🚫 ጥምር የመጅሊስ አመራሮች ምን እየሰሩ ነው ?
ከአሕባሽና ሱፍይ ጋር የተደመሩት ኢኽዋንና ሙመዪዓዎች የመጅሊስ ወንበር ላይ ሲፈናጠጡ ለእስልምናና ሙስሊሞች እንደሚሰሩ ሲደሰኩሩ ሰፊሁ ህብረተሰብ በሐሴት ተሞልቶ ነበር ። ደስታቸውን በተለያየ መንገድ ሲገልፁ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው ። በተለይ የኢኽዋን የእንጀራ ልጆች የሆኑት ነሲሐዎች ደስታቸውን የገለፁበት መንገድ የሚገርም ነበር ።
የተውሒድና ሱና የበላይነት የሚረጋገጥበት እድል እንተገኘ በማስመሰል በዚህ ያልተደሰተ ሙናፊቅ ነው እስከማለት የተደረሰበት ንቅናቄ ተደርጓል ። እንዳይፈረድባቸው የእንጀራ አባቶቻቸው በስሜት ስካር ውስጥ ሆነው " እንግዲህ እድሉ መጥቶልናል አሁን ያገኘነው እድል ሙሳም ቢመጡ ፣ ዒሳም ቢመጡ ፣ ነብዩና ሙሐመድም ቢመጡ ይህን እድል …… " አናገኘውም ነበር በሚል መሀላ ሲደረድሩ ከዛሬ ጀምሮ ከናንተ ከኮሚቴዬች አንስቶ ሱፍይ ፣ ሰለፍይ ፣ ኢኽዋንይ የሚለውን መስማት አንፈልግም እኛ የኢትዮዽያ ሙስሊሞች ነን ሲሉ መስማታቸው እነርሱንም አስክሯቸው ሊሆን ይችላል ።
የኢኽዋን መሪዮች የመጅሊሱን ወንበር ገና ከመፈናጠጣቸው የፈለገ መውሊድ ያውጣ የፈለገ ጫት ይቃም ብለው በአደባባይ በማወጅ አላማቸውና ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ሲገልፁ የስልጣን ፍርፋሬ የደረሳቸው ነሲሐዎች ምን እንደተሰማቸው ራሳቸው ይወቁ ። በአብዛኛው ምስኪን ተስፋ ላይ ግን ውሃ ነበር የቸለሱበት ። ራሱን እንዲጠይቅም አደረጉት ። ነገር ግን ማን ምን ሊያመጣ ዋናውን ስልጣን የተቆጣጠረው የኢኽዋን አንጃ ስልጣኑን ለማቆየት ኡማውን ቀብር አምላኪና ስሜቱን ተከታይ ማድረግ እንዳለበት ስለሚያውቅ ይህን ወደ መተግበር ገባ ።
አመራሮቹ የተውሒድ ዳዒ የሚባል ነገር መስማት አንፈልግም አሉ ። መጀመሪያውኑ እንደገለፁት አሕባሽ ፣ ሱፍይ ፣ ኢኽዋንይ የሚል ድምፅ ማጥፋት ዋና ተግባራቸው ሆነ ። የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል ስሜት ይህን እድል ተጠቅመው የነሲሓ ርዝራዦች ከመጅሊስ ባገኙት የስልጣን ፍርፋሬ ሰለፍዮችን ማፈናቀልና ማባረር ዋነኛው ስራቸው አድርገውታል ።
በአሁኑ ሳአት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ አካባቢ ፣ በስልጤ ዞን ፣ በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ፣ በስብጥር ከላይ እስከታች የተቀመጡ የመጅሊስ አመራሮች በጣም አሳፋሪ በሆነ መልኩ ኢኽዋኖችና ነሲሓዎች ከአሕባሽና ሱፍዮች ጋር በመሆን በተለያየ የመንግስት ተቋማት ላይ ያሉ አመራሮችን መጠቀሚያ በማድረግ የሕብረተሰቡን ህገ መንግስታዊ መብት በመርገጥና በመጣስ በሀይል መስጂዶችን መንጠቅና ኢማሞችንና ኡስታዞችን ማፈናቀልና ማባረር ይህን የሚቋወም ኮሚቴም ሆነ የሕብረተሰብ አካል ካለ ማሰር ግንባር ቀደም ተግባር እንዲሆን አድርገዋል ።
በተለይ በተጠቀሱት አካባቢ ላይ ያሉ የመንግስት ተቋም አመራሮች የተጣለባቸውን ህገመንግስታዊ አደራ ወደ ጎን በማለት ስልጣንን ለግል ስሜትና አመለካከት ማስፈፀሚያ እያደረጉ ይገኛሉ ። የሚገርመው የዚህ አይነት አፈናና የመብት ጥሰት በብልፅግና ዘመን ላይ መሆኑ ነው ።
በኢሀዲግ ዘመን የፀደቀው ህገ መንግስት አይደለም የህዝብ የግለሰብም የእምነት ነፃነት ይረጋገጣል የሚል ነው ። እንደሚታወቀው በኢሀዲግ ዘመነ መንግስት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የማይፈልገውን አመለካከትና እምነት በመጅሊስ አማካይነት በመጫን ተግባራዊነቱ ትላልቅ የመንግስት ተቋማቶች ያስፈፅሙ ነበር ።
የህገ መንግስቱ የዜጎች መብት የሚያትቱ ህይወት አጥተው ወረቀት ላይ የነበሩ ቃላቶችን እንባ የሚያብስም ሆነ የህዝቡን ጩኸት የሚሰማ አልነበረም ።
የዶ/ር አብይ የብልፅግና ዘመን ሲቀየር ግን ሁሉም እነዚህ ህይወት አልባ ሆነው ወረቀት ላይ የቀሩ መብቶች ህይወት ዘርተው እውን እንደሚሆኑ ባለ ሙሉ ተስፋ ነበር ። ነገር ግን በየደረጃው ያሉ የኢሀዲግን ጃኬት አውልቀው የብልፅግና ጃኬት ያጠለቁ የህዝብን መብት ማክበር የሚለውን መርሕ ያልተቀበሉ አመራሮች አሁንም ተመሳሳይ ተግባር እየፈፀሙ ይገኛሉ ።
አብዛኛዎች ከላይ እስከታች በመንግሰት መዋቅር ያሉት አመራሮች ሀገሪቷንና ሕዝቦቿን እያስተዳደሩ ያሉት በህገ መንግስቱ ሳይሆን ከመጅሊስ አመራሮች በሚመጡ መመሪያዎችና ደንቦች ይመስላል ። ‼
የትኛውም የመንግስት አመራር በየትኛውም ቢሮ ወንበር ላይ ሲቀመጥ የግል እምነቱን አመለካከቱንና ስሜቱን ከቢሮ በራፍ ውጪ አስቀምጦ ሁሉንም ህዝብ ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት መብቱን እንዲያገኝና ግዴታውን እንዲወጣ በማድረግ ማገልገል ይኖርበት ነበር ። ነገር ግን ይህ የሚታሰብ አይመስልም ። አብዛኛው በሀላፊነት ቦታ የተቀመጡ አመራሮች ማን ይጠይቀኛል የፈለኩትን መስራት መብቴ ነው የሚሉ ይመስላሉ ።
በተለይ የፀጥታ አካላት ከማንም በላይ የሀገርና ህዝብ አደራ የተሸከሙ ከመሆናቸው አንፃር የሀገርና የህዝብን ሰላም በማስጠበቅ ፍትህን ማስፈን አላማቸው አድርገው ሊንቀሳቀሱ ይገባል ። የሚያሳዝነው ግን በተጠቀሱት አካባቢዮች በሚደርሰው የዜጎች መብት ረገጣ ድራማና ተውኔት ላይ አብዛኛዎች የድራማና ተውኔቱ ገፀ ባህሪ ጥቂቶች ደግሞ የድራማው ደራሲ ሆነው እያየን ነው ።
በተለያዩ አካባቢዮች እየሆነ ያለው ይህ ነው ። ሰላማዊ የሆኑ መስጂዶችና ጀማዓዎች ላይ ችግር አለ የሚል ድራማ እየሰሩ ለምን የሚልን ሰብስበው ማሰር ምን ይሉታል ። የህግ አካል ችግር አለ ካለ የመጀመሪያው እርምጃ በሰከነ ሁኔታ ነገሮቹን ማጣራትና መለየት ነበር የሚያስፈልገው ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጣርተን ነው የምናስረው አስረን አናጣራም ሲሉ ያልተደመመ አልነበረም ። ይህ ማለት እሳቸው በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች እንዲሁም የሆነ ቀበሌ ላይ ወርደው ይፈፅሙታል ሳይሆን እሳቸው የሚመሩት ፓርቲ መርህ ተብሎ ስለሚታመን ነው ። በመሆኑም በየደረጃው ያሉ የፀጥታ ሀይሎች ይህን መርህ ተከትለው ይሰራሉ የሚል አንድምታ ስለተወሰደ ነው ቃሉን ሁሉም በአግራሞት የተቀበለው ።
ለመሆኑ የመጅሊስ አመራሮች እንዳሉትም የሀገር መሪዮች ናቸው ወይስ የአንድ የሌሎችን መብት መከልከል የማይችል ተቋም መሪዮች ? የአሁኑ ተግባራቸው ንግግራቸውን እውነት ነው እንዴ እንዲባል የሚያደርግ ነው ። ከክልል ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ አንዳንድ ተቋማትን ህገ መንግስቱን በተቃረነ መልኩ በደብዳቤ ሲያዙና ተፈፃሚ እንዲሆን ሲያስደርጉ እየታየ ስለሆነ አንድ ሊባሉ ይገባል ። በልካቸው እንዲቆሙ ካልተደረገ ሀገሪቷን እየመራ ያለውን ፓርቲ ገፅታ የሚያበላሽ ተግባር እየፈፀሙ መቀጠላቸው አይቀርም ።
ለማንኛውም የሀገራችን ሙስሊሞች ባጠቃላይ ሰለፍዮች በተለይ የመጅሊስ አመራሮች ተውሒድና ሱናን የበላይ ያደርጋሉ ብላችሁ እንዳትጠብቁ ። ይልቁንም ትልቁ ጠላታቸው አድርገው የያዙት የተውሒድ ዳዕዋና የተውሒድ ዱዓቶችን ነው ።
ከተወሰነ ማስተካከያ ጋር በድጋሚ የተለቀቀ ወቅታዊ ማስገንዘቢያ ።
https://t.me/bahruteka