የትራምፕ የጤና ፖሊሲ እርምጃዎች ምንድን ናቸው? የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስልጣን እንደተቆናጠጡ ከፈረሟቸው ፕሬዝዳንታዊ ትእዛዛት መካከል ጤናን የሚመለከቱ ስር ነቀል ፖሊሲዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ሆነዋል። አሜሪካን ከአለም ጤና ድርጅት (WHO) ከማስወጣት እስከ ቁልፍ የጤና ኤጀንሲዎች እስከ መዝጋት ድረስ ሰፊ ክርክር አስነስተዋል።
1️⃣ ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መውጣት፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ለመውጣት ሂደቱን የጀመሩት ድርጅቱ የዓለም ጤና ጉዳዮችን በተመለከተ ያለውን ቸልተኝነት በመንቀፍ ነው። ትራምፕ የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት አፋጣኝ እና ግልጽ ስራ ባለመስራቱ ለቫይረሱ መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርጓል ብሎ ያምናል። የቻይና ፖለቲካዊ ጣልጋ ገብነት አለበትም ሲሉ ከሰዋል።
ይህ እርምጃ የአለም አቀፋዊ የበሽታ ልየታ፣ ክትትል እና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓቶችን ያዳክማል በሚል ስጋት ፈጥሯል።
2️⃣ የአሜሪካ የጤና ተቋማትን ኮሚኒኬሽን መዝጋት፡
የአሜሪካ በሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማእከል እና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንን ጨምሮ ሁሉም የፌደራል ጤና ኤጀንሲዎች የውጭ ግንኙነቶችን እንዲያቆሙ ትእዛዝ ተላልፏል። ይህ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ መመሪያ ሲሆን አዲስ የበሽታ ወረርሽኝ ሲነሳ ወቅታዊ መረጃዎችን ለተቀረው አለም መንግስታትና ህዝብ ለማሰራጨት መዘግየት ይፈጥራል የሚል ስጋትን ጭሯል።
3️⃣ የዲኢአይ (Diversity, Equity, and Inclusion, DEI) መታገድ
ይህ ፕሮግራም በአሜሪካ ተቋማት ውስጥ አካታችነት፣ እኩልነት እና ፍትሃዊነትን ለማስፈን የወጣ ፕሮግራም ሲሆን ትራምፕ እንዲቆም ፈርሟል። ይህ እርምጃ በተቋማት ስራ ውስጥ ፍትሃዊ አካታችነት እና እኩልነት ለማስፈን የሚደረግውን ጥረት ወደኋላ ሊመልስ ይችላል ሲሉ ብዙዎች ተችተዋል።
4️⃣ የሮበርት ኬኔዲ የጤና ሚኒስቴር ሆኖ መሾም፡
ይህ ሰው በክትባት እና አንዳንድ የጤና አሰጣጥ ስርአቶች ላይ አወዛጋቢ አቋም እንዳለው ስለሚታዎቅ ስራዉን እንዴት ይመራው ይሆን የሚል የሰላ ክርክር አስነስቷል።
ለታዳጊ ሃገራት ጤና ምን ተጽእኖ ያመጣል?
እነዚህ እርምጃዎች የአሜሪካ መንግስት በጤና ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያሳየ መሆኑን አመላካች ናቸው። ይህ ፖሊሲ በአሜሪካ ድጋፍ የሚሰሩ በርካታ የጤና ዘርፎችን፣ ህክምናዎችና እና ዓለም አቀፍ የጤና ትብብር ስራዎች ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል ሲሉ የጤና ባለሙያዎች እና ተሟጋቾች ስጋታቸውን አንጸባርቀዋል።
ለብዙ ታዳጊ ሃገራት የጤና ወጪ ከፍተኛውን ድጋፍ የምታደርገው አሜሪካ ናት። ስለሆነም የዚህ ድጋፍ መቀነስ አስፈላጊ የጤና ፕሮግራሞች የገንዘብ እጥረት ያጋጥማቸዋል። ለምሳሌ
👉 የክትባት ዘመቻዎች፣
👉 ኤችአይቪ/ኤድስ፣
👉 ቲቢ እና
👉 ወባን መከላከል
የመሳሰሉት ፕሮግራሞች በአሜሪካ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ናቸው። የአሜሪካ ገንዘብ ድጎማ ከቀነሰ እነዚህ ወሳኝ የጤና አገልግሎቶች አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ።
እነዚህ ፖሊሲዎች
በኢትዮጵያ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ምን አንድምታ ይኖራቸዋል ብለው ያስባሉ? ሃሳብዎትን ያጋሩን!
ቴሌግራም
@HealthifyEthiopiaYouTube
https://www.youtube.com/@HealthifyEthiopia