የካቲት ፮ /6/
በዚችም ቀን ጌታን ሽቱ ለቀባችው ማርያም የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው ። ይችም ቅድስት አስቀድማ ኑሮዋን በዝሙት ያሳለፈች ኃጢአተኛ ነበረች ። እርሷም ጐልማሶችን ወደርሷ ትማርካቸው ዘንድ በየራሱ በሆነ ሽልማትና ጌጥ ትሸለም ነበር።
በአንዲትም ዕለት እንደ ልማድዋ ተሸልማ አጊጣ ሽቱም ተቀብታ ፊቷን በመስታዋት ተመለከተች የጉንጯ ቅላትና ደም ግባቷ የዓይኗም ወገግታና ጥራት ማማሩን አይታ እያደነቀች አንድ ሰዓት ያህል ቆየች ከዚህም በኋላ በጎ ኀሳብ በላይዋ መጣ ሞትንና የዚህን ዓለም ማለፍ አሰበች።
የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስም ኃጢአተኞችን እንደሚቀበልና ኃጢኣትንም እንደሚአስተሰርይ ሰምታ ገንዘቧን ወስዳ የአልባስጥሮስን ሽቱ ገዝታ በስምዖን ዘለምጽ ቤት ለምሳ ተቀምጦ ሳለ ወደ ጌታችን ሔደች።
ከእግሩ በታችም ሰግዳ ያንን ሽቱ ቀባችው እግሮቹን በዕንባዋ አጠበችውና በራስዋ ጠጉር ወለወለችው ጌታችንም የፍቅርዋን ጽናት አይቶ ኃጢኣቷን በደሏን ተወላት የመንግሥት ወንጌልም በሚሰበክበት ይህን ያደረገችውን እንዲአስቡ አዘዘ ። በረከቷም ከእኛ ጋርይኑር ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር
💚 @ortodoxmezmur 💚
💛 @ortodoxmezmur 💛
❤️ @ortodoxmezmur ❤️