የካቲት ፭ /5/
በዚችም ዕለት ተጋዳይ የሆነ አባት ጴጥሮስ የተባለ አባ ብሶይ አረፈ።
እርሱም ከላይኛው ግብጽ አክሚም ከሚባል ከተማ ነው። በጐልማሳነቱም ጊዜ የከፉ ሥራዎችን የሚሠራ ሁኖ ነበር በመብላትና በመጠጣትም ይደሰት ነበር ። እግዚአብሔርም የነፍሱን ድኅነት ሽቶ ጽኑ ደዌ አመጣበትና ለመሞት ተቃረበ።
ነፍሱንም በተመሥጦ አውጥተው የሥቃይ ቦታዎችንም ጥልቅ የሆነች ጕድጓድንም አሳዩት። በዚያም ብሩህ ልብስ የለበሱ ሰዎች አሉ በእጆቻቸውም የሰው በድን ነበረ አራት ክፍል አድርገው ለያዩትና የሰውን ገንዘብ የሚሰርቀውን ሁሉ እንዲህ ያደርጉበታል አሉት። ይህንንም ነገር በሰማ ጊዜ ጮኸ ከልቡም አዝኖ አለቀሰ ከዚህም በኋላ ነፍሱ ተመለሰች ዐይኖቹንም ወደ ሰማይ አቅንቶ ጌታዬና ፈጣሪዬ ከዚህ ደዌ ከአዳንከኝ እኔ ስለ ኃጢአቴ ንስሐ በመግባት በፍጹም ልቡናዬ አመልክሃለሁ ከእንግዲህም ከቶ ለዘላለሙ የሴት ፊት አላይም አለ።
በዚያንም ጊዜ ከደዌው አዳነውና ተነሥቶ ብንዋይ ወደሚባል ገዳም ሔደ መነኰሳቱም ከፈተኑት በኋላ የምንኲስናን ልብስ አለበሱት በግብጽ አገር ሁሉ እስከሚሰማ ታላቅ ተጋድሎን በጾም በጸሎት በመስገድም ተጋደለ ከሁሉ በላይም ከፍ ከፍ አለ ለመነኰሳትም ትምህርት የሚሆኑ የሚጠቅሙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ አንድ ጊዜም እንጀራ ሳይቀምስ ውኃ ሳይጠጣ አንድ ወር ጾመ እንዲህም እየተጋደለ ሠላሳ ስምንት ዓመት ያህል ኖረ።
መላዋንም ሌሊት በጸሎትና በስግደት በመትጋት ቁሞ ያድራል ሰዎች የሚሠሩት ሁሉ ጻድቅም ቢሆን ኃጢአተኛም ቢሆን በፊቱ ግልጥ ሆኖ ይታየዋል። ከዚህም በኋላ ጥቂት ታመመና በሰላም አረፈ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር
💚 @ortodoxmezmur 💚
💛 @ortodoxmezmur 💛
❤️ @ortodoxmezmur ❤️