔፕሲ፣ ሚሪንዳ እና 7-አፕ ለስላሳ መጠጦችን በማምረት ይታወቃል።