+ከአእላፋት ማግስት+
Credit:ዲ/ን ዮሐንስ ጌታቸው (
@yohannes_getachew1)
''ይሄንስእል እያመለክሽ ነው ሳታገቢ የቆየሽው በጌታ በእየሱስ ስም መንፈስሽን ወጋሁት''
እናቴ ናት በጠዋት እንዲህ የምትለው። አሁንማ ገና እየደረሰ በመሆኑ፥ አእላፋት ዝማሬ ብቻ ሆኗል ወሬው እሱ ይረብሻታል።
ስለ እናቴ ትንሽ ላውራቹህ...
ኤልሳትባላለች። ሲበዛ ተጫዋች፥ ረጅም፥ በጣም ቀይ፥ ስትስቅ ጥርሷ የሚያምር፥ በዛ ላይ ዲምፕል ያላት ውብ ናት። አባቴ ደግሞ ሱራፌል ይባላል፤ ዲያቆን ነበር። በእርግጥ እኔ 16 አመቴ እያለ ነው የሞተው። ሰዎች ስለ እርሱ አውርተው አይጠግቡም። ሰው ቀና ብሎ የማያይ፥ ትንሽ ትልቁን አክባሪ፥ ጸሎተኛ ነበር ፤ መምህሩ ሲቀሩ እርሱ ነበር ጉባኤ ዘርግቶ የሚያስተምረው። ሁሉም ነበር የሚወደው። እኔን ራሱ ውዳሴ ማርያም፥ ዳዊት፥ ቅዳሴ፥ ሰዓታት አስተምሮብኛል። '
'ሰበኔ...ሴት ሆንሽብኝ እንጂ አንቺን ዲያቆን ነበር የማደርግሽ'' የሁል ጊዜ ንግግሩ ነበር።
እናቴ አባቴ በእግዚአብሔር ላይ ያለው መተማመን ይገርማታል። እኔ ልክ 15 አመት ሲሆነኝ አባቴ በጠና ታመመ። የሳንባ ካንሰር ያዘው። ከቤት መውጣት ከበደው፤ ቀኑን ሙሉ የሚያሳልፈው አልጋ ላይ መጽሐፈ መነኮሳትን እያነበበ ነበር። ትንሽ ህመሙ ባስ ሲልበት ደግሞ መጽሐፉን ደረቱ ላይ አድርጎ ለሰአታት መተንፈስ የከብደው ነበር። ከእርሱ ህመም በኋላ ቤታችን ውስጥ ሳቅ የሚባል ጠፋ። እናቴ ቀይ ፊቷን ማድያት ወረሰው።
.......የሆነማክሰኞ ቀን ጠዋት ላይ ''ኡኡኡኡኡኡኡኡ'' የሚል ጩኸት ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ። እናቴ ነበረች። ብርድ ልብሱን ከራሴ ላይ በስርአት ሳላወልቅ ሮጥኩኝ። ኤልሲ አባቴን አቅፋ ፥-
"ጌታዬ ጉድ አታድረገኝ ባክህ ጉድ አታድርገኝ"
"እማ አባቴ ምን ሆነ?"......እምባዬከየት እንደመጣ አላውቅም። ፊቴ ርሷል...
"የልጀነትፍቅሬ ኧረ ተው" ትላለች።
"እማ አባቴ ምን ሆኗል?!"
"ጉድአረከኝ!ብቻዬን ለማን ጥለከኝ!ኧረ ያላንተ አይሆንልኝም!ኧረ ጉዴ ኧረ ጉዴ ኧረ ጉዴ"
ጩኸታችንን የሰሙ ጎረቤቶቻችን ቤታችንን ሞሉት። በአንዴ ግማሹ ቲቪ ይሸፍናል፥ ግማሹ ስለ ድንኳን ያወራል......ራሴንሳትኩ፤ ስነቃ ቀብር ሊሄዱ ህዝብ መጥቷል። ቤቱ ውጪው ግጥም ብሏል። ያ ሁሉ ህዝብ አንድ አባቴን አልሆን አለኝ.....
አባቴካረፈ ጊዜ ጀምሮ ቤታችን የማይቀሩ የማይቀሩ 3 ሰዎች ነበሩ። እነዚህ የእናቴ የስራ ባልደረቦች ታዲያ በመጡ ቁጥር ለእናቴ እንፀልይልሽ ብለዋት ነው የሚሄዱት፤ የሆነ ቀን ላይ ከታናናሾቼ ጋር ጸሎት እያደረግን "ከዛሬ ጀምሮ የዚህ ቤት ሃይማኖት ተቀይሯል!"አለችን።
"ወደምን?"አልን
"ጌታን ተቀብለናል!ነገ ትጠመቃላችሁ። አቁሙ አሁን!"
"እንዴኤልሲ!እኛ እኮ ልጅ እያለን ተጠምቀናል"
"አንቺ ልጅ!ተናገርኩ በቃ!"
"አልቀይርም!አባቴ ያስተማረኝ ያወረሰኝ ነው፤ አልቀይርም!"አልኩ።
ኤልሲም መልሳ "ነው?ከሆነ ከቤቴ ውጪ!እናንተም እንደዛ ነው?
ታናሽእህቴም አዎ አለች።
"ውጡ!ችግር እና ረሃብ ሲፈራረቅባችሁ ትመጡ የለ!"አለችን በቁጣ።
ስልኬን አንስቼ ለአያቴ ደወልኩ። አያቴ ብቻዋን የምትኖር፥ በጣም ትልቅ ጊቢ ያላት፥ እሱ ላይ ወደ 20 ምናምን ቤት ሰርታ የምታከራይ ሴት ናት። ስደውል ኑ ኧረ ኑ አለች
.........እናቴ ሃይማኖቷን ቀየረች። ሁሉንም እኛ ክፍል የነበረ ስእለ አድኅኖ አውጥታ አቃጠለች። የአባቴን ግን ከበዳት። የእርሱን ዳዊት፥ የጸሎት መጻሕፍት፥ ሁሉን ነገሩን በአንድ ላይ አድርጋ አንድ ክፍል ውስጥ ቆለፈችበት። እኛም አያታችን ጋር መኖር ቀጠልን።
---------------------------------------------------
እናቴን ሃይማኖቷን ያስቀየሯት ሰዎች Theology እንድትማር አደረጉና ፓስተር ሆነች ።
ዛሬ...
"እሺባክሽ...አእላፋት ምናምን እያላችሁ ነው ደግሞ በነጭ ልብስ ጣኦት ልታመልኩ"
"ተይ እንጂ እማዬ...የማይሆን አትናገሪ። ለምን ዛሬ አብረን አንሄድም?"
"ማን?እኔ?ሆሆሆሆሆሆሆሆ...ሥራ አልፈታሁም"
"ምን ችግር አለው?ከደበረሽ ቶሎ እንወጣለን።"
"ቆይይይይይ እሄዳለው። የምሄደው ግን እንዴት ልክ እንዳልሆናችሁ ላሳይሽ ነው!"
ሁላችንምለባብሰን ወጣን። በጊዜ ነበር የደረስነው፤ ቦሌ መድኃኔዓለም ሞልቷል። እንደምንም ብለን ፊት ተጠጋን። ዲያቆኑ "እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስ" ይላል። ቁርጥ የአባቴን ድምፅ!ኤልሲ ደነገጠች። አባቴን ያየችው መስሏት ተንጠራርታ ፈለገችው፤ የለም። የሚፀየውን ጸሎት በግእዝም በአማርኛም ስታየው ቆየች። እምባዋ ይፈስ ጀመር። ጸሎቱ ተጠናቆ ነጫጭ የለበሱ ዘማሪያን መድረኩን ሞሉት። መዝሙር ቀጠለ። ቸሩ ሆይ የሚለው መዝሙር ዘማሪዎቹ መዘመር ጀመሩ። የአባቴ የሚወደው መዝሙር ነበር። የሲቃ ድምጽ አውጥታ አለቀሰች። አሳዘነችኝ ደስም አለኝ። መዝሙሩ አለቀ። በአባቶች ብራኬ ተጠናቀቀ። ኤልሲ ሙሉ ሰአት እያለቀሰች ነበር ።
"ኤልሲዬ በቃ አንቺ ሂጂ፥ እኛ እናስቀድሳለን።"
"ልምጣ?"
"የምርሽንነው?"
"አዎልምጣ"
"ነይ" ድንጋጤዬ ያስታውቃል።
ማህሌቱ አልቆ፥ ቅዳሴው አልቆ፥ ቤት ገባን። እኛ ቤት ከመጣሁ 10 አመት አልፎኝ ነበር። ያው ነው፥ ምንም አልተቀየረም። እናቴ ሮጣ ጸሎት ቤት ገባች። ሁሉ ነገሩ አባቴን አባቴን ይላል። ትልቅ የእመቤታችን ምስለ ስዕል ፊት ወድቃ አለቀሰች።
"ሰበኔ አሁን ገባኝ!ልቤ ተሰብሬ ሲያገኙኝ ዓለም ገደል ስትሆንብኝ አግኝተውኝ ነው!ልጆቼ ይቅር በሉኝ!በጎደለኝ በኩል ሲቆሙ ወዳጆች መሰሉኝ ......"
ተቃቅፈንተላቀስን። ምን ተረዳሁ መሰላችሁ?እግዚአብሔር ስራው Mysterious ነው። እንዲህ ነው ብለን Define የማይደረግ። ዛሬ ላይ ቤተሰቤ ሙሉ ሆኗል፤ እናቴም ወደ ክርስትና ለመመለስ ትምህርት ለመማር ከመምህሬ ጋር አገናኝቻለሁ። ከ 10 ዓመት ከብዙ ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር ጸሎቴን ሰማኝ። እጆቼን ከፍ አድርጌ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ...
"የእኔንእምባ ያቆምክ እግዚአብሔር...እምባቸውን ለሚያወጡ ድረስ" ብዬ። "ሰላም ለናፈቁ ሁሉ ሰላም ስጥ። አባቴ የደከሙ ልቦችን አሳርፍ፥ ፈገግታን የናፈቁን ሁሉ ሳቅ አጥግብ፥ ለደስታ የተግደረደሩትን ሁሉ አላምዳቸው ...ባለቀሱበትቦታ እንባቸውን አብስ። ሁሉን ቻይ ሆይ፥ የመዳናቸውን ቀን አታርቅ።"
ዲያቆን ዮሐንስ ጌታቸው (Instagram:-
@yohannes_getachew1)
ጥር1 / 2017
አዲስ አበባ