ህዳር 10፤2017 - የገዛ ልጁን ሰርቀሃል በማለት እሳት ባለው እንጨት ደብድቦ ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገው አባት በእስራት ተቀጣ
በምዕራብ ጉጂ ዞን የገዛ ልጁን ሰርቀሃል በማለት በከፍተኛ ሁኔታ በመደብደብ ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገው አባት በእስራት መቀጣቱ ተገልጿል።
አበበ መንገሻ የተባለው ግለሰብ ከባለቤት እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይኖሩ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት ግጭት ውስጥ ይገቡ ነበር። የጸቡ መነሻ ካሏቸው አራት ልጆች መካከል ሻሌ የተባለው 12 ዓመት ልጅ ከቤት እና ከአካባቢው ነዋሪዎች ይሰርቃል የሚለው ስሞታ በመቅረቡ ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል።
በዚህም መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም በእናት እና አባት መካከል በተፈጠረ ግጭት እናትየዋ
ከቤት ወጥተው ይሄዳሉ። ለግጭቱ መነሻ የ12 ዓመቱ ልጅ ገንዘብ ሰርቋል በማለት በመቅጣታቸው ግጭቱ ሊነሳ ችሏል።ከቤት ብር መጥፋቱ እና ከጎረቤትም በተደጋጋሚ የሚደርሰውን ስሞታ ንዴት ውስጥ የከተታቸው አባት የ12 ዓመቱን ታዳጊ በመደብደብ እና እሳት ባለው እንጨት ሰውነቱን በማቃጠል የተለያዩ የአካል ክፍሉ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የምዕራብ ጉጂ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ክፍል ሃላፊ ኮማንደር ብዙነህ ዘውዴ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
በዚህም እናት በልጃቸው ላይ የተፈጸመው ቅጣት ማስጣል ሳይችሉ ይቀራሉ።ልጁም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ፤ በፍጥነት ህክምና ሳያገኝ በመቅረቱ ህይወቱ ያልፋል። የታዳጊእ ህይወት ማለፉን ተከትሎ የአካባቢው ማህበረብ ለፖሊስ ባደረሰው ጥቆማ መሰረት ፖሊስ አስከሬኑን በቦታው ደርሶ ሲመለከት ከፍተኛ የሆነ ቃጠሎ እና ድብደባ መድረሱን በመመልከት ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ይልካል። በዋነኛነት የድርጊቱን ፈጻሚ የሆኑት አባት ተከታትሎ በቁጥጥር ስር በማዋል የምርመራ መዝገቡን በማጠናከር አባት ድርጊቱን መፈጸማቸውን እና ምክንያታቸው የልጃቸው የእጅ ዓመል መሆኑን ቃላቸውን ይገልጻሉ።
ፖሊስም የምርመራ መዝገቡን በማስረጃ በማጠናከር ለዓቃቢ ህግ ይልካል ። ዓቃቢህግ ከፖሊስ የተላከውን መዝገብ በመመልከት በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ቁጥር 539 መሰረት ክስ ይመሰርታል ። የተመሰረተውን ክስ የተመለከተው የምዕርብ ጉጂ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ አበበ መንገሻ በፈጸመው ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑ በመረጋገጡ በሃያ አንድ ዓመት እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን የምዕራብ ጉጂ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ክፍል ሃላፊ ኮማንደር ብዙነህ ዘውዴ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ።
@marakinews