መስከረም ፲
በዚህች ዕለት ጼዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል፤ ከሠሌዳዋም ቅባት የሚንጠፈጠፍባት የእመቤታችን የድንግል ማርያም ሥዕል ተዐምር ተገለጠ።
ይህችን ሥዕል የሳላት ቅዱስ ሉቃስ ነው። ወደ ጸዴንያ እንዴት መጣች ቢሉ፤ አንዲት ማርታ የምትባል ሴት ነበረች በቤቷም እንግዳ ትቀበል ነበር። ድንግል ማርያምንም አብዝታ ትወዳት ነበር። በአንዲት ቀንም ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል መነኩሴ በእንግድነት መጣ። በማግስቱ ስትሸኘው ወዴት ነህ ብላ ጠየቀችው። እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሆነ ነገራት። እርሷም ሲመለስ የእመቤታችንን ሥዕል አምጣልኝ አለችው።
ከዚህም በኋላ ከቦታው ደርሶ ሥዕሏን ሳይገዛ ተመለሰ፤ በመንገድም ሥዕሏን ለምን አልገዛህም? የሚል ድምጽ ሰምቶ ተመልሶ ገዛ። በጎዳናው እየተመለሰ ሳለም የሚያስፈሩ ወንበዴዎች፤ ኋላም አንበሳ ገጠመው፤ የያዛት ሥዕልም ቃል አውጥታ አዳነችው። አባ ቴዎድሮስም ይህን ድንቅ ተአምር ባየ ግዜ ሥዕሏን ወደ ሀገሩ ሊወስዳት ወደደ። በሌላ ከተማም አድርጎ ሊሄድ መርከብ ተሳፈረ።
በመርከቧ ሳለም ታላቅ ነፋስ ተነስቶ አቅጣጫውን አስቀይሮ ወደ ጸዴንያ ወሰደው። ኋላም ቢመሽበት ማርታ ቤት ሄደ እራሱን ግን አልገለጠም። በማግስቱም ተሰውሮ ከከተማው ሊወጣ ቢሞክር መውጫው ጠፍቶት ሲዞር ውሎ ተመለሰ። እንዲህም እያለ ሶስት ቀን ሆነው። ማርታም ይህን ተመልክታ ምን እንደሆነ ጠየቀችው። እርሱም ሁሉንም ነገራት።
በኋላም የመነኩሴውን እጅና እግር ስማ ሥዕሏን ተቀበለች። በታላቅ ክብርም አስቀመጠቻት። ያም መነኩሴ እስከሚሞትበት ቀን ድረስ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገለ ኖረ።
የእመቤታችን በረከት ይደርብን! 🙏🙏🙏
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ:- መጽሐፈ ስንክሳር
@ewuntegna