በሰባዎቹ መጨረሻና በሰማንያዎቹ መጀመሪያ ካገኘናቸው ከዋክብት ድምፃዊያን አንዱ ነው ፤ ፀጋዬ እሸቱ የተወለደው በአዲስ አበባ ከአባቱ እሸቱ በቀለና ከእናቱ ከ ወ/ሮ እህታገኝ ሾተል በአዲስ አበባ ጥይት ቤት አካባቢ ነው።
በተቀሸሩ ዜማዎቹ በተመረጡ ግጥሞቹ ልዩ ቀለም ባለው ድምፁና በተለያዩ ታሪኮች በልዩ ልዩ የምናውቀው ፀግሽ አራት ወጥ አዳዲስ አልበሞችንና ወደ ሰባት የሚጠጉ ከብዙ ድምፃዊያን ጋር የተሰበሰቡ አልበሞችን ሰርቷል ፤ የመጀመሪያ አልበሙ የወጣው በ 1980 ሲሆን ፤ ቀጣዮቹ ደግሞ በ 1983,1987 እና 1995 ዓ.ም ናቸው።
ከዛ በኋላም በቅርቡ የቀደሙ ስራዎቹን በድጋሚ የተጫወተበት አልበም ሰቶናል ፤ በፊትም የሰርግ ስራዎችን ይሰራ የነበረ ቢሆንም በ 1999 ዓ.ም የሰርግ ጨዋታዎች ያሉበትን አንድ አልበም ካሳተመ በኋላ ግን ፋታ በማይሰጥ በሰርግ የዘፈን ስራዎች ውስጥ ተጠምዷል ማለት ይቻላል።
የመጀመሪያዎቹ ሶስት አልበሞቹ ዛሬ ድረስ የፀጋዬን ስም የተሸከሙ አምድ የሆኑ ስራዎች ናቸው ማለት ማጋነን አይሆንም።
ለመጀመሪያ ጊዜ የሙዚቃ ቡድን አባል የሆነው በ 1969 "የከፍተኛ አስራ ስድስት የኪነት ቡድን" እየተባለ ይጠራ በነበረው የሙዚቃ ቡድን ነበር ፤ የከፍተኛ አስራ ስድስት የኪነት ቡድን አባል ሆኖ የመጀመሪያ መተዋወቂያ ዘፈኑም "አይኖሩም የማያነቡ አይኖች" የተሰኘው ዜማ ነበር።
በ 1976 ዓ.ም የህንፃ ኮንስትራክሽን ባንድ አባልና የመስሪያ ቤቱ ክለርክ ወይንም ፀሀፊ ሆኖ ተቀጥሮ ነበር።
ፀጋዬ ለ "አሞራው" ባንድ መመስረት ምክንያት ከመሆኑም በላይ አሁንም ድረስ በ 1979 ዓ.ም የተመሰረተው የ "አክሱማይት" ባንድ መስራችና ባለቤትም ነው።
ፀግሽ ባለ ትዳር ሲሆን በትዳሩም አንድ ሴት እና አንድ ወንድ ልጅ አፍርቷል ፤ ሴቷ የልቤ ፀጋዬ እና ወንዱ ባምላክ ፀጋዬ ፤ ባለቤቱ ዘነበች ጌታሁን በሀገር ፍቅር ትያትር የዘመናዊ ዳንስ ትደንስ ነበር ፤ አሁን ላይ ደግሞ የዳንስ አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች።
በብዞቻችን ህይወት ውስጥ የራሱ የሆነ ድርሻ ያለውና የተወደዱ ዜማዎቹን የምናስታውስለት ውዱ ድምፃዊ ፀግሽ እናት ሀገሩ እርዳታ ባስፈለጋት ሰዓት የሚያስፈልጋትን እርዳታ በተቻለውና ባለው አቅም ከማገዝ ወደኋላ ብሎም አያውቅም ፤ በብዙ በጎ አድራጎት ስራዎች በመስራትና በመካፈል ብዙ አስተዋፅኦ ያደረገ ቢሆንም ከካሜራ በስተጀርባ ስለሆነ ተግባሩ በቅርብ ካሉት ወዳጆቹ በስተቀር ብዙ ሰዎች የማያቁት ደስ የሚል ባህሪና ትልቅ ስብዕና ያለው ታላቅ ድምፃዊ ነው።
📢
@TsegayeEshetu