የአዕምሮ ዕውቀት ብቻውን በጎ ሰው አያደርግም!
(እ.ብ.ይ.)
አላዋቂ መሆን ቀላል ነው፤ አለማሰብ አይከብድም፡፡ ደነዝ መሆን እውቀት አይሻም፡፡ ዓላማ ቢስ መሆን አያስቸግርም፡፡ ድንቁርና ወጪ የለውም፡፡ ጨካኝ ለመሆን የሮኬት ሳይንስ ማጥናት አይጠበቅብህም፡፡ ሰው ላይ ክፋት ለመፈፀም የተለየ ችሎታ አይፈልግም፡፡ አድፍጠህ፣ ተደብቀህ፣ ጨለማን ተገን አድርገህ ሰው ላይ ጉዳት ማድረስ ልዩ ክህሎት አይሻም፡፡ የውሸት ወሬ ፈጥረህ ሰውን ከሰው ማጋጨት፣ ትዳር መበተን፤ ወዳጅነትን ማበላሸት፤ ፍቅርን ማርከስ ስማርት መሆን አይጠይቅም፡፡ ክፉ ለመሆን ዋና መስፈርቱ አለማሰብ ነው፡፡ ጨካኝ ለመሆን የሚጠበቅብህም ህሊና ቢስ መሆን ነው፡፡ ለመሸምጠጥ፣ ቃልህን ለማጠፍ፣ አደራህን ለመብላት ምንም የምትወጣው ዳገት፤ የምትወርደው ቁልቁለት የለም፡፡ የሰውን ልብ ለመስበር፣ ተስፋውን ለመንጠቅ፤ ህልሙን ለመቀማት፤ ዓላማውን ለማደናቀፍ ዩንቨርስቲ መግባት አያስፈልግህም፡፡ የሚያስፈልግህ እፍረተ-ቢስ መሆን ብቻ ነው፡፡ ሕሊናህን ለመሸጥ፤ ሞራልህን ለማውደም፣ ሰውነትህን አሽቀንጥረህ ለመጣል፤ በሆድህ ለመውደቅ አለማሰብ በቂ ነው፡፡
ፕሌቶ ‹‹አብዛኛው ሰው ሌላ ሰውን በቀላሉ ሊጎዳ ይችላል፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው በቀላሉ በጎ ስራ መስራት አይችልም፡፡ (Any man may easily harm, but not every man can do good to another)›› የሚለው ለዚህ ነው፡፡ አንዳንዶች መልካምነት ቀላል ነው ይላሉ፡፡ እኔ ግን አልስማማም፡፡ መልካምነት ከባድ ነው ባይ ነኝ፡፡ በዚህ ‹‹እኔ ብቻ›› በሚቀነቀንባት ዓለምና ዘመን ውስጥ መልካም ሰው ሆኖ መገኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ መልካምነት የሃሳብ ውጣ-ውረድ አለው፤ ማንም ዘው ብሎ የሚገባበት አይደለም፡፡ መልካምነት ዕውቀት ይፈልጋል፡፡ መልካምነት ከሌለህ ላይ መስጠትን ግድ ይላል፡፡ መልካምነት ከራስ ማለፍን ይሻል፡፡ መልካምነት ከእውነት ጋር ያጣብቃል፡፡ መልካምነት ያለአጃቢ፣ ያለአጭብጫቢ፣ ያለደጋፊ “ብቻን-መቆም” ይጠይቃል፡፡ መልካምነት ላለውም ለሌውም፤ ለተራውም ለባለስልጣኑም፤ ለሐብታም ልጁም፤ ለድሀአደጉም እኩል ማሰብን ይፈልጋል፡፡ መልካምነት ያለፍትሐዊነት ዋጋ የለውም፡፡ መልካምነት ከሆድ ይልቅ ህሊናን ያስቀድማል፡፡ ቅን አሳቢ መሆን የቤት-ስራው ብዙ ነው፡፡ አዋቂ ለመሆን ከራስ ሃሳብ ጋር ውጊያ መግጠም ያስገድዳል፡፡ ከአጉል ባህሉ፣ ከዘልማድ አስተሳሰቡ፣ ከአሉታዊ አመለካከቱ፤ ከዓለሙ ጋር የፊትለፊት ጦርነት መክፈት ይሻል፡፡ መልካምነት ራስንም ሌላውንም ከመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡ ሰው ሺ ዩንቨርስቲ ገብቶ ቢወጣ ከራሱ ጋር መነጋገር ካልጀመረ ውጫዊ እንጂ ውስጣዊ ዕውቀት አይኖረውም፤ ሌላውን ያውቃል እንጂ ራሱን አያውቅም፡፡ ስለቁሱ ይመራመራል እንጂ ስለመንፈሱ አይራቀቅም፡፡ በእንጀራ እውቀት ብቻ ሰው አዋቂ አይሆንም፡፡ የአዕምሮ ዕውቀት ብቻውን በጎ ሰው አያደርግም፡፡ በአዕምሮም፣ በስሜትም፣ በመንፈስም አዋቂ ለመሆን ራስንም፣ ሌላውንም የሚገነዘብ ደግ ልቦና ግድ ይላል፡፡ ለዚህ ነው አሜሪካዊዋ ፈላስፋ ማርታ ኑሳቡም (Martha Nussbaum) ‹‹ዕውቀት ለመልካም ባህሪ ዋስትና አይሆንም፤ አላዋቂነት ግን ለመጥፎ ባህሪ ምናባዊ ማረጋገጫ ነው (Knowledge is no guarantee of good behavior, but ignorance is a virtual guarantee of bad behavior.)›› የምትለን፡፡
ፕሌቶ ‹‹“ሁለት ዓይነት የነፍስ በሽታዎች አሉ፡፡ እነሱም የሞራል ውድቀትና ድንቁርና ናቸው፡፡ “There are two kinds of disease of the soul, vice and ignorance.”›› ይላል፡፡ እውነት ነው ብልህ ሰው ሞራሉ እንዳይወድቅ ዘወትር ሰውነቱን ያጎለብታል፤ አዕምሮውም እንዳይደነቁር መልካም ሃሳቦችን ለልቡ ይመግበዋል፡፡ በራሱ አሉታዊ ሃሳብ በሚፈጥረው በሽታ ነፍሱን አያሰቃይም፡፡ አስተዋይ ሰው ሃሳብን ከሃሳብ እያፋጨ አዲስ ሃሳብ ይፈጥራል እንጂ ሰዎችን እያጋጨ ከፀቡ በሚገኘው ትርፍ ስራ አይፈጥርም፡፡ ወሬ በማቀበል፣ ነገር በመስራት፣ ሴራ በመጎንጎን፤ ተንኮል በመቀመር፣ ክፋትን በመለማመድ ያልታመመ ጤነኛ ሰው መሆን አይቻልም፡፡ ጤነኛ ሰው ቆሻሻ ሃሳቡን ወዲያው ወዲያው ያስወግዳል፤ ክፉ ሃሳቦች በአዕምሮው ሲመላለሱ ቶሎ ብሎ ያፀዳቸዋል፡፡ ቅናትና ምቀኝነትን የሚጠነስሱ ስሜታዊ ሃሳቦች የአዕምሮውን ግድግዳ ጥሰው ሲገቡ ቀና ሃሳቦችን በመፍጠር ይዋጋቸዋል፡፡ የዲያብሎስ ውጊያ ይሉሃል ይሄ ነው!! የሃሳብ ጦርነቱ የመጀመሪያው ግንባር ከራስህ ጋር የሚደረገው ነውና!!
ወዳጄ ሆይ… አሜሪካዊው ፀሐፊና ገጣሚ ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን ‹‹እውነት ከፍቅር የበለጠ እጅግ ውብ ነው፡፡ መልካምነትህ የእውነት ጠርዝ ከሌለው ዋጋ የለውም (Truth is handsomer than the affectation of love. Your goodness must have some edge to it, — else it is none.)›› እንዲል ዕውቀትህ መልካምነት፤ መልካምነትህ እውነት ይኑረው፡፡ መፅሐፈ ሲራክም ‹‹ደስም ቢለው ቢያዝንም የሰው ልቡ ፊቱን ይለውጠዋል፡፡ ደስ ያለው ልቦና ምልክቱ ብሩህ ገፅ ነው፡፡›› እንዲል ደስታ ከመልካምነትህና ከእውነተኛነትህ የምትለቅመው ጣፋጭ ፍሬ ነው፡፡ ብዙዎች ያገጥጣሉ እንጂ አይስቁም፡፡ በጥርሳቸው ሊሸውዱህ የሚሞክሩ ውስጡን ለቄስ የሆኑ ሺ ናቸው፡፡ ሳቃቸው ከጥርሳቸው የማያልፍ የትየለሌ ናቸው፡፡ እውነተኛዋን ሳቅ የሚስቋት ግን መንፈሳቸውን ያነቁ፣ ስሜታቸውን የገሩ፤ አዕምሯውን ያበለፀጉና ለራሳቸውም ሆነ ለሌላው መልካም የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡
ቸር ጊዜ!
ደግ ስራ! እውነተኛ ዕውቀት!
ኢትዮጰያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑሩ!
____
© እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሠኞ ጥር ፲፪ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም.