ኅዳር ፬ /4/
በዚችም ቀን የደማስቆ ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ቶማስ በግብጽና በሶርያ እስላሞች በነገሡ ጊዜ በሰማዕትነት አረፈ።
ይህንንም ቅዱስ ቶማስ ከመምህራኖቻቸው ውስጥ አንድ እስላም በተከራከረው ጊዜ ቅዱስ ቶማስ በረታበት፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማይና ምድርን በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ የፈጠረ አምላክ እንደሆነ በማስረዳት አይሎ ረታው።
ያም እስላም በአፈረ ጊዜ ወደ መኰንናቸው ሒዶ ይህ ክርስቲያናዊ ቶማስ ሃይማኖታችንን ረገመ ብሎ ወነጀለው። መኰንኑም ወደርሱ አስቀርቦ በውኑ ሃይማኖታችንን ትረግማለህን አለው፤ ቅዱሱም መርገምስ ከአፌ አልወጣም ክርስቶስ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ከእርሱም ሕግ በኋላ ሌላ ሕግ እንደማይመጣ አጽንቼ አስረዳሁት እንጂ ብሎ መለሰለት።
መኰንኑም የእኛስ ሕግ ከእግዚአብሔር ነውን ወይስ አይደለም አለው፤ ቅዱሱም ከእግዚአብሔር አይደለም አለው። በዚያንም ጊዜ መኰንኑ ተቆጣ ራሱንም በሰይፍ እንዲቆርጡት አዘዘና ቅድስት ራሱን ቆረጡት። በመንግሥተ ሰማያትም የምስክርነት አክሊልን ተቀበለ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ :- መጽሐፈ ስንክሳር
💚 @ortodoxmezmur 💚
💛 @ortodoxmezmur 💛
❤️ @ortodoxmezmur ❤️