መንፈሳዊ ትምህርት | eotc theology 🔍 dan repost
እንኳን ለቅዱስ ኤልያስ ዓመታዊ ክብረ በዓል (የልደት ቀን) በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፥ አደረሰን፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ካሉት ቅዱሳን ነቢያት ዝናም በማቆም ብቸኛ ነቢይ፡፡
👇
በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ካሉት ቅዱሳን ነቢያት ዝናም በማቆም ብቸኛ ነቢይ፡፡
✤ 1. ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር ከመስጠት እንዲከለከል ምድርም የተከሉባትን እንዳታጸድቅ የዘሩባትን እንዳታበቅል ለባለንብረቱ አመለከተ ይህም ጥያቄው ከእግዚአብሔር መልስ አግኝቷል፡፡ ነገሥ 17፥1-2፡፡ ከዚህ ላይ የሊቀ ነቢያት ሙሴንና የኢሳይያስን ቃል ያስጠቅሳል ዘዳ 32፥1-4፣ ኢሳ 1፥2-5፡፡ በእነዚህ እስከፊ ዓመታት ውስጥ በመሪዎች አመፅ በኤልያስ ተግሣጽ የሚመለከተውም የማይመለከተውም የሚልሰውና ሚቀምሰው አጥቶ በዋለበት እንደ ቅጠል ረገፈ እንደሻሸተ ነጠፈ፡፡ የኀጥአን ፍዳ ጻድቅ ይደፋ ይሏል ይህ ነው፡፡
ዛሬም በአምስቱ ክፍለ ዓለም የብዙኃኑ እልቂት ሲፈጸም የሚታየው በጥቂት እግዚአብሔር የለሽ ሰይጣን ጁንታዎች ሽፍቶች መሆኑን ከአክአብና ኤልዛቤል ይማሯል፡፡
ይህን የኤልያስን ጠበቅ ያለ እገዳ ከስምንት መቶ አምሳው ነቢያተ ሐሰት ካህናተ ጣዖት አንዱም ወደ ሚመለከተው በጸሎቱም ሆነ በመሥዋዕቱ አመልክቶ ሊያስነሳ ወይም ለማስነሳት የቻለ የለም፡ ጠንቋዮችና አታላዮች በብሉይ ኪዳን ብዙ ጊዜ ከቤተ መንግሥት ተለይተው አይርቁም፡፡ 1ኛ ነገሥ 18፥22፣ዳን 2፥1-14፡፡
✤ 2. አመጸኞች አክአብንና ኤልዛቤልን ምንነታቸውን ካሳወቀ በኋላ የዘጋውን ለመክፈት ወደ ፈጣሪው በመጸለይ ዝናም አዝንሟል፡፡ 1ኛ ነገሥ. 18፥41-46፣ ያዕ 5 17-18 እግዚአብሔር ለወዳጆቹ የገባውን ቃል ኪዳን አያጥፍም አቁም ሲሉት ያቆማል ስጥ ሲሉት ይሰጣል እንጂ ምን አገባቸው ብሎ እንደፈለገው አያደርግም፡፡
የእግዚአብሔር ሐዋርያ ስለ ኤልያስ ማንነት ሲያደንቅ ኤልያስ እንደኛ ሰው ነበር ዝናም እንዳይዘንም ከለከለ እንደገናም እንዲዘንም አደረገ በማለት በዘመኑ የነበሩ ክርስቲያኖች ከቀና ክርስትናቸው ምን እንደሚጠበቅባቸው ከእምነታቸው ምን ማግኘት እንዳለባቸው ይጠይቃል ያዕ.5፥13-20፡፡ ዛሬስ ምን ይመስሎታል፡፡
ኤልያስ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ካሉት ቅዱሳን ነቢያት ዝናም በማቆም ብቸኛ ነቢይ ነው፡፡ ነገር ግን በረዶ ያዘነመላቸው አንደኛ ሙሴ ዘፀ 9፥13-21 ሁለተኛ ኢያሱ 10፥9-12 ሦስተኛም ሳሙኤል 1ኛ ሳሙ 12፥1-19 ይመለከታል፡፡
✤ 3. በተፈጥሮ የማይመስላቸው በቋንቋም የማይግባባቸው እንኳን ለሰው ሥጋ ሊያመጡ ከሰው ሥጋ የሚነጥቁ አሞራዎች ከየት እንደሚያመጡት የማይታወቅ እንጀራና ሥጋ ለምግብ እንዲያመላልሱለት አደረገ 1ኛ ነገሥ 17፥6-7፡፡ እነዚህ አሞራዎች ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ በጋ ከክረምት የለምንም እረፍት ኤልያስን ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡ እምነት ካለ ተአምር መሥራት አይገድም ይህንም ከኤልያስ ይማራል፡፡
✤ 4.ለአንዲት መበለት ዱቄትና ዘይት አበረከተ፡፤ ኤልያስ ቁራሽ እየለመነ ያደረገውን ተአምር ልብ ይሏል፡፡ 1ኛ ነገሥ. 17፥16-24፡፡
✤ 5. ዱቄትና ዘይት ያበረከተላት ሴት ልጇ ቢሞት ከሞት አስነሳው 1ኛ ነገሥ. 17፥20-23 ይህች ሴት በእምነቷ አርአያነት ያላት ደገኛ ሴት ናት፡፡ ኤልያስን የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ፣ ኀጢአቴንስ ታስብ ዘንድ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን ብላዋለች፡፡ ኤልያስም በእግዚአብሔር ኀይል ማንኛውንም ችግር ለመፍታት ሙሉ መብት ነበረውና ወዲያውኑ የሞተውን ብላቴና ጠጋ ብሎ ወደ ፈጣሪው በጸሎት በማመልከት አስነስቶ የብላቴናውን እናት አስደስቷል 1ኛ ነገሥ 17 17-24
ሐዋርያ እምነት ጀግኖችን በመዘገበበት አንቀጽ ይችን ሴት ልብ ይሏል፤ ዕብ 11፥35፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያሉ እናቶች ያስፈልቷል፡፡ ይህችን ሴት የሚመስሉ እናቶች 2ኛ ነገሥ. 4፥18-38 ፣ሉቃ 7፥11-17 ተመዝግበዋል፡፡ በሐዋርያት ሥራም ያሉት እናቶች ከእነዚህ ጋር ያነጻጽሯል የሐዋሥ 9 36-43፡፡
✤ 6. ለብዙ ጊዜ በቤተ መንግሥት ተሰግስገው አክአብና ኤልዛቤልን በሐሰት ሲደልሉ ግብዝ ሕብረተሰቡን ሲያታልሉ ለፍቶ ያገኘው ገንዘቡን ሲሸልጉ በኀጢአት ሊያስወጉ የነበሩ ነቢያተ ሐሰትና ካህናተ ጣዖትን በሕብረተሰቡ ፊት እስከ መምህራቸው ሰይጣን በቅሌት አከናንቦ ሲያስቅባቸው ውሏል፤ 1ኛ ነገሥ 18 20 -29፡፡ ሰይጣን በሰማርያ በምድር እንደዚያ ቀን ሰው መዘባበቻ በመሆን የውርደት ቀን ገጥሞት አያውቅም፡፡ በገዛ አገሩና መንደሩ፡፡
7. ወደ ፈጣሪው በጸሎት በማመልከት ያቀረበው ንጹሕ መሥዋዕቱን ከሰማይ እሳት ወርዶ በሰው ፊት በላለት 1ኛ ነገሥ 18 30-40፡፡ በዚህም ማንነቱን በሰይጣንና በሰይጣን አቀንቃኞች ፊት አስመስክሯል፡፡
✤ 8. ምግብና መጠጥ መልአክ ከሰማይ አመጣለት ያንን ተመግቦ ለአርባ ቀን ያለምንም ምግብ መጠጥ ተጉዟል 1ኛ ነገሥ 19፥5-7
✤ 9. እሳት ከሰማይ በማዝነም ሊጣሉት የመጡትን መምለኪያነ ጣኦት ምሉአነ ኀጢአት የሰይጣን ሠራዊት በሰው ደም የሰከሩ በዲያብሎስ የሚመሩ ጠላቶቹን አጋይቷል 2ኛ ነገሥ 1 9-13
✤ 10. በመጎናጸፊያው የዮርዳኖስን ባሕር ከፍሎ ከነ ደቀመዝሙሩ በደረቅ ተሸግሯል 2ኛ ነገሥ. 2፥11
✤ 11. ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ918 ዓመተ ዓለም ሳይሞት በሕይወቱ መራራው ሞት ዕያየው በብርሃን ሠረገላ ወደሰማይ አርጓል 2ኛ ነገሥ. 2 6-9
✤ 12. እንደ እያስፈላጊነቱ ከፈጣሪው ጋር ለብዙ ጊዜ ተነጋግሯል ከአንድ እስከ አስራ አንድ ያደረጋቸውን ተአምራት የፈጸመለት ታማኝ ፈጣሪው ሰው በሆነበት ወራት በተራራ ከጓደኞቹ ጋር ብርሃነ መለኮቱን ገለጠለት ማቴ 17 ፥3 ፡፡ ከዚህ ዓለም ከተሰናበቱ በኋላ ወደዚህ ዓለም መጥተው የፈጣሪጣቸውን ሰው መሆን ያዩ ከነቢያተ ጽድቅ ሙሴና ኤልያስ ብቸኞች ናቸው ብፁዓን ከተባሉት ሐዋርያትም ተቆጥረዋል፤ በዚህም ቅዱሳን ከሞት በኋላ እንደሚያማልዱም መስክሯል፡፡ ማቴ 13፥16-17፡፡
ኤልያስ ሰው መባል ወይም ተብሎ በመጠራት እንደማንኛውም ሰው መሆኑ መልአክ አለመሆኑን ሐዋርያ ነግሮናል ያዕ 5፡17-20፡፡
ከኤልያስ ብዙ ነገር ወይም ተግባር ስለሚማሩ ከቅዱስ መጽሐፍ ከ 1ኛ ነገሥ 17፡1 ጀምረው እስከ 2ኛ ነገሥ 2፡11 ረጋ ብለው ይመርምሩ ክርስትናዎትንም ይፈትሹ፡፡
👇