ከአንዳንድ የመንግሥት ተሽከርካሪዎችና አሽከርካሪዎች የትራፊክ ደንብ ጥሰት እንቅስቃሴ ምን እንማር?
ከመሠረት ሚድያ ተከታታይ የተላከ
በግሌ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከወትሮው የተለየና መልካም ምሳሌነት የጎደለው የመንግሥት ባለሥልጣናትና የጸጥታ ኃይሎች ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ እያስተዋልኩ ነው፡፡ በአነስተኛ ቁጥርና መጠን ሊኖሩ ቢችሉም ተመሳሳይ ድርጊቶች በዘመነ ደርግም ይሁን በኢህአዴግ ወቅት ብዙ አልታዘብኩም፡፡
አሁን ግን ህጋዊ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህ ድርጊት የሚታየው የመንግሥትን ተሽከርካሪዎች በሚያሽከረክሩ መለስተኛ ባለሥልጣናት ወይም ሾፌሮችና ፖሊስንና መከላከያን በመሳሰሉት ነው፡፡ ኮድ 3 የተለጠፈላቸው ተሽከርካሪዎችም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አልፎ አልፎ አይቻለሁ፡፡
ተሽከርካሪ እንዲቆም የሚያዘውን የትራፊክ መብራት ጥሰው ሲሄዱ ጠያቂ የላቸውም፤ በአንድ የጉዞ መስመር ላይ ሶስተኛና አራተኛ ደርበው መጥተው ቆርጠው በግድ ወደ መስመር ለመግባት እየታገሉ የትራፊክ ፍሰቱን ሲያስተጓጉሉ ሃይ የሚላቸው የለም፡፡
በርካታ ተሽከርካሪዎች እጅግ እስኪገርመኝ ድረስ፣ በተቃራኒ መስመር የአደጋ ጊዜ መብራት (hazard light) በማብራት ወይም ሳያበሩ ከፍተኛና መለስተኛ የሕዝብ ተሽከርካሪዎች ማለትም ለምሳሌ እንደ የከተማና ሃገር አቋራጭ አውቶቡሶችና መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻዎች (ሃይገር፣ ቅጥቅጥ) ወዘተ የተፈቀደ የቀኝ መስመር ያለ ከልካይ እየተጋፉ ሲያሽከረክሩ ሃይ ባይ ያላቸው አልመሰለኝም፡፡ ከቤታቸው አርፍደው ተነስተው ከኋላ መጥተው ቀድመው መሄድ ይፈልጋሉ፡፡
ለምን እንደኛ እየተንፏቀቁ ይሂዱ? የመንግሥት ታርጋ ናቸዋ! እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች የሚከናወኑት በትራፊክ ፖሊሶች እይታ ውስጥ መሆኑ ነው፤ ማንም ምንም አይላቸውም፡፡ አስቁሞ ‘ማነህ’? ‘ወዴት ነህ’? ‘ምክንያትህስ’? የሚለው የትራፊክ ፖሊስ አላየሁም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊቶች በተለይም በሥራ መግቢያና መውጫ ሰአቶች ላይ ከፍተኛ ነው፡፡
የከተማዋ ትራፊክ ፖሊስ ለአንገብጋቢ ሥራ ወይም በልዩ ሁኔታ ፈቃድ የተሰጣቸውን ተሽከርካሪዎች የሚያስተናግድበት አሠራር እንዳለው አውቃለሁ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ህጋዊ አሠራር ላይ ቅሬታ የለኝም፡፡ ግን ያሰኘው የመንግሥት ተሽከርካሪ እንደልቡ መብራት እየጣሰና ለሌሎች ለሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የተፈቀደ መንገድ በፍጹም ባለመብትነት መጠቀም ማለት ትርጉሙ ምንድነው?
እውነት ለመናገር የመንግሥት ታርጋ የለጠፈ ተሽከርካሪ እንደ ሲኖ ትራክ መፍራትና መራቅ እየጀመርን ነው (ቢያንስ እኔ እየጀመርኩ ነው) ምክንያቱም ብዙ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች የሚያሽከረክሩ ግለሸቦች መጥፎ የማሽከርከር ሥነ-ምግባር ምሳሌ እየሆኑና በማን አለብኝነት የሚያሽከረክሩበት ከተማ ውስጥ እየኖርን ነውና፡፡
እኔ በበኩሌ ድርጊቱ የመንግሥትን ሥልጣን ከለላ በማድረግ አንዳንድ ግለሰቦች የሚፈጽሙት ተግባር እንጂ በህግ አግባብ የተሰጣቸው ተገቢ መብት አልመሰለኝም፡፡ እነዚህ እየገለጽኳቸው ያለኋቸው ሰዎች እኮ ትልልቅ የደህንነት ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮችና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች አይደሉም፡፡ እነሱንማ ያለጥያቄ እናሳልፋለን ምክንያቱም ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፤ በእርግጥም ከኛ ጋር ተጋፍተው ይሂዱ ሊባል አይችልም፡፡ የምናወራው ስለ በአንድ የመንግሥት ተቋም ክፍል ወይም መምሪያ/ዳይሬክቶሬት ኃላፊ ወይም ተሽከርካሪውን ለማሽከርከር ስለ ተመደበ ሾፌር ሊሆን ይችላል፡፡
በነገራችን ላይ ተሽከርካሪዎቹ የተገዙትም ሆነ የኃላፊዎቹም ይሁን የሾፌሮቹ ደመወዝ ከኛ ከህዝቡ በታክስ መልክ የተሰበሰበና እኛ የምንከፍለው ሳይሆን እነሱ እየከፈሉን ስላለ ‘በሁሉም ነገር ቅድሚያ ለኛ’ የሚል መልእክት እያስተላለፉልን ይመስላል፡፡
የምንፈልገውን መንግሥት የመምረጡ መብትም የኛ የዜጎች እንጂ በጉልበት ወደ ሥልጣን በመጣ ወታደራዊ መንግሥት እየተመራን አይደለንምና ባለሥልጣናቱ ወይም ተሽከርካሪዎቻቸውን የሚዘውሩ ሾፌሮቻቸውን አደብ ሊያስይዙልን ይገባል፡፡
አንድ ሰው ተነስቶ ይህ የትራፊክ ፖሊሶቹ ችግር ነው ሊል ይችላል፡፡ እኔ በበኩሌ አልስማማም ምክንያቱም ትራፊኮቹ እኮ ቤተሰብ አላቸው፣ ዝም ብሎ ከማንም ጋር መጋፈጥ አይፈልጉም እናም ልፈርድባቸው አልችልም፤ በአለቆቻቸው በኩል ሊሚጣባቸው የሚችለውን ጣጣ በመስጋት ወይም በርካታ ህገወጦች ስላሉ በመሰላቸት ሊሆን ይችላል፡፡ እነሱ የማይፈሩት እኛን ‘ተራዎቹን’ መቅጣት ነው፣ ምን ያርጉ?
እርግጠኛ አይደለሁምና አሉባልታ እንዳይመስልብኝ እንጂ ትራፊኮቹም ቢሆኑ ብዙ አሽከርካሪ በቀጣና ባልቀጣ መካከል የጥቅማ ጥቅም ልዩነቶች አሉ ሲባል ደጋግሜ ሰምቻለሁ፣ የትራፊክ ቅጣት መጠን ከአንድ ሰው ደመወዝ በላይ እንዲሆን መደረጉን ሳንክድ፤ ያውም ‘በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ’ እንደሚባለው እየናረ ባለ የገበያ ሁኔታ፡፡
በጥቅሉ እያየን ካለነው የመንገድ ላይ ሥርዓት አልበኝነት ምን ልንማር እንችላለን? መንግሥት ህግ ከማስጠበቅ አንጻር ትልቅ ኃላፊነት ከህዝብ የተቀበለ እንደመሆኑ፣ ይህን በከተማዪቱ ውስጥ በዋናነት እራሱ በሾማቸው አንዳንድ አነስተኛ ባለሥልጣናትና ኮድ 3 እና 4 አሽከርካሪዎች ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል እላለሁ፡፡
አመሰግናለሁ!
@MeseretMedia