የምርመራ ዘገባው ከምን ደረሰ...!?ዛሬ የማወጋችሁ በቀኃሥ ዘመን በኢትዮጵያ የሚኖር
የግሪክ ማኅበረሰብ እንዲማርበት ተቋቁሞ ከዓመታት በሗላ ራሱን በድብቅ ወደ ንግድ ተቋምነት ቀይሮ ላለፉት 25 ዓመታት አምስት ሳንቲም ግብር ሳይከፍል ከአንድ ልጅ በመቶ ሺሆች ብር እያስከፈለ በመቀጠል ላይ ስላለ «የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት»ስለሚባል ተቋም ነው።
ግሪክ እና ኢትዮጵያ ከእነ ሔሮድተስ እስከ ባለቅኔው ሆሜር ዘመን፣ከታላቁ እስክንድር እስከ ታላቂቱ ሕንደኬ ጊዜ፣ከዘጠኙ ቅዱሳት እስከ 19ነኛው ክፍለ ዘመን የሲራራ ነጋዴዎች ወቅት የተሻገረ ለዓለም የሥልጣኔ ጮራ ሆኖ የማብራት የጋራ ድል ጌቶች ናቸው።
ግሪካዊው ባለቅኔ ሆሜር በዘመኑ በአፍሪቃ ምድር ያበበችውን ውብ አገር ኢትዮጵያ አወድሶ አይጠግብም።
ኮስመስ የተባለው ግሪካዊ ተጓዥ ስለ አክሱም ወርቃማ ዓመታት ለመክተብ ባሕር አቋርጦ በእነ ዞስካለስ መንደር፣በአዶሊስ ቀየ ሰነባብቷል።
የታላቁ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ እና የታሪክ ጸሐፊ ጳውሎስ ኞኞ አባት ያንን ባለ ብሩህ አዕምሮ ልጃቸው ለመውለድ ከኢትዮጵያዊት ሴት ወይዘሮ ትበልጫለሽ አንዳርጌ ቀየ መገኘት ነበረባቸው።
ይህ ሁሉ የሁለቱ ቀደምት ሕዝቦች ውብ የታሪክ ሰበዝ ሲመዘዝ የሚገኘ ሃቅ ነው።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግን ግሪክም ሆነች ኢትዮጵያ የዓለም ጭራ ሆነዋል።የሶቆራጥስ አገር በአውሮጳ አበዳሪዎቿ የተናቀች ድሃ ምድር ከሆነች ዓመታት «እንደ መስክ ውሃ ፈሰሱ»።
የቅዱስ ያሬድ ምድር ኢትዮጵያ ደግሞ ዛሬ ድረስ ልጆቿን በሰላም ማኖር ተስኗታል።
ከሁሉም የከፋው ግን ለወራት የአፍሪካ ሕዳሴ ቴሌቪዥን አገልግሎት(Arts tv) በግሪካዊያን ባለቤትነት በሚተዳደረው፣ከብዙ ስሞቹ በአንዱ"የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት"ብለን በምንጠራው የትምህርት ተቋም ውስጥ አተኩሮ የያዘው የምርመራ ዘገባ ላይ የሚታየው ነገር ነው።
ከዚህ ጽሁፍ ቀደም ብሎ በጉዳዩ ዙሪያ ከስድስት በላይ ዝግጅቶችን አስተላልፈናል፣ብዙ ጋዜጦች እና ብዙኃን መገናኛዎች የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ለዓመታት ግብር ሳይከፍል በመሐል አዲስ አበባ መነገዱን ዘግበዋል፣ትምህርት ሚኒስቴር ከ2014 የትምህርት ዘመን በሗላ ማስተማር እንደሚከለክለው በአደባባይ ተናግሯል፣ብዙ ብዙ ነገሮች አልፈዋል።
ይህ ጽሁፍ በማኅበራዊ መገናኛዎቸ በሚነበብበት አፍታ፦
1.ከብዙ መጠሪያ ስሞቹ በአንዱ«የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት»የሚባለው ተቋም በትምህርት ሚኒስቴር፣ፍትሕ ሚኒስቴር፣የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና በትምህርት ቤቱ ወላጅ ማኅበር በሕገ-ወጥ አሠራሮች ተጠርጥሯል።
2.ይህን ላለፉት ከ20 በላይ ዓመታት አገሪቱን ከ አራት ቢሊዮን ብር የሚበልጥ ግብር እንደሠረቀ የሚገመት ትምህርት ቤት ለትርፍ ወዳልተቋቋመ ድርጅትነት ለመመለስ በቁጥር አንድ የተጠቀሱትን አካላት እና ራሱን ትምህርት ቤቱን የሚወክሉ አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል።
3.ይህ በእንዲህ እንዳለ ትምህርት ቤቱ እንደሽፋን ተጠቅሞ ከኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ ላይ ግብር ያጭበረብርበታል የተባለው በእየ ሁለት ዓመቱ የሚታደስ ጊዚያዊ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች ፈቃድ ከፈረንጆቹ መጋቢት 30 ቀን 2023 ወዲህ አብቅቷል።አልታደሰም።
4.ተቋሙ በአርትስ ቴሌቪዥን፣በእኔ እና መረጃ በመሥጠት በተባበሩ አገር ወዳድ ቁርጠኛ የተማሪ ወላጆች፣መምህራን ላይ የ«እንከሳችሗለን፣እናባርራችሗለን»ዛቻ በጽሁፍም ሆነ በድምጽ ከወረወረ በሗላ አልሳካለት ብሎ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት ውስጥ የጊዚያዊ ኮሚቴው ሒደት እንዲቆምለት ትምህርት ሚኒስቴር'ን ና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንን ከሶ በአንድ ቀን እግድ ተፈቅዶለት ሒደቱን እያጓተተ ይገኛል።
5.በጉዳዩ ላይ የከፊል ምርመራ ዘገባው ቡድን መሪ በመሆን ላለፉት በርከት ያሉ ወራት ብዙ የተቋማትን ደጅ ረግጫለሁ።አብዛኞቹ በአካሄድ ስልቴ የተነሳ መጠነኛ መረጃዎች ሰጥተውኛል።የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤት የሆነው ትምህርት ሚኒስቴር ግን እስከዚች አፍታ ድረስ መረጃ ለመስጠት አልቻለም።
ከሰሞኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሁለት ደብዳቤዎች ወደ ተቋሙ እንዳስገባ ከጠየቁኝ ባለሥልጣን ላይ ጥሩ ተስፋ ይታየኛል።ፈጣን ምላሽ እጠብቃለሁ።
አድናቆት...!
ሃላፊነቱ የሆነን ሰው አላመሰግንም።መደናነቅ ግን የአንድ ዘመን ሰዎች ልማድ መሆን አለበት።
ስለሆነም፦
ሀ.የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት'ን እንከኖች ተመልክተው በከፍተኛ ቁርጠኝነት መረጃ በመሥጠት እየተባበሩኝ ያሉትን አካላት(ወላጆች፣መምህራን፣የሕግባለሞያዎች፣የቀድሞ ሠራተኞች)
ሁ.አገሩ ሁሉ «ግደለው፣ስቀለው»ወይም «አሸሸ ገዳሜ»በሆነበት ጊዜ እንዲህ ያለ ትውልድ የሚያድን ሥራ እንዲሠራበት ጣቢያውን ለፈቀዱት የአርትስ ቴሌቪዥን ከፍተኛ አመራሮች፣
ሂ.በተቃራኒ አንፃር ሆነው የትምህርት ቤቱን መልካምነት ና ሕጋዊ አካሄድ ለማስረዳት በራቸውን እና አንደበታቸውን የከፈቱ አካላት አድናቆት ይገባቸዋል።
ከሞላ ጎደል ጫፍ ላይ የደረሰውን የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ጉዳይ እየተከታተልኩ ሃቅ ለሚገዳቸው ሁሉ አደርሳለሁ።
ታመነ መንግስቴ ውቤ—ጋዜጠኛ
የአፍሪካ ሕዳሴ ቴሌቪዥን አገልግሎት(Arts tv) በግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ላይ እየከወነው ባለው የምርመራ ዘገባ ሒደት ለሕዝብ ዕይታ የቀረቡ ዝግጅቶች በቅደም ተከተል፦
1.https://
youtu.be/NMTu7865Cdk2.https://
youtu.be/v-kSmKPEOFE3.https://
youtu.be/4bAUAZ8fm3w4.https://
youtu.be/3R5UcMFYcGk5.https://
youtu.be/3R5UcMFYcGk6.https://
youtu.be/jgnUn_3wZMcናቸው!