ተረኛው ጨባጭ!
“አንድ ሰው ሕጻን ሆኖ ሲወለድ እጁን (መዳፉን) ጨብጦ ነው፤ አንድ ሰው ሸምግሎ ሲሞት ደግሞ እጁን (መዳፉን) ዘርግቶ ነው” ይላል ካልታወቀ ምንጭ የተቀዳ አባባል፡፡
ለአንድ ሕጻን አንድን ነገር በእጁ አስይዛችሁት ካወቃችሁ ልጁ የያዘውን ነገር በቀላሉ እንደማይለቅ ትደርሱበታላችሁ፡፡ አንድ ሕጻን ልጅ እጁን ጨብጦ መወለዱ ሁሉን ለመያዝ፣ ሁሉን በእጁ ለማስገባትና ሁሉን ነገር በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ የመሞከሩ ምልክት ነው፡፡
አንድ ሰው ሸምግሎ ሲሞት እጁን ዘርግቶ መሞቱ ደግሞ ሁሉን አይቶት፣ ሞክሮት፣ ጨብጦና “የእኔ ነው” ብሎ በመጨረሻ ምንም ነገር የእርሱ እንዳልሆነና አንድ ቀን ሁሉም ነገር ከእርሱ ቁጥጥር ውጪ እንደሚሆን የመገንዘቡ ምልክት ነው፡፡
እውነታው ይህ ነው፡- ተወልደን በልጅነት ባሳለፍንበት ወቅትና ሸምግለን ከዚህ አለም ወደመሰናበት በምንደርስበት ወቅት መካከል ባሉን እንደ ጥላ በሚያልፉት አመታቶቻችን መያዝና መቆጣጠር በምንችለውና በማንችለው መካከል መለየት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ነገ ሁሉንም ነገር ትተነው እንደምናልፍ በመገንዘብ ሁሉን ነገር የእኛ ለማድረግ ጦር ስንማዘዝ ዘመናችንን እንዳናባክነው እናስተውል፡፡
እጅህ በገባው ነገር ደስተኛ ሁን፣ ለመልካም ነገር ተጠቀምበት፡፡ እጅህ ለማስገባት ያልቻልከውን ነገር ለማስገባት ሞክር፣ ነገር ግን ሁሉን ካልያዝኩ በማለት ስትሟገት በጦርነትና በፍርድ ቤት ዘመንህን አታስበላ፡፡ የአለምን ምድር ሁሉ ጨብጠን የእኛ እናደርጋለን ብለው የነበሩ ምእራባውያን ቅኝ ገዢዎች የጨበጡትን ሁሉ ቀስ በቀስ እየለቀቁ እንደሄዱ አትዘንጋ፡፡ እንዲያውም የእነሱንም ቀስ በቀስ የሚያስለቅቃቸው ሁኔታ እየተጋረጠባቸው ነው፡፡
ለጊዜው ነው እንጂ ምንም ነገር በቋሚነት የአንተ አይደለም፡፡ የእኔ ነው ብለህ የምታስበው ሁሉ ለጊዜው በአደራ የተሰጠህ ነው፡፡ ዛሬ አንተ የምትኖርበትን ቤትና መሬት ትናንት የእኔ ነው ብሎ የሚኖርበት ሰው ነበር፡፡ ዛሬ ግን የአንተ ነው፡፡ ነገ ደግሞ ይህንን ስፍራ ሌላው ተረኛው ጨባጭ ይረከበዋል፡፡ ቁም ነገሩ በዘመንህ የጨበጥከውን ነገር የመልቀቂያህ ጊዜ እስከሚመጣ ድረስ ለመልካም ዓላማ የመጠቀምህ ጉዳይ መሆኑን ላስታውስህ፡፡
✍ዶ/ር እዮብ ማሞ
@Gemhalya