የካቲት ፬ /4/
በዚች ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሐዋርያ የከበረ አጋቦስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ ጌታችን ከመረጣቸውና ይሰብኩ ዘንድ ከመከራው በፊት ከላካቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ ነው።
በጽርሐ ጽዮንም አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋር ስጦታውን ተቀብሏል። እግዚአብሔርም የትንቢትን ሀብት ሰጠው ስለርሱ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደ ተናገረ የቅዱስ ጳውሎስን መታጠቂያ አንሥቶ ራሱ እግሮቹን አሠረባትና የዚችን መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም አይሁድ እንዲህ ያሠሩታል አለ መንፈስ ቅዱስ ብሎ ትንቢት ተናገረ ትንቢቱም ተፈጸመች።
ከዚህም በኋላ ሕይወት በሆነ በወንጌል ትምህርት ሊአስተምር ከሐዋርያት ጋር ወጣ እያስተማረና ቀና የሆነ የእግዚአብሔርን መንገድ እየመራ ብዙ አገሮችን ዞረ ከአይሁድና ከዮናናውያንም ብዙዎችን የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅን ሃይማኖት አስገባቸው በከበረች በክርስትና ጥምቀትም አነፃቸው።
አይሁድም ይዘው በጽኑ አሰቃይተው በድንገይ ወግረው ገደሉት። በዚያንም ጊዜ ከሰማይ ብርሃን ወርዶ በሥጋው ላይ እንደ ምሰሶ ተተከለ ወደ ሰማይም ደርሶ አሕዛብ ሁሉ ወደርሱ ሲመለከቱ ነበር።
እግዚአብሔርም የአንዲት አይሁዳዊት ሴት ልቡናዋን ገለጠላትና ይህ ሰው እውነተኛ ነው አለች። ያን ጊዜም በላይዋ ብርሃን ወረደ እንዲህ ብላ ጮኸች እኔ በቅዱስ አጋቦስ ፈጣሪ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነ በጌታ ኢየሱስ የማምን ክርስቲያን ነኝ እግዚአብሔርንም ከፍ ከፍ እያደረገች ስታመሰግነው በደንጊያ ወገሩዋት ነፍሷንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር
💚 @ortodoxmezmur 💚
💛 @ortodoxmezmur 💛
❤️ @ortodoxmezmur ❤️