#ምሥጢረ ንስሓ
ንስሓ ሰውና እግዚአብሔር የሚታረቁበት፣ የእግዚአብሔር ምሕረት፣ ይቅርታና ሰላም የሚገኝበት፣ ስርየተ ኃጢአት፣ ጸጋና በረከትን የምናገኝበት ምሥጢር ነው። ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንም አንዱ ነው። አፈጻጸሙም መናዘዝ በሚችል ሥልጣነ ክህነት ባለው ካህን አማካኝነት ተነሳሒው የበደለውን በደል ተጸጽቶ በመናዘዝ ላጠፋው ጥፋት ተገቢውን ቀኖና የሚቀበልበት ነው። ንስሓ የሰው ልጆች ከአማናዊው ድኅነት ተካፋይ እንዲሆኑ እግዚአብሔር ያዘጋጀልን የጽድቅ በር ነው። ራስን ወቅሶ፣ ስሕተትን አምኖ፣ ዳግም ላለመፈጸም ወስኖ እና ተናዝዞ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው።
“ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ ትጠፋላችሁ” (ሉቃ.13፣3) ተብሎ የተነገረው ንስሓ ከጥፋት ለመዳን ዋናው መንገድ መሆኑን የሚያመለክት ነው። “ንስሓ ግቡ፤ ኃጢአታችሁ ይሰረይላችሁ ዘንድ” (ሐዋ.2፣28) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ያስተማረው የሚያስገነዝበን ይህን ነው። ከኃጢአት ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃችንም ሊያድነን የታመነ ነው” (1ኛዮሐ.1፣8) የተባለው ንስሓ ከአምላካችን የምንታረቅበት በመሆኑ ነው።
በንስሓ ጊዜ መሥዋዕትነትና መንፈሳዊ ትግል ያስፈልጋል። “ከኃጢአት እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ አልተቃወማችሁም (ዕብ.12፣4) እንዲል። ንስሓ እየገቡ ከሰይጣንና ከፈቃደ ሥጋ ጋር ታግሎ ለማሸነፍ መወሰን አማናዊውን ሰላም ያስገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ቦታዎችና በተወሰኑ ግለሰቦች ሲፈጸም የሚታየው ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ተቃራኒ ተግባር ነው። ሰውን የሚያዘናጋ፣ መንፈሳዊ ተጋድሎን ዋጋ የሚያሳጣ ነው። ተነሳሕያን ይህን ተረድተው ሥርዓተ ቤተክርስቲያን የሚያዝዘውን መፈጸም ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ከጸጋ እግዚአብሔር ያርቃልና። ንስሓ ምሥጢር መሆኑንም እንድንዘነጋ ያደርገናልና። ምሥጢረ ንስሓ በአንድ ካህንና በአንድ ተነሳሒ ምእመን አማካኝነት የሚፈጸም ምሥጢር ነው።
በንስሓና በምሥጢረ ንስሓ መካከል መጠነኛ ልዩነት አለ። ንስሓ የምንለው ከመጸጸት ጀምሮ ለካህኑ እስከ መናዘዝ ያለውን ሒደት ነው። ምሥጢረ ንስሓ የምንለው ግን በካህኑ የሚታይ አገልግሎት ቀኖና በመስጠት፣ በመናዘዝ፣ በመምከር፣ ንስሓውን በአግባቡ ሲፈጽም ሥጋ ደሙን እንዲቀበል በማድረግ፣ የመንጻቱ ማረጋገጫ የሚሆነውን ጸሎተ ፍትሐት በማድረስ፣ ማየ ምንዝህ በመርጨት የሚገለጥ ነው። የተነሳሒው ኃጢአት ሲሰረይ በዓይን አይታይም። ምሥጢር ከሚያሰኘው ጉዳይ አንዱም ይህ ነው። ንስሓ ከሚደገሙ ምሥጢራት አንዱ መሆኑም ሰዎች ኃጢአት መሥራት ስለሚደጋግሙ ደጋግመው ንስሓ በመግባት የድኅነት ተካፋይ እንዲሆኑ ነው።
ይህን ታላቅ ምሥጢር አንዳንድ “አጥማቂ ነን ባዮች” በዓመት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ በቀጠሮ ሲያከናውኑ ይታያል። ድርጊቱ ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ውጭ ነው። ለንስሓም ቀጠሮ አይሰጥም።መቼ
እንደምንሞት ስለማናውቅ ተዘጋጅተን መጠበቅ እንጅ ለንስሓ ቀጠሮ ተቀብሎ መቀመጥ አይገባም። ዕለት ዕለት የሠራነውን ኃጢአት ለንስሓ አባታችን በመናዘዝ ንጹሕ ሆነንና ተዘጋጅተን መጠበቅ ይኖርብናል እንጂ። ንስሓ ክህነት በሌለው ሰው ሊፈጸም የማይገባ ድንቅ ምሥጢር ነው። “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ራስህን ለካህን አሳይ” (ማቴ.8፣2) ተብሎ የተነገረውም ለዚህ ነው። በዚህ ዓይነት መንገድ ሲፈጸም የኖረውን ምሥጢረ ንስሓ ስመ ክርስትናን በወረቀት ጽፎ በማቃጠል “ኃጢአትህ ተሰረየልህ” እያሉ ማታለል በተነሳሕያኑም፣ በምሥጢሩም መቀለድ ነው። ድኅነትን ገንዘብ ማድረግ ከፈለግን አታላዮች ከሚፈጽሙት ኢ-ክርስቲያናዊ ድርጊት በመጠበቅ ቤተክርስቲያን የሠራችውን ቀኖና መፈጸም ይገባል።
“ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ይሰረይላቸዋል፤ ይቅር ያላላችኋቸው ግን አይሰረይላቸውም” (ዮሐ.20፣23 የተባለው የሚፈጸመው በሥርዓት ነው። አስቀድመን እንደተመለከትነው ስርየተ ኃጢአት የሚገኘው ስምን በወረቀት ጽፎ ሰብስቦ በማቃጠል ሳይሆን ሥልጣነ ክህነት ያላቸው አባቶች በሚሰጡት ቀኖና አማካኝነት ነው። ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ የተለየ የንስሓ አፈጻጸም የለም። ንስሓ ጸጸት ብቻ ሳይሆን መናዘዝም ያስፈልገዋል። በፈጸመው ኃጢአት ንስሓ ገብቶ ቀኖና አልተቀበለም እንጂ መጸጸትማ ይሁዳም ተጸጽቶ ነበር።
ንስሓ ራሱን የቻለ ጥምቀት አለው። ለዚህ ነው ሥልጣነ ክህነት ባለው አባት እንዲፈጸም ቤተክርስቲያን ሥርዓት የሠራችው። “እኔስ ለንስሓ በውሃ አጠምቃችኋለሁ” (ማቴ. 3፣11) የተባለው ሳይፈጸም የክርስትና ስምን በወረቀት ጽፎ በማቃጠል ስርየት እንደሚገኝ ቤተክርስቲያን ስላላስተማረችን የድርጊቱ ፈጻሚዎችም፣ በዚህ መንገድ ንስሓ ለመግባት የሚፈልጉ ተነሳሕያንም መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።
@Ethiopian_Orthodox