ፅጌሬዳ
ክፍል 40
ማታ ላይ የእህቴ ባል ከስራ እስኪመጣ እኛ መለባበስ ጀመርን እሱም ከስራ በዛው ወደቤቱ ገባና ለባብሶ መጣ ።
አለ ወደተባለው ሆቴል አመራን በጠረጴዛ ዙሪያ ቤተሰቡ ተሰብስቦ ቁጭ አለ።
እኔና ማሂ ጎን ለጎን እህቴና ባሏም ጎን ለጎን አባቴና እናቴም ግን ለጎን አቶ ሳሙኤል ከሁላችንም ፊት ለፊት ነገር ብቻቸውን ቁጭ አሉ።
እራታችንን በላን ከዛ ሁሉም የየራሱን መጠጥ አዞ መጠጣት ጀመርን።
ማሂ ሞቅ እያላት ሲመጣ እኔ ላይ መለጣጠፍ ጀመረች።
እናቴም ያባቴ ትከሻ ውስጥ ሽጉጥ አለች እህቴና ባሏ ብቻ እንዲሁ ቁጭ ብለው እኛን ማስተዋል ጀመሩ።
ማሂ እንኳን መጠጥ ጠጥታ እንዲሁም እንባ ይቀድማታል ።
ቁጭ ብለን እየጠጣን አባቷን አየችና ይሄኔኮ ለኔ ብሎ ሳያገባ ሌላ ሴትጋ ሳይሄድ ብቻውን ባይኖር ኖሮ አሁን ብቻውን አይቀመጥም ነበር እሱም ሚያቅፈው ሚስት ይኖረው ነበር ብላ አለቀሰች።
አቶ ሳሙኤልም አብረዋት እንባ እየተናነቃቸው አይ ልጄ አሁን አንቺን በሱ እቅፍ ውስጥ ሳይሽ ካንቺ በላይ እኔ ደስ እንዳለኝ ብታውቂ እንደዚህ አትይም ነበር ልጄ አንቺ ከኔ አልፎ ሌላ ምትደገፊው ትከሻ አገኘሽ ማለት እኔ አገኘሁ ማለት አደል እንዴ አሏት።
ልክ ነህ አባቴ እንዲሁ ሆድ ይብሰኛልኮ አለችና ለቅሶዋን ወደሳቅ ቀየረችው።
ሳቋ ደሞ ለሁሉም ይጋባል ሁላችንም እሷን ተከትለን መሳቅ ጀመርን።
ብቻ ምሽቱ ለኛ ብቻ የተፈጠረ እስኪመስለን ድረስ በደስታ አሳለፍን ሁሉም ሞቅ እያለው ሲመጣ በሆነው ባልሆነው መሳቅ ጀመርን እህቴ ብቻ አልኮል ስለማትጠጣ በኛ ተግባር እየተገረመች ታየናለች።
እስከ ሌሊቱ ድረስ ስንዝናና ስንጠጣ አመሸን ።
ከስንት ሰአት ቡሀላ እራሴን ማጣት እንደጀመርኩ አላቅም እኔና ማሂ እኩል በሚባል ደረጃ ነበር የተቀየርነው።
ወደቤት እንዴት እንደገባን እራሱ አላስታውስም ።
ጠዋት እህቴ ሁላችንንም እየዞረች ቀሰቀሰችንና ለቁርስ እንድንነሳ ነገረችን ማታ ከነባሏ እኛ ቤት ነበር ያደሩት እኔና የእህቴ ባል ሶፋ ላይ ነው ያደርነው የሌሎቹን አላቅም።
ቁርስ ሳይሆን ወሬ ነበር የበላነው ማለት እችላለሁ።
እህቴ የሁላችንንም ጉድ ካባቴና ከአቶ ሳሙኤልጋ እየተጋገዘች ትተርክልን ጀመር።
ከሁሉም በላይ እኔና ማሂ ላይ ነበር ሙድ ሲይዙብን የነበረው።
እህቴ ሳቋን መቆጣጠር እስኪያቅታት ድረስ እየሳቀች ሰው ሁላ ብልጥ ለመሆን ሲሞክር ማታ ጉዳቸው ተዝረከረከ ሰው ሁላ እስኪታዘብ አፈቅርሀለሁ አፈቅርሻለሁ ስትባባሉብን አመሻችሁ አለች።
አቶ ሳሙኤል ቀበል አሉና እኔ ጉዴን መች አውቄ ልጄን እያስታመመልኝ ነው ብዬ ሀሳቤን ጥዬ ከአዲስ አበባ እዚህ እመላለሳለሁ እሱ ለካ ጣጣውን እየጨረሰ ነው አሉ።
እኔ ሁሉንም ቀና ብዬ ለማየት እያፈርኩ አቀርቅሬ ዝም አልኩ።
ደሞ የሷ ይባስ እንጂ አባቴ ሳልነግርህ መቼስ ትረዳኛለህ ምን ያህል እንደማፈቅረው እያለች ያ ሁሉ ሰው በተሰበሰበበት ስትጮህ እኔ አፍሬ ምገባበት እስካጣ ድረስኮ ነው የጨነቀኝ አሉ አቶ ሳሙኤል።
አባቴም በተራው እኔ አንድም ቀን ጠርጥሬ አላቅም ነበር ይቺ መጠጥ ጉዱን አዝረከረከችው እንጂ እንደፈረንጅ ፊልም ሲላላሱብን አመሹኮ የነሱ ሲገርመኝ የኔው ሚስት መራመድ አቅቷት እሷን ተሽክሜ አስገባሁ እናንተ ሆዬ እጅ ለእጅ ተጣብቃችሁ ከተላቀቅን ሞቼ እገኛለሁ አላችሁ።
የልጄ ባል ብቻ ነው ያኮራኝ ጎበዝ የኔ ጀግና እንደዛ ጠጥቶ ንቅንቅ ሳይል እንደማንኛውም ሰው እናንተን እየመራ እስከቤት አመጣችሁ አለን።
እናቴ በተራዋ እየሳቀች እኔኮ ተው አልጠጣም ብዬ ነበር እናንተ እንቢ አላችሁ እንጂ ለማንኛውም ግን እንኳንም ወጣን እንኳንም ጠጣን ይሄ ፍቅር ይፋ ወጣ በምክንያት አለች።
ብቻ ተሳስቀን አንዱ አንዱላይ ሙድ እየያዘ ቁርሳችንን በልተን ጨረስን።
ከዛን ቡሀላ በቃ ቁጭ ብለን እንደቤተሰብ ማውራት ያለብንን እናውራ ከአሁን ቡሀላ ጊዜ ማጥፋት የለም ወደውሳኔ እንግባ አሉ አባቴም ልክ ነው አዎ እስቲ እንመካከር አለ።
ሁላችንም የየራሳችንን ሀሳብ እያነሳን ከተመካከርን ቡሀላ ።
አቶ ሳሙኤል በቃ ናታኔም ከኔጋ ወደ አዲስ አበባ ይሄዳል ትምህርቱን እየተማረ ጎን ለጎን ደሞ ከኔጋ ስራ ይጀምራል 12 ከፍሎ ይፈተንና ከዛ ቡሀላ college ማርኬቲንግ ትማራለህ እስከዛ ከኔጋ ስራ ትሰራለህ ወረቀቱን ከያዝክ ቡሀላ ደሞ ወደ ከፍታ ወደ አስተዳዳሪነት ትመጣለህ ጭንቅላትህ perfect ስለሆነ ምንም እንደማይከብድህ አቀዋለሁ አሉኝ
አይኔን ሳላሽ ተስማማሁ እናቴ እንደዛ ከሆነኮ በድጋሜ ተራርቀን ልንኖር ነው ማለት ነው አለች ቅር እያላት።
አይ እናቴ እንደዛ አደለም ይኸው ምን ያህል ቅርብ እንደሆነ እያየሽ አደል እንዴ ቅዳሜና እሁድ መምጣት እችላለሁ አንቺም እየመጣሽ እስከፈለግሽው ቀን እየቆየሽ መሄድ ትችያለሽ አልኳት።
ለማንኛውም ፈጣሪ የወደደውንና የፈቀደውን ነው የሚያደርገው እሱ ያሳካልህ ልጄ መንገድህ ብቻ ይስተካከል እንጂ ችግር የለውም በቃ አለችኝ።
በነጋታው ተነስተን ሶስተቻንም ወደ አዲስ አበባ መጣን።
ማታ እራታችንን በላልተን ስንጨርስ ማሂን አንቺ ግቢ እኔ እሱን ላወራው እፈልጋለሁ አሏትና ተነስታ ገባች።
ወደ በረንዳው ወጥተን ቁጭ አልን።
ምነው በሰላም ነው የፈለጉኝ አልኳቸው።
አዎ የኔ ልጅ ምን መሰለህ ትናትም ላወራህ አልቻልኩም ነበር አሁን ፍሪ ሰአት ስላለን አንዳንድ ነገሮችን ላውራህ ብዬ ነው።
ምን መሰለህ እኔ እዚህ ምድር ላይ ለመቆየትህ ትልቁ ምክንያት ምንድነው ብትለኝ የልጄ መኖርና መተንፈስ አለማቆሜ ነው ።
እና በየቀኑ የሷን ደስታ ማየት ስትስቅ ስትጫወት ስላላት ህይወት ስታመሰግን ማየት እፈልጋለሁ።
እዚህ ምድር ላይ ደስተኛዋ ሰው እንድትሆንልኝ እፈልጋለሁ ጥሩ አባት ነበረኝ አሁን ደሞ ጥሩ ትዳር ፈጣሪ ሰጠኝ ብላ እንድታመሰግን ነው ምኞቴ።
ጥሩ ባል ስለመሆንህ አልጠራጠርም ግን የሰው ፍፁም የለውም ብቻ ግን አደራ አደራ የምልህ ነገር ቢኖር በቃ ለልጄ ባል ወንድም ዘመድ ሁንላት ።
መቼም ቢሆን ከፊቷ ላይ ፈገግታ ጠፍቶ ማየት አልፈልግም አደራ ናታኔም አደራ አሉኝ።
ሁኔታቸው አስፈራኝ ።
መቼም ቢሆን አላስከፋትም ቃሌ ነው አልኳቸው።
ጥሩ አሁን ይቺን ሳምንት ህጋዊ መንጃ ፍቃድህን እንጨርስና ወረቀቱን በእጅህ ታደርጋለህ።
ድጋሜ ዴሊቬሪ ስራም ሆነ የጋራጅ ስራውን አትሰራም ።
እንደመጀመሪያ የኔ ሹፌር ሆነህ ነው ድርጅቱ ውስጥ ምትቀጠረው ከዛን ቡሀላ አንዳንድ ጉዳዮችን ማስፈፀም ትጀምራለህ ።
ቀስ በቀስ ስራውን እንድታቀውና እንድትለምደው አደርግሀለሁ እኔ ከድሮ ጀምሮ ማሂ ደርሳልኝ ከኔጋ አብራ ትሰራለች እሷ ታስተዳድርልኛለች ብዬ ነበር ምጠብቀው ግን እንደምታየው እሷ ፍላጎት የላትም አሁን ግን አንተን መተካት እችላለሁ ትምህርት ላይም ትኩረት ታደርጋለህ አሉኝ።
እሺ አልኳቸው መልሴ ሁላ አጫጭር ነበር ።
ሌላውና የመጨረሻው ነገር ደሞ ልክ የመንጃ ፍቃዱን ወረቀት እንደጨረስክ ጊዜ ሳታጠፋ ቀለበት ታስርላታለሁ ያልጠበቀችውን ሰርፕራይዝ እናዘጋጅላታለን ከዛን ቡሀላ የሰርጋችሁን ነገር እራሳችሁ ትወስናላችሁ ግን አሁን ቀለበት ሳታስሩ ዝም ብላችሁ ጓደኛሞች ሆናችሁ አንድ ቤት መኖር ትንሽ ይከብዳል አሉኝ።
በጣም ደስ ይለኛል የኔም ምኞት ነው አልኳቸው።
በቃ ጥሩ ደና ደር በቃ ወደመኝታችን እንሂድ አሉኝና ተነስተው ገቡ።
እንዳሉትም ያቺን ሳምንት ወረቀቱን ለማስጨረስ ስንሯሯጥ ቆየንና ተሳካልን ከዛን በመቀጠል ድርጅታቸው ውስጥ እንደሹፌራቸው ሆኜ ተቀጠርኩ።