🎤🌼ድምፀ ተዋህዶ🌼🎤 dan repost
መስከረም ፲፮
በዚች ቀን በኢየሩሳሌም አገር ንግሥት ዕሌኒ የገለጠቻቸው የከበሩ ቦታዎች ሁሉ የተሠሩበትና የከበሩበት ሆነ ።
ቆስጠንጢኖስ ከነገሰ በኋላ እናቱ ቅድስት ዕሌኒ ልጄ ሆይ እኔ ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም በመሔድ የክርስቶስን ዕፀ መስቀል ፈልጌ አወጣ ዘንድ ለእግዚአብሔር ስዕለትን ተስያለሁ አለችው ።
ቆስጠንጢኖስም ሰምቶ ደስ አለው ብዙ ሠራዊትና ገንዘብ ሰጥቶ ላካት። ኢየሩሳሌምም በደረሰች ጊዜ ከከበሩ ቦታዎች ተባረከች ። ከዚህም በኋላ የከበረና አዳኝ የሆነ የክርስቶስን ዕፀ መስቀል ከብዙ ፍለጋ በኋላ አገኘች እግዚአብሔርንም አመሰገነች።
ከዚህም በኋላ በጎልጎታ፣ በቤተልሔም፣ በጽርሐ ጽዮን፣ በጌቴሴማኔ፣ በደብረ ዘይት እና በከበሩ ቦታዎች ሁሉ በዕንቁ በወርቅና በብር የቤተ መቅደስ መሠዊያዎች እንዲሠሩ አዘዘች።
ጻድቅ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም በነገሠ በ፴ ዓመቱ የከበሩ ቦታዎች ሕንፃቸው በተፈጸመ ጊዜ ለቁስጥንጥንያ፣ ለአንጾኪያ፣ለእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ኤጲስቆጶሶቻቸውን በመያዝ ሁሉም በኢየሩሳሌም የታነፁትን አብያተ ክርስቲያናት እንዲያከብሩ አዘዘ። ንጉሡም እንዳዘዘ ሁሉም ተሰበሰቡ የቁርባን ቅዳሴንም ቀድሰው ለምእመናን ሥጋውንና ደሙን አቀበሉ በዚችም ቀን ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ።
የቅዱሳን በረከታቸው ይደርብን! አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ:- መጽሐፈ ስንክሳር
#ድምፀ_ተዋህዶ
https://t.me/dmtse_tewaedo