እንግዲህ በዚህ ዕለት የዓለም መድኃኒት ከድንግል ማኅፀን በቀለ!! ዓለም በሙሉ የተጠማውን የሕይወት ውኃ ለመጠጣት የተዘጋጀበት ዕለት ነው። ይህን ዕለት በመንፈሳዊ ደስታ ደስ ተሰኝተን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልናከብር ይገባናል እንጂ፤ በዘፈንና በስካር በቆሸሸ ሀሳብ በዓሉን አናበላሸው ። የልደቴ ቀን እያልን በቤታችን ኬኩን እና ሌላውን ሁሉ የምንበላ ኹሉ እውነተኛውን የልደት ቀን ማወቅ ከፈለጋችሁ ይህ ነው የልደታችሁ ዕለት/ቀን። በዚህ ቀን ጌታችን ስለሁላችን ድኅነት ብሎ ስለተወለደ የእርሱ የልደት ዕለት የእኛም የልደት ዕለት ነው። አዲስ አድሮጎ ሊወልደን በአምሳላችን ፈጣሪያችን የተወለደበት ዕለት የልደት ዕለታችን ኾኖ ካልተከበረ የቱ ቀን ሊከበር ነው። ዛሬ እውነተኛ ብርሃን ጨለማችንን ያርቅልን ዘንድ የወጣበት ዕለት ነው።
ዮሐንስ ዘክሮንስታድ “እኛን ከምድር አፈር የፈጠረንና የሕይወትን እስትንፍስ እፍ ያለብን ወደ ዓለም መጣ፤ በአንዲት ቃል ብቻ የሚታዩትንና የማይታዩትን ፍጥረታት ካለመኖር ወደመኖር ያመጣቸው እርሱ መጣ። ... የእርሱ መምጣት እንዴት ያለ ትሕትና ነው!! ምድራዊ ሀብት ከሌላት ድንግል በአንዲት ጎጆ ተወለደ፤ በድህነት ጨርቅ ተጠቅልሎም በበረት ተኛ።” እያለ የክርስቶስን በትሕትና መምጣት ያስረዳናል።
ይህቺ ዕለት ትሕትና በምድር ላይ የታየችበት የትሕትና ዕለት ናት። አዳም በትዕቢቱ ከቀደመ ክብሩ ቢዋረድም ክርስቶስ በትሕትና ከቀደመው ወደተሻለ ቦታ ከፍ አድርጎ አወጣው። በእርግጥ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾኖ የተገለጠበት አንዱ ምክንያት ለአርአያነት ስለኾነ÷ በትሕትና መታየቱ የሰው ልጅ ወደ መዳን ለመግባት የትሕትናንን ትምህርት ከራሱ ከባለቤቱ መማር ስላለበት ነው። በጌታችን የልደት ዕለት በትዕቢት የሚመላለሱ ልቦናዎች የጌታችንን የልደት ዕለት የረሱ ልቦናዎች ናቸው። እጅግ ዝቅ ማለት እጅግ ከፍ ያደርጋል፤ አምላክ ሰው ኾነ የሚለውን መስማት በምንም ቋንቋ ሊገለጥ የማይቻል እጅግ ጥልቅ የኾነ የትሕትና ውቅያኖስ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው የማይቆጠሩ ብዙ ጸጋዎችን ልናገኝ የቻልነው። እንግዲህ በዚህች ዕለት የትሕትናንን ትምህርት ቁጭ ብሎ መማርና የትሕትና መምህራችንን ማመስገን ያስፈልገናል። በዚህች ዕለት በተድላ ሥጋ ኾነው ስለ ትሕትና መምህር ስለክርስቶስ የመወለድ ምሥጢር ሳይማሩና በምሳሌ ሳይኾን በተግባር ወደ ጌታችን የልደት ዕለት ወደምትወስደን ቅድስት ቤተልሔም ለማድነቅና በምስጋና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ለመደመር አለመሄድ እንዴት ያለ አለመታደል ነው!
ቃል ሥጋ የኾነው እኛን ከምድራዊ አኗኗር ወደ ሰማያዊ አኗኗር ለማሸጋገር ነው፡፡ ኀጥአንን ጻድቃን ለማድረግ፣ ከመበስበስ አንሥቶ ወዳለመበስበስ ሊያስነሣን፣ ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባርያ ከመኾን የእግዚአብሔር ልጅ ወደመኾን ሊያሻግረን፣ ከመዋቲነት ወደ ኢመዋቲነት፣ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ከእርሱ ጋር የንጉሥ ልጆች አድርጎ ሊያከብረን መጣ፡፡ አቤት ገደብ የለሽ የእግዚአብሔር ርኅራኄ! አቤት የማይገለጽ የእግዚአብሔር ጥበብ! አቤት ታላቅ መደነቅ! የሰውን አእምሮ ብቻ የሚያስደንቅ ሳይኾን የቅዱሳን መላእክትን ጭምር ነው እንጂ!። የዛሬውን ዕለት ማክበር ማለት እነዚህን ኹሉ ጸጋዎች ለማግኘት መብቃት ማለት።
በዛሬው ዕለት ውስጥ ወደ መደነቅ ከፍ ያላለ ፍጥረት ማግኘት ፈጽሞ የማይቻል ነው። የእግዚአብሔር ጥበብ የጠላታችንን ጥበብ ያፈራረሰበት ዕለት ነው። የጌታችንን የልደት ዕለት በማያቋርጥ ምስጋና ልናክብር የሚገባን ከላይ የተዘረዘሩትን ልዩ ስጦታዎች ለመቀበል ነው። አንድ ሕፃን ልጅ በልደቱ ዕለት ስጦታ ቢሰጠው ገና እንደተወለደ ስጦታውን ስጦታ መኾኑን ተረድቶ ሊቀበል አይችልም፡፡ ዛሬ የምናከብረው የልደት ዕለት ግን ሕፃኑ ራሱ ልደቱን ለማክበር ለመጡት በቃላት የማይገለጽ ስጦታ የሰጠበት ዕለት ነው።
ቅዱስ አምብሮስ ደግሞ “ማርያም ከተፈጥሮ ሕግ በተቃራኒው በኾነ መንገድ ልጅ ወለደች የሚለው ለምንድን ነው አልታመን ያለው? ከተፈጥር ሕግ ውጭ ባሕር ዐየች ሸሸችም ዮርዳኖስም ወደ ኋላዋ ተመለሰች ተብሎ አይደለምን? መዝ 113÷3፣ ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ ከዓለት ውኃ ፈልቋል ዘጸ 17፣ ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ ውኃው እንደ ግድግዳ ቆሟል ዘጸ 14÷6፣ ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ ብረቱ በውኃ ላይ ተንሳፍፏል፣ ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ ሰው በባሕር ላይ ተራምዷል” እያለ ይህ ታላቅ ሊቅ የእመቤታችንን ድንግልና ላለመቀበል ምንም ዓይነት ምክንያት መፍጠር እንደማንችል ይገልጥልና።
ስለዚህ በጌታችን የልደት ዕለት ከሰው ልጆች ልቦና የጥርጣሬ ድንጋይ ተነቅሎ ይወድቃል የተፈጥሮን ሕግ የሚቃረነው የድንግል በድንግልና መውለድ ይመሰከራል!! ዛሬ ሊብራሩ የማይችሉ ልዩ ኹነቶች የተፈጸሙበት ዕለት ነው፡፡ አምላክ የሰውን ሥጋና ነፍስ ተዋሕዶ ሰው ኾኖ የተገለጸበት፤ ድንግልም የማይወሰነውን አምላክ በማኅፀኗ ከመወሰንም አልፋ በታተመ ድንግልና የወለደችበት ዕለት ነው።
ድንግል ወለደች ተብሎ ከተፈጥሮ ሕግና ሥርዓት ውጭ በኾነ መንገድ የሚገለጽበት ልዩ ዕለት! የተፈጥሮ ባለቤትን በንጽሕት ሙሽራ በደንግል ማርያም ማኅፀን የራሱን ቤት በተዋሕዶ ሠርቶ የወጣበት ዕለት። ዛሬ ሰማይ ወለደች እንላለን፤ ግን ይህቺ ሰማይ ግሳንግሱ ፀሐይ የሚታይባት ሰማይ ሳትኾን የማይታየው ፀሐይ የሚታይባት ሰማይ ናት።
በዓለምም ከዓለም ውጭ ያለው ጌታ በቤተልሔም የታየበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ሲባል አጥርተው ማየት በማይችሉ ዘንድ ውስን ብቻ የሚመስል÷ ነገር ግን በቅድስና መስታወት ለሚያዩት በአርያምም እየተመሰገነ በቤተልሔም የተወለደበት ዕለት ነው። ሰይጣን የደነገጠበትና ኃይሉ የደከመበት ዕለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት በልደቱ ስፍራ መኾን አጋንንትን እንዳይቀርቡን ያደርጋል እልፍ አእላፋት መላእክት በዚያ ከበው ይጠብቁናልና። ተፈጥሮአዊውን ሕግ የገለበጠው ጌታ የተፈጥሮን ሕግ የሠራውና እንደፈቃዱም የሚያደርገው እርሱ መኾኑን ያወቅንበት ዕለት ነው። እንኳን በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ!
@sebhwo_leamlakne