🔴 ምክረ አበው MEKRA ABAW™


Kanal geosi va tili: Efiopiya, Amharcha
Toifa: ko‘rsatilmagan


#አባቶችን_ጠይቅ_ይነግሩሃል
● ጠቢብ ከሰነፍ ጋር ቢጣላ፥ ሰነፍ ወይም ይቈጣል ወይም ይስቃል፥
ደምን ለማፍሰስ የሚሹ ሰዎች ፍጹሙን ሰው ይጠላሉ፥ ደግሞም የቅኑን ሰው ነፍስ ይሻሉ።
ሰነፍ ሰው ቍጣውን ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል።
○ መጽሐፈ ምሳሌ ምዕ. 29 ○
ሀሳብ ካላችሁ @habmisget

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Kanal geosi va tili
Efiopiya, Amharcha
Toifa
ko‘rsatilmagan
Statistika
Postlar filtri


ወዳጄ ሆይ ከመብል ሽሽ፤ ከመጠጥም ራቅ፡፡ ጥጋብ ስንፍናን ትወልዳለችና፡፡ ጾምን ጠብቅ። በጾም ኃጢአት ይሠረያልና፡፡ እንዳይጠግብ፣ የሚጋልበውንም እንዳይጥለው ፈረስን እንደሚለጕሙት አንተም እንዲሁም ሥጋህ በፍትወት ነፍስህም በኃጢአት እንዳይወድቅ አፍህን ከመብልና ከመጠጥ ለጕም፡፡ ጌታችን እንበላና እንጠጣ ዘንድ አላዘዘንምና፡፡ ነገር ግን ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጹሙ ጸልዩ አለን እንጂ፡፡

የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፡፡ ስለ መብል በወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉና፡፡ አጥማጆችም በሚያጠምዱበት ጊዜ ወጥመዱን በመብል ይሠውሩታልና፡፡ እንዲሁም ሰይጣን ጣፋጩን ተስፋ አስደርጎ መራራውን ይሰጣል፡፡ ዳግመኛም ብዙውን ተስፋ አስደርጎ ትንሽን ይሰጣል፡፡ አዳምን አምላክ እንደሚሆን ተስፋ እንዲያደርግ አደረገው፡፡ ነገር ግን ከገነት ዕራቍቱን አስወጣው፡፡

በጌታውም ዘንድ የተናቀ አደረገው፡፡ በዚህም መርገምን ወረሰ፡፡ በእርሱ ምክንያትም ምድር ተረገመች፡፡ ሞትም በሰው ላይ ሁሉ ሠለጠነ። የሚበር ወፍ ወደ ምድር ካልተመለከተ ወደ ወጥመድ አይወርድም፡፡ እንዲሁም ለሚጾም ሰው ልቡ በሰማይ ያለውን ያስብ ዘንድ ሥጋው በኃጢአት እንዳይወድቅ ለሰውነቱ ምኞቷን ይከለክላት ዘንድ ይገባል፡፡

ጾም የጸናች ናት፡፡ ትሕትናም የንስሓ ራስ ናት፡፡ በጾም ኤልያስ ከመላእክት ጋር ተቆጥሯልና፡፡ ኤልሳዕም የመምህሩን የኤልያስን መንገድ ተከተለ፡፡ ዕጥፍ ድርብ በረከቱንም አገኘ፡፡

ወንድሞቼ ሆይ በአጋንንት ላይ በሥጋ ድል ማድረግን እናገኝ ዘንድ በጾምና በበጎ ሥራ ሁሉ የመምህሮቻችንን መንገድ እንከተል፡፡ ንጹሕና የተመረጠ ጾምን እግዚአብሔር ይወዳል፡፡ አመፃ ስንፍና ናት፡፡ እግዚአብሔር አማፅያንን ፈጽሞ ይጠላቸዋል፡፡ በአፉ እየጾመ ወንድሙን ለሚገድል ለእርሱ ወዮለት፡፡ በአፉ ጾምን ለሚያውጅ በአንደበቱ ደግሞ አመፃን ለሚናገር ለእርሱ ወዮለት፡፡

ወንድሜ ሆይ አፍህ ከጾመ ልብህም እንዲሁ ይጾም ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡ እነሆ ዐይንኖችህ ክፉን ከመመልከት ይጹሙ፡፡ እጆችህና እግሮችህም ከክፉ ሁሉ ይጹሙ፡፡ የጠላት ወጥመዱ ብዙ ነውና፡፡ በንጉሥ ፊት ተጋዳይ ወታደርን ልትሆን ብትወድ የጦር ዕቃን ትይዝ ዘንድ ተገቢ ነው፡፡ እንዲሁም ከሰይጣን ወጥመድ መዳን የሚወድ ሰው የክርስቶስን ትዕዛዙን ይጠብቅ፡፡ ከገሃነም እሳት ትድን ዘንድ ከትዕቢት ራቅ፡፡ መንግሥተ ሰማያትንም ትወርስ ዘንድ ትሕትናን ፈልግ፡፡

ወዳጄ ሆይ እኔስ ከመብልና ከመጠጥ ትሸሽ ዘንድ ጾምንም በፍጹም ልብህ ትከተላት ዘንድ እፈልጋለሁ፡፡ ትሑታንን ውደዳቸው ከትዕቢተኞችም ራቅ፤ ከጥላቻ ፈቀቅ በል፤ ሰላምንም ፈልጋት፡፡ የክርስቶስን ትዕዛዝ ትፈጽምም ዘንድ በፍቅር ሩጥ፡፡ በአንተ ላይ የኃጢአት ፍሬ እንዳይታይም ከልብህ ቂምንና በቀልን አስወግድ፡፡ ክፉ ሕሊና በመጣብህ ጊዜ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በምታስፈራ የፍርድ ዐደባባይ የምትቆምባትን የፍርድ ቀን አስባት፡፡

(ቅዱስ ኤፍሬም ድርሳን በእንተ ጾም ➛
በድርሳነ ሠለስቱ ሊቃውንት መጽሐፍ ገጽ 195-199 በመምህር ቃለጽድቅ ሕግነህ የተተረጎመ)
@mekra_abaw


ምጽዋት ሥርየተ ኃጢአትን ትሰጣለች፡፡ ሞትንም ቢኾን ታርቃለች፡፡ ይህስ እንደ ምን ነው ያልከኝ እንደ ኾነም ቀጥዬ ግልጽ አደርግልሃለሁ፡፡

“መጽውቶ ከሞት የተረፈ ማን አለ?” ብለህ ትጠይቀኝ ይኾናል፡፡ ወዳጄ ሆይ! ምጽዋት ሞትን እንድታርቅ ኃይል ጉልበት እንዳላት በእውን ከተደረገ ታሪክ ተነሥቼ እነግርሃለሁና የምነግርህን ነገር አትጠራጠር፡፡

ጣቢታ የምትባል አንዲት ሴት ነበረች፡፡ መልካም ሥራን የሞላባትና ምጽዋትን የምትወድ በዚህም ለራሷ መዝገብ የምታከማች ነበረች፡፡ ለመበለቶች ልብስንና የሚያስፈልጋቸውን ኹሉ ትሰጣቸው ነበር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን ሞተች፡፡

አሁን ደግሞ እነዚያ እርሷ ስትረዳቸው የነበሩ መበለቶች በየትኛው ሰዓት ብድራታቸውን እንደሚከፍሉ ተመልከት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን መበለቶቹ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ኼዱ፡፡ ጣቢታ የሰጠቻቸውን ልብስንና ሌላውን ኹሉ አሳዩት፡፡ ከእነርሱ ጋር በሕይወተ ሥጋ ሳለች ምን ምን ታደርግላቸው እንደ ነበረች ነገሩት፡፡ እንደ እናት የምትኾንላቸውን እንደ አጡ አልቅሰው ነገሩት፡፡ ስለ እነርሱ እጅግ እንዲያዝንም አደረጉት፡፡

የተወደደ ጴጥሮስስ ምን አደረገ? “ኹሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮ ጸለየ፡፡ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ ‘ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ’ አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች፡፡ ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች፡፡ እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፡፡ ምእመናንንና መበለቶችንም ጠራ፡፡ ሕያውም ኾና በፊታቸው አቆማት” (ሐዋ.9፥40-41)፡፡

የሐዋርያውን ኃይል ወይም በሐዋርያው አድሮ እግዚአብሔር ምን እንዳደረገ አስተዋልህን? በወዲያኛው ዓለምስ ተወውና በዚህ ዓለምም ሳይቀር ጣቢታ ስለ መልካም ሥራዋ ምን እንደ ተቀበለች ተገነዘብን? እርሷ ለመበለቶች የሰጠችውንና መበለቶቹም ለእርሷ የሰጡትን አየህን? እርሷ ምግብና ልብስ ሰጠቻቸው፤ እነርሱ ግን ከሞት ወደ ሕይወት እንድትመጣ አደረጓት፡፡ ለመበለቶቹ ባሳየችው ቸርነት ቸሩ እግዚአብሔር ብድራቷን ከፈላት፡፡

እንግዲህ የምጽዋት የመድኃኒትነቷን ኃይል ተመለከትህን? እንግዲያውስ እኛም ይህን መድኃኒት ለራሳችን እናዘጋጅ፡፡ መድኃኒቱ ይህን ያህል ጽኑ መድኃኒት ቢኾንም ቅሉ እጅግ ርካሽ እንጂ ውድ አይደለምና ለራሳችን እንግዛ፡፡ ይህን መድኃኒት ለመግዛት ብዙ ወጪ አይጠይቅምና እንግዛ፡፡ መልካም ሥራ መልካም የሚባለው በሚሰጡት ገንዘብ መጠን ሳይኾን በሚሰጡት የእደ ልብ ስፋት መጠን ነውና እንግዛ፡፡ አንድ ሰው አንዲት ኩባያ ቀዝቃዛ ውኃ ሰጥቶ እጅግ እንደ ሰጠ የሚቈጠርለትም እግዚአብሔር ከእያንዳንዳችን የሚሻው ወደንና ፈቅደን የምንሰጠው በጎ ፈቃዳችንን መኾኑን የሚያሳይ ነውና ይህን እንግዛ፡፡ መበለቶች፥ እንደ ጣቢታ ከሞተ ነፍስ ይታደጉን ዘንድ ይህን መድኃኒት ከእነርሱ እንግዛ፡፡

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ አምስቱ የንስሐ መንገዶች)

@mekra_abaw


የመካከለኛው ክፍለዘመን (Medieval century) የአርየንታል ኦርቶዶክስ ሊቃውንት እና ይህ ፍኖት አሁን ላይ ያለው መልክ ምን ይመስላል?

ይሄ ጊዜ ከአምስተኛው ክፍለዘመን በኋላ ያሉትን ጊዜያት ሲያጠቃልል አውሮጳውያን ዘመኑን ዘመነ-ጨለማ (Dark age) እያሉ ይጠሩታል።
ምንአልባት ለአውሮጳ ቢሆን እንጂ ጊዜው ሌላውን ዓለም ጨለማ የማያስብልም ሊሆን ይችላል።

በዚህ ጊዜ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ የዓለማችን ክፍል በነገረ-መለኮት፣በፍልስፍና፣በፊዚክስ፣በሕክምና፣በፖለቲካ፣በነገረ-ከዋክብት እንዲሁም በሌሎች የትምህርት አይነቶች እና እውቀቶች ያሸበረቀበት ጊዜ ነበር!

በዚህ የዓለማችን ክፍል በሲሪያክ በአረበኛ በፐርሽያን እና መሰል ቋንቋዎች የተጻፉ መጽሐፍት ከዚህ ዘመን በኋላ ለመጡት የዘመነ-ሕዳሴ (ዘመነ-ትንሣኤ) (Renaissance) የአውሮጳ የፍልስፍና፣የሕክምና እና የሳይንስ እውቀት ላይ የድርሻቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል በመካከለኛው ክፍለዘመን የነበሩ የመካከለኛው ምስራቅ ሊቃውንትም በዚያው በዘመነ-ህዳሴ በነበሩ እና ቀጥሎ በመጣው በዘመነ-አብርሆት (Enlightenment) ሙሕራን ሊቃውንት ላይ ተጽእኖ ፈጣሪነታቸው በቀላሉ የሚታለፍም አይደለም!

በዚያ ዘመን የነበሩ ክርስቲያን ሊቃውንት ውስጥ (የሶርያ ያዕቆባዊት ቤተክርስቲያን ምእመናን የኬልቄዶናውያንን ክርስቲያኖች እና የአሴሪያን ምስራቃዊት ቤተክርስቲያን (ንስጥሮሳውያን ክርስቲያኖችንን)ያጠቃልላል።
ቢሆንም እኛ የምንጠቅሳቸው ያዕቆባውያን ክርስቲያኖችን ነው።) ፍልስፍናን በአረቡ ዓለም ያስተዋወቁ እና እንዲሁም ሶርያውያን ክርስቲያኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ከመካከለኛው ምስራቅ ሕዝቦች ውስጥ የአርስጣጣሊስን(Aristotle) የፍልስፍና መጽሐፍት ከግርክ ቋንቋ ወደራሳቸው ሲሪያክ ቋንቋ ተርጉመው ለሌለው ዓለም የተረፉ እንደሆኑ ይነገራል።

በተለይም ለአረቡ የእስልምና ዓለም ፍልስፍና ፈለጋቸውን አኑረዋል ለዚህም በኤዴሳ የነበረችው ትምህርት ቤት አስተዋጽኦ ሲኖራት በኋላም የእነ ዮሐንስ ተአቃቢ (John of philoponus) ቅዱስ ያዕቆብ ዘኤዴሳ፣ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘአረቢያ እና መሰል ክርስቲያን ሊቃውት በአርስጣጣሊስ ላይ የሰሩት የትርጓሜ(Commentary) ሥራዎች አስተዋጽኦ ቀላል አልነበረም ሌሎች ክርስቲያን ፈላስፎችን ለመጥቀስ ያህልም ቅዱስ ዘካርያስ የህያ እብን አዳይ፣ቅዱስ ሙሴ ባርኬፋ፣የህያ እብን ጃሪር፣እብን ዙራ እንዲሁም ቅዱስ ጎርጎርዮስ ባር ሂብራዎስ አቡ ኣል-ፈረጅን እና ሌሎች ፍልሱፋንን መጥቀስ ይቻላል።

እኒህ ሊቃውንት ለየት የሚያደርጋቸው ነገር ባለብዙ እውቀት (Polymath) መሆናቸው ነው።
ማለትም የፍልስፍና ብቻ ሳይሆን የነገረ-መለኮት፣የፊዚክስ ፣የኬሚስትሪ የነገረ-ከዋክብት፣የሕክምና እና መሰል እውቀቶች ባለቤት መሆናቸው ነው።
በዚህም ምክንያት የጻፏቸው መጽሐፍት ተተርጉመው ከኋላቸው ለመጡት እና በዘመናቸው ለነበሩት ሌሎች ሊቃውንት በተለይም ለአረቡ የእስልምና ዓለም አሻራቸውን ትተዋል።
ከእስልምናውም ዓለም ፍልሱፋን ውስጥ ደግሞ
ኣል-ኪንዲን፣ኣል-ፈራቢ፣አቡ ሲና፣እብን ረሺድ (አቬሮስ)፣ኣል-ገዛሊ እና እብን ቱፋይን የመሳሰሉ አይከን ሊቃውንትን መጥቀስ ይቻላል።

በዚህ ዘመን በርካታ የአረብ እና የሶርያ ክርስቲያን የነገረ-መለኮት ሊቃውንት ተነስተዋል አጃኢብ የሚያሰኙ ጽሑፋት ተጽፈዋል ከቅዱስ ሳዊሮስ እስከ አቡ ኣል-ፈረጅ ድረስ ብዙ አጃኢብ የሚያሰኙ ሊቃውንት ተነስተዋል በዚህ ዘመን የተነሱ የነገረ-መለኮት ሊቃውንት ባለብዙ እውቀት ስለሆነ አብዛኞቹ ፍልሱፋንም ጭምር ናቸው።
ከእነርሱም ውስጥ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ
ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ፣ቅዱስ ፈሎክሲኖስ ዘማንቡግ፣ዘካሪያስ Rhetorician፣ቅዱስ ያዕቆብ ዘኤዴሳ፣ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘአረቢያ፣፣ቅዱስ ሀቢብ አቡ ራኢጣ ዘካርያስ የህያ እብን አዳይ፣ቅዱስ ዮሐንስ ዘዳራ
ዲዮናስዮስ ባር ሳሊቢ፣ሙሴ ባርኬፋ፣ቅዱስ ኪራኮስ ዘተክሪት፣ቅዱስ ጎርጎርዮስ ባር ሂብራዎስ አቡ ኣል-ፈረጅ ን ከሶርያ ስንጠቅስ ቅዱስ ሳዊሮስ አል አሽሙኒን፣እብን ኣል -አሳል፣
ቡሎስ(ጳውሎስ ማለት ነው በአረብኛ) ኣል-ቡሺ
እብን ከባርን ደግሞ ከግብጽ የአረቡ ክፍል መጥቀስ እንችላለን።
ከአርመን ክርስቲያኖች ደግሞ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘናሬክን እንዲሁም አርመንያዊው ፍልሱፍ ቶማስ አኩይናስ የሚባለውን ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘታቴቭን ማንሳት ይቻላል።

ይህን ሁሉ ማንሳት የፈለግኹት ምንያህል ቤተክርስቲያናችን በመካከለኛው ክፍለዘመን የነበሯትን ሊቃውንት ለማስታወስ እና ለማሳወቅም ጭምር ነው።
ባለንበት ዘመን የምስራቅ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት Neo patristic የሚባል እንቅስቃሴ ያመጡ ሲሆን በዚህም በመካከለኛው ክፍለዘመን የነበሯቸውን ሊቃውንቶቻቸውን እንዲታወቁ አድርገዋል በተይም ሊዮንጢየስ ዘበራንጥያን፣ሊዮንጥየስ ዘእየሩሳሌምን፣መክሲሞስ ናዛዜን፣ዮሐንስ ዘደማስቆን፣ስምኦን ሐዲስ ነባቤ መለኮትን፣ ፎጢየስ ዘቁስጥንጥንያን እንዲሁም ጎርጎርዮስ ፓላማስን እና መሰል ሊቃውንቶቻቸውን በመጽሐፍቶቻቸው በመጠቀም አስተምህሮዎቻቸውን Develop ያደረጉ ሲሆን ወደኛ ቤተክርስቲያን ስንመለስ ግን በዚህ ላይ ትልቅ ክፍተት እመለከታለሁ እንዳውም እነ ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያን እና መሰል ቤተኛ ሊቃውንቶቻችንን ተጠቅመን አስተምህሮዎቻችንን Develop ማድረግ ሲገባን የኛን አባቶች ገሸሽ አድርገን ወደ እነ ዮሐንስ ዘደማስቆ እና ኬልቄዶናውያን አበው መቀላወጥ ከጀመርን ሰነባበትን እኒህን አበው በስም እንኳ የማናውቅ ውለታቢስ ትውልዶች  እልፍ ነን!

እዚህ ፍኖት ላይ የደረስነው Neo patristic movementን ገና እየጀመርን በመሆኑ ይመስለኛል።
በዚህ እንቅስቃሴ መዘግየት እና ፍሬ አለማፍራት የተነሳ ምስራቃውያን ሳይቀሩ የእነርሱን አስተምህሮዎች የምንወስድ እስከሚመስላቸው ድረስ ደርሰናልኮ!
ምናልባትም በዚል እንቅስቃሴ ልንጠቅስ የምንችላቸው የቤተክርስቲያናችን ዘመነኛ ሊቃውንት ትንሽ ናቸው ወደፊት ይሄ እንቅስቃሴ ባለበት ከቀጠለ እኒሁ አበው ተዳፍነው ይቀራሉ እና ይሄ እንቅስቃሴ እየጎመራ እንዲሄድ እንመኛለን!
ሌላው የቤተክርስቲያናችን ምእመናን ካላቸው ርቀትም የተነሳ ያለው ክፍተትም ነው ለዚህ ያበቃን!

@mekra_abaw


ሰብህዎ በክህሎቱ (እግዚአብሔርን በከሃሊነቱ አመስግኑት) ☦☦ dan repost


ሰብህዎ በክህሎቱ (ሁሉም በችሎታው) ያገልግል☦☦ dan repost
የእመ ምዑዝ ፍቅርተ ክርስቶስ አንድነት ገዳም ጥሪ

በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ 021 ቀበሌ የምትገኘዉ የእመ ምዑዝ ቅድስት ኪዳነምሕረትና ፍቅርተ ክርስቶስ አንድነት ገዳም ጥሪ አቅርባለች።

ገዳሟ በአጼ ሱስኒዮስ ዘመነ መንግስት በኖረችው ሰማእቷ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ የተመሠረተች ሲሆን በሰሜን ወሎ ከሚገኙ 25 አንድነት ገዳማት መካከል አንዷ ነች።

እንደ ገዳሙ አበምኔት ንቡረ እድ መ/ር ቆሞስ አባ ወልደትንሳኤ ገብረሥላሴ ሞላ ገለጻ በአሁኑ ወቅት ገዳሟ ከፍተኛ አደጋ ከፊቷ ተጋርጧል።

በርካታ በጸሎት እና በቅድስና የጸኑ ባሕታዉያን አባቶች እንደዚሁም እናቶች የሚገኙባት ይህች ገዳም አሁን ላይ በጎርፍ አደጋ ምክንያት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ናት እናም ትብብራችሁን እንሻለን ሲሉ የገዳሙ አበምኔት ንቡረ እድ መ/ር ቆሞስ አባ ወልደትንሳኤ ገብረሥላሴ ሞላ ተናግረዋል።

አክለውም የገዳሟ ቤተመቅደስ የታነጸው በገደሉ አፋፍ ላይ እንደመሆኑ መጠን በጎርፍ አደጋ እና በመሬት ናዳ ምክንያት ለአደጋ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋልጧል ብለዋል።

በገዳሟ አጽመ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ እና የሌሎች ቅዱሳት አጽም የሚገኝበት ታላቅ ቦታ መሆኑን ያስረዱት የገዳሟ አበምኔት
በአደጋው ምክንያት እነዚህን በረከቶቻችንን እንዳናጣ አስቸኳይ መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ብንረዳም ለእኛ ግን ከአቅማችን በላይ ስለሆነብን ለሕዝበ ክርስትያኑ ጥሪ ለማድረግ ተገደናል ብለዋል።

ስለሆነም በመላዉ ዓለም የምትኖሩ የመንፈስ ልጆቻችን በሙሉ የአቅማችሁን እንድትረዱንና አጽመ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ እና የሌሎች ቅዱሳት አጽም በጎርፍ ከመወሰድ እንድትታደጉልን ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ለዚህም ኅዳር 29/ 2017ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ አዲስ አበባ ሜክሲኮ በማኅደረ ስብሐት ቅ/ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ስብከተ ወንጌል በሚያዘጋጀው ጉባዔና የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ ተገኝተው የተቻላችሁን እንዲያደርጉና ገዳሟን ከመጥፋት አባቶች እና እናቶችንም ከጭንቀት ትታደጉ ዘንድ ተጋብዘዋል።

በዕለቱም ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ የገዳሙ አባቶች እና እናቶች እንዲሁም ታላላቅ መምህራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ።
በዚህ እለት ሑሉም ምዕመናኖች እንድትገኙ ገዳሟ ጥሪዋን አስተላልፋለችለገዳሟ እርዳታ ማድረግ ለሚፈልጉ በገዳሟ የተከፈቱ የባንክ የሂሳብ ቁጥሮች ገቢ ማድረግ ይቻላል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
〽 1000076665285
አቢሲኒያ ባንክ
〽 8089205


እነዚህን መግዛት የሚፈልግ @habmisget ላይ ያናግረኝ




ያም ወጣት መጋቢውን መልኩ እንዴት ነው ምን ይመስላል አለው መጋቢውም አካሉ አንተን ይመስላል አለው ይህንንም ብሎ ወደ ሥዕሉ ወስዶ ገልጦ አሳየው ወጣቱም በእገሌ በረሀ የታየኝ በእውነት ይህ ነው። በፈረሱም ላይ አፈናጥጦ ወደዚህ ያደረሰኝ ይህ ነው። እነሆ ታጥቋት በወገቡ ላይ ያየኋት የወርቅ መታጠቂያው ይቺ ናት። ስማኝ ልንገርህ እኔ በዚች አገር የምኖር አባቴም ስሙ ረጋ የሚባል መስፍን የሆነ እስላም የሆንኩ ሰው ነኝ። ክርስቲያንም ለመሆን ይች ምልክት ትበቃኛለች አሁንም በቦታ ውስጥ ሠውረኝ ለማንም ሥራዬን አትግለጥ። የክርስትና ትምህርትን አስተምሮ የእግዚአብሔርን መንገድ የሚመራኝን አምጣልኝ አለው። እርሱም ያለውን ሁሉ አደረገለት የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቀው።

ከዚህም በኋላ ወደ ነቢያቸው መቃብር የሔዱ እሊያ እስላሞች በአንድ ወራቸው ደረሱ። ዘመዶቻቸውም ሊቀበሏቸው ወጡ። ይህን ወጣት የመስፍን ልጅ ግን አላገኙትም። አባቱም አደራ ያስጠበቀውን ወዳጁን በጠየቀው ጊዜ እርሱም በበረሀ ውስጥ ቀርቶ እንደ ጠፋ እያለቀሰ ነገረው አባቱም በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀዶ አለቀሰ እንዲሁም ቤተሰቦቹ ሁሉም አርባ ቀኖች ያህል አለቀሱለት።

ከዚህም በኋላ በጥዋት ከቤተ ክርስቲያን ሲወጣ ይህን ክርስቲያን የሆነውን ወጣት አንድ እስላም አየው። ወደ ወላጆቹም ሒዶ እንዲህ ብሎ ነገራቸው ልጃችሁ በበረሀ ውስጥ የሞተ ከሆነ በመርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ያየሁት እርሱን ባልመሰለኝ ነበር፤ እስቲ ሒዳችሁ አረጋግጡ። በሰሙም ጊዜ በስውር ሒደው ፈለጉት አግኝተውትም ይዘው ወሰዱት። እንዲህም አሉት በወገኖቻችን መካከል ልታሳፍረን ይህ የሠራኸው ምንድን ነው አሉት። እርሱም እኔ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታዬና በፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝ ብሎ መለሰላቸው።

ይህንንም ሲል ታላቅ ሥቃይን አሠቃይተው ከጨለመ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት። ሽንታቸውን በላዩ እየደፉ የቤት ጥራጊም እያፈሰሱበት ያለ መብልና ያለ መጠጥ በዚያ ሰባት ቀንና ሌሊት ኖረ። እናቱ ግን ቀንም ሌሊትም በላዩ የምታለቅስ ሆነች ከልቅሶዋም ብዛት የተነሣ ከጉድጓድ አውጥተው እኛ ወደማናይህ ቦታ ሒድ አሉት። ወዲያውኑ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሒዶ በዚያ እያገለገለና እየተጋደለ ሁለት ዓመት ኖረ።

ከዚህም በኋላ በላዩ የትንቢት ጸጋ ያደረበት አንድ መነኰስ ወደ ምስር ከተማ ሒደህ ሃይማኖትህን ከምትገልጽ በቀር በዚህ መኖር ለአንተ አይጠቅምህም አለው። ወዲያውኑ ተነሥቶ ወደ ምስር ከተማ ሔደ።

አባቱም በአየው ጊዜ ሐኪም ወደ ሚባል ንጉሥ ወስዶ ይህ ልጃችን ነበር የእስልምና ሃይማኖትን ትቶ ወደ ክርስቲያን ሃይማኖት ገብቷል አለው። ንጉሡም ስለአንተ የሚናገሩት ዕውነት ነውን አለው። እርሱም በበረሀ ውስጥ ሳለ በሌሊት ቅዱስ መርቆሬዎስ እንደ ተገለጸለትና ከእርሱ ጋር በፈረስ እንዳስቀመጠው፣ በምስር አገር ወዳለች ቤተ ክርስቲያኑ የሃያ ሁለት ቀን መንገድ እንደ ዐይን ጥቅሻ አድርሶ ከውስጥዋ እንዳስገባው፣ ሥዕሉንም አይቶ ያመጣው እርሱ መሆኑን እንደ ተረዳ ለንጉሡ ነገረው።

ንጉሡም በሰማ ጊዜ እጅግ አደነቀ። ታላቅ ፍርሀትም አደረበት አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምነኝ አለው። እርሱም በቅዱስ መርቆሬዎስ ስም ዳግመኛም በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን እንድሠራ ታዝልኝ ዘንድ እሻለሁ አለው።

ንጉሡም በአስቸኳይ እንዲታነፁለት አዘዘለት። በውስጣቸውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ። እርሱም አበ ምኔት ሁኖ ወደርሱ ብዙዎች መነኰሳት ተሰበሰቡ። ሁለት ድርሳናትንም ደረሰ። ከሀዲያንንም አስተምሮ ወደ ቀናች ሃይማኖት መለሳቸው እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ። ለዚህም መነኰስ የክርስትና ጥምቀትን በተቀበለ ጊዜ ያወጡለት ስም ዮሐንስ ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ መርቆሬዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር)

@mekra _abaw


#ተአምር_ዘቅዱስ_መርቆሬዎስ - ፩

ከተአምራቱም አንዲቱ ዑልያኖስ በነገሠ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ካደ። በዚያንም ወራት ቅዱስ ባስልዮስ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ነበረ ተአምራቱ በተጻፉበት መጽሐፍ እንደተጻፈ ምእመናን በጽኑዕ ሥቃይ ዑልያኖስ ባሠቃየ ጊዜ መክሮ አስተምሮ ከስሕተቱ ይመልሰው ዘንድ ቅዱስ ባስልዮስ ወደርሱ መጣ።

ዑልያኖስም ቅዱስ ባስልዮስን በአየው ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችንን ሰደበ። ቅዱስ ባስልዮስንም አሠረው። በዚያ በእሥር ቤትም የቅዱስ መርቆሬዎስን ሥዕል አይቶ በፊቱ ቅዱስ ባስልዮስ ጸለየ ሥዕሉም ከቦታው ታጣ። ያን ጊዜ ወደ ዑልያኖስ ሒዷልና በጦርም ወግቶ ገደለውና ወዲያውኑ ወደቦታው ተመለሰ ከጦሩም አንደበት ደም ይንጠፈጠፍ ነበር። ቅዱስ ባስልዮስም ከሀዲ ዑልያኖስን እንደገደለው አውቆ እንዲህ ብሎ ተናገረ የክርስቶስ ምስክር ሆይ የእውነት ፀር የሆነ ዑልያኖስን ገደልከውን ያን ጊዜ አዎን እንደሚል ሥዕሉ ራሱን ዘንበል አደረገ ቅዱስ ባስልዮስም ደስ ብሎት እግዚአብሔርን አመሰገነ።




#ተአምር_ዘቅዱስ_መርቆሬዎስ - ፪

የዚህም የቅዱስ መርቆሬዎስ ሌላው ተአምር ከምስር አገር ከመሳፍንት ወገን የሆነ አንድ የእስላም ወጣት ነበረ የእስላሞችንም ሕጋቸውንና መጻሕፍቶቻቸውን ተምሮአል። በአንዲትም ዕለት ወደ ባሕር ዳርቻ በመንገድ አልፎ ሲሔድ አንድ የተፈረደበትን ሰው አገኘ። አስቀድሞ እስላም የነበረ አሁን የክርስትና ጥምቀትን የተጠመቀ የንጉሥ ጭፍሮችም ይዘውታል። ሊአቃጥሉትም ጉድጓድን ምሰው በውስጡ ታላቅ እሳት አንድደው አዘጋጅተውለታል። ብዙዎች ሰዎችም ሲቃጠል ለማየት ተሰብስበው ነበር።

ያም የመስፍን ልጅ ወጣት እስላም ወደ ተፈረደበት ሰው ቀረብ ብሎ "አንተ ከሀዲ ሰው ወደ ሲኦል ለመግባት ለምን ትሮጣለህ በኋላም በገሀነም እሳት ውስጥ ለመኖር አንተ እግዚአብሔርን ባለ ልጅ ታደርገዋለህና ሦስት አማልክትንም የምታምን ነህና ክፉ ነገር ነውና ይህን ስድብ ትተህ እኔን ስማኝ" አለው ።

ያ የተፈረደበትም እንዲህ ብሎ መለሰለት "እኛ የክርስቲያን ወገኖች ሦስት አማልክትን የምናመልክ ከሀድያን አይደለንም። አንድ አምላክን እናመልካለን እንጂ ይኸውም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው። ወልድ ከአባቱ ከእግዚአብሔር ልዩ አይደለም። የራሱ ቃሉ ነው እንጂ። መንፈስ ቅዱስም ሕይወቱ ነው። የሃይማኖታችን ምሥጢር ከአናንተ የተሠወረ ድንቅ ነው። ዛሬ ለአንተ ልብህ ጨለማ ነው በውስጡ የሃይማኖት ብርሃን አልበራም በኋላ ግን ልብህ በርቶልህ እንደ እኔ ስለ ክርስቶስ ስም በመጋደል መከራውን ትቀበላለህ።"

ያም ወጣት እስላም በሰማው ጊዜ እጅግ ተቆጣ ጫማውንም ከእግሮቹ አውልቆ አፉን ፊቱንና ራሱን ጸፋው። ይህ የምትለው ከእኔ ዘንድ አይደረግም እያለ አብዝቶ አሠቃየ። የተከበረው ሰማዕትም ይህን ያልኩህን አስበህ የምትጸጸትበት ጊዜ አለህ አለው።

በዚያንም ጊዜ ራሱን በሰይፍ ቆርጠው ሥጋውን ከእሳት ማንደጃ ውስጥ ጨመሩ ከዚህም በኋላ እሳቱ ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ታላቅ አጥር ሆነ። የንጉሥም ወታደሮች እየጠበቁት ሦስት ቀን ኖረ። ከዚህም በኋላ ከቶ እሳት ምንም ሳይነካው እንደ ተፈተነ ወርቅ ሆኖ ሥጋውን አገኙት። ይህንንም ለንጉሥ ነገሩት። እርሱም እንዲቀብሩት አዘዘ።

ያ ወጣት እስላም ግን እያዘነ ወደ ቤቱ ገባ እርሱ ክርስቲያን እንደሚሆን ስለተናገረው ከኀዘኑ ብዛት የተነሣ የማይበላና የማይጠጣ ሆነ። እናቱና ወንድሞቹም ወደርሱ ተሰብስበው የማትበላ የማትጠጣ በአንተ ላይ የደረሰ ምንድን ነው አሉት። ክብር ይግባውና ለጌታችን ኢየሱስ ምስክር የሆነው የተናገረውን ነገራቸው። እነርሱም ይህ አሳች የተናገረውን ተወው በልብህ አታስበው እያሉ አጽናኑት። እርሱ ግን ከቶ ምንም አልተጽናናም።

በዚያም ወራት ወደሐሰተኛ ነቢያቸው መቃብር ለመሔድ የሚሹ ሰዎችን አይቶ ከእሳቸው ጋር መሔድ እፈልጋለሁ ብሎ ለአባቱ ነገረው። አባቱም እጅግ ደስ ብሎት የሚበቃውን ያህል የወርቅ ዲናር ሰጠው ለወዳጁም አደራ ብሎ ሰጠውና አብሮት ሔደ።

በሌሊትም ሲጓዙ እነሆ ብርሃን የለበሰ አረጋዊ መነኰስ ተገለጸለት በፊቱም ቁሞ ትድን ዘንድ ና ተከተለኝ አለው እንዲሁም ሁለተኛና ሦስተኛ ተገልጦ ተናገረው።

በደረሱም ጊዜ ሥራቸውን ፈጽመው ወደ አገራቸው ተመለሱ ሰባት ቀንም ያህል ተጓዙ። እነርሱም በሌሊት ሲጓዙ ስለ ሥጋዊ ግዳጅ ያ ወጣት ከገመል ላይ ወርዶ ለመጸዳዳት ዘወር አለ። ባልንጀሮቹም በበረሀ ውስጥ ትተውት ሔዱ ከእሳቸው ጋር የሚጓዝ መስሏቸዋልና በተነሣም ጊዜ ተቅበዘበዘ ወዴት እንደሚሔድ አላወቀምና አራዊትም እንዳይበሉት ፈርቶ ደነገጠ።

በዘያንም ጊዜ በምስር አገር በአባቱ ቤት አቅራቢያ ያለች የሰማዕት የቅዱሰ መርቆሬዎስን ቤተ ክርስቲያን አስታውሶ በልቡ እንዲህ አለ። ሰዎች ሁሉ በእርሷ ዘንድ እየተሳሉ ይፈጸምላቸዋል። በዚያንም ጊዜ የክርስቶስ ምስክር መርቆሬዎስ ሆይ በዚህ በረሀ ካሉ አራዊት አፍ በዛሬዋ ሌሊት ካዳንከኝና ያለ ጥፋት ካወጣኸኝ እኔ ክርስቲያን እሆናለሁ ብሎ ተሳለ።

ወዲያውኑ መልኩ የሚያምር ጎልማሳ የከበረ ልብስ የለበሰና የወርቅ መታጠቂያ በወገቡ የታጠቀ በፈረስ ተቀምጦ ወደርሱ መጣና አንተ ከወዴት ነህ እንዴት በዚህ በረሀ ውስጥ ጠፋህ አለው። ወጣቱም ስለ ሥጋ ግዳጅ ከገመል ላይ ወረድኩ ባልነጀሮቼ ትተውኝ ሔዱ አለው ባለ ፈረሱም ና በኋላዬ በፈረሱ ላይ ተፈናጠጥ አለው በዚያንም ጊዜ ወደ አየር በረረ በምስር አገር ወዳለች የቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን እንደ ዐይን ጥቅሻ አደረሰውና እንደተዘጋች ከውስጧ አስገባው። ከፈረሱም ላይ አውርዶ በዚያ አቆመው ወደ መጋረጃ ውስጥም ገብቶ ከእርሱ ተሠወረ።

የቤተ ክርስቲያኑም መጋቤ በሌሊት በመጣ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከፍቶ ሲገባ ይህን ወጣት ከመካከል ቁሞ አገኘው። ደንግጦ ሊጮህ ፈለገ ጠቀሰውና ወደኔ ዝም ብለህ ና አለው ወደርሱም ሲቀርብ ይቺ ቦታ የማናት አለው የቤተ ክርስቲያኒቱ መጋቢም ይቺ በምስር አገር ያለች የቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ናት። አንተን ግን ልቡ እንደ ጠፋ ሰው ስትናገር አይሃለሁ ከዚህ ምን አመጣህ አሁንም ንገረኝ አለው። ወጣቱም እንዲህ ብሎ መለሰለት ልቤ እንዴት አይጠፋ እኔ በዛሬው ሌሊት በእገሌ በረሀ ሳለሁ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ሰው ተገለጠልኝና ከኋላው በፈረሱ አፈናጠጠኝ ከዚህም አድርሶ ተወኝ አለው።

መጋቢውም የዚያችን በረሀ ስም በሰማ ጊዜ አደነቀ እንዲህም አለው ልብህ ጠፍቷል በማለቴ መልካም የተናገርኩህ አይደለምን የምትናገረውን አታውቅምና የዚያ በረሀ መጠኑ የሃያ ሁለት ቀን ጉዞ የሚያስጉዝ ስለ ሆነ በእርግጥ አንተ ወንበዴ ነህ የቅዱስ ሰማዕት መርቆሬዎስ ኃይል ያለ ገመድ አሥሮሃል፣ እርሱ የዚህን ዓለም ክብር ንቆ የተወ፣ ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ስም ከሀዲዎች ጽኑ ሥቃይ አሠቃይተው የገደሉት፣ ክርስቶስም በመንግሥቱ ውስጥ የተቀበለው፣ በቦታዎችም ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ታነፁለት በውስጣቸውም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። እርሱ መርቆሬዎስ ለተማፀነበት ሁሉ ይማልዳልና ድንቆች የሆኑ ታላላቅ ተአምራትንም ያደርጋልና።


"ከሁለቱ የጽድቅ እንቅፋቶች እናስተውል"!

       ፩.ጸድቄአለሁና
       ፪. አልጸድቅም

ጸላኤ ሠናያት ሰውን የሚጎዳበት ሁለት ወጥመዶች  አሉት። አንዱ ጸድቂያለሁ ማሰኘት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አልጸድቅም ማሰኘት ነው። በሁለቱም ምክንያቶች ጽድቅ መሥራት አይቻልም። ጸድቄያለሁ የሚያሰኛቸው መናፍቃንን ነው። ለምን ሲባሉ ጌታን እወደዋለሁና ይላሉ። አምናለሁና ይላሉ።

ጌታን ስለምወደው ጸድቄያለሁና ጽድቅ አልሠራም የምትል ከሆነ የምትድን አይምሰልህ። ለምን ትለኝ እንደሆነ ጌታ ራሱ በመውደድ ብቻ አላዳነንምና። እወዳችሁአለሁና ዳኑ ብሎ በዙፋኑ ተቀምጦ ትእዛዝ ሰጥቶ አልቀረም።
ወዶ ምን አደረገ ትለኝ እንደሆነ፦

ምሉዕ ስፉሕ  ጌታ በጠባብ ደረት በአጭር ተወሰነ። ሰማይን በደመና የሚሸፍነው በጨርቅ ተጠቀለለ።
ከነደ እሳትነቱ የተነሳ ኪሩቤል የሚንቀጠቀጡለት በብላቴናዋ በድንግል ማኅፀን ተወሰነ። ምድርና ሰማይን የሚያቀልጣቸው የክብር መብረቅ በክንደቿ ታቀፈችው። በፊቱ የእሳት ጎርፍ የሚንቆረቆርለትን በከንፈሮቿ ሳመችው። አገልጋዮቹን የእሳት ነበልባል የሚያደርገውን  እንዳይበርደው እንስሶች አሟሟቁት። አዳራሹን በመብረቅ የሠራው በበረት ተኛ። ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን የተሠወረው ቅጠል ለበሰ። የስደተኞች ተስፋ ተሰደደ። የሰማይና የምድር አባት በየጥቂቱ አደገ። ምድርን በደሙ የሚያነጻት ማይን ያነጻት ዘንድ ተጠመቀ። የዓለማት ዓለም ማደሪያ አጥቶ ቀን በምኩራብ ሌሊት በተራራ ተንከራተተ። የመምህራን አምላክ ለማይሰማ ሕዝብ በሰው ቃል ዝቅ ብሎ አስተማረ። ለመምህራን  በሞገስ መከበርን የሰጠ እየተሰደበ አስተማረ። መላእክት እያመሠገኑ ለማመስገን የሚሳሡለት የአይሁድን ጽርፈት ሰማ። ለተበደሉት የሚፈርድላቸው በፍርድ አደባባይ ቆመ። ከፍርድ የሚያድነው ተፈረደበት። እስረኞችን የሚፈታ ታሰረ። ሰውን ወደ ሰማይ በልዕልና ስቦ የሚያሳርገውን ጎተቱት። መንሥኤ
ሙታኑን ጣሉት። ቁስለኞችን የሚፈውሰውን ቸንክረው አቆሰሉት። ራሱን ሊያለብስ የመጣውን አራቆቱት። ርኩሳኑን በደሙ ያጠበውን ርኩስ ምራቅ ተፉበት።የኃጢአትን እሾህ የሚነቅለውን የእሾህ አክሊል ደፉበት። የሕይወትን ውኃ መራራ አጡጡት። ዲያብሎስን በመስቀሉ የቸነከረውንበጦር ወጉት። ሕይዎት እርሱን ሰቅለው ገደሉት። የምድር መሠረት የሰማይን ጽንዓት በምድር ውስጥ ተቀበረ። ትንሣኤና ሕይወት ነውና ሞትን በሞቱ ደምስሶ ተነሣ!

ወደጄ ሆይ ጌታን ስለምወደው ስለማምነው ጸድቄያለሁ የምትል ከሆነ እንዲህ ብሎ ሲጠይቅህ ምን ትመልስለታለህ? ልጄ ሆይ እኔ አንተን ወድጄ ተሰቀልኩልህ።አንተ እኔን ወደህ ምን ሆንህልኝ?በዚህ ጊዜ ስለምወድህ ትጋት ትቼ ሰነፍሁልህ ልትለው ነው? ሁሉን የሚችል አምላክ በቃሉ ብቻ ማዳን እየቻለ ነገር ግን ፍቅሩን በመከራ ገልጦ ካዳነ ሰው ለአምላኩ ቃል ብቻ እንዴት ይበቃዋል?

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወረቅ እንዲህ ሲለን እንስማ!         
"ኢትበል እፈቅድ ባሕቲቱ=ወዳጄ እወዳለሁ ብቻ አትበል"ዋናተኛ ዋና እወዳለሁ በማለት ወንዝ ይሻገራልን?ሐናጺ መሆን የሚሻ ቤት መስራት በመፈለግ ብቻ ሙያውን ሳይለምድ ቤት መስራት ይችላልን? መርከበኛ መሆን የሚሻ መርከብ መቅዘፍን ሳይለምድ ሊቀ ሐመር መሆን ይችላልን?ጸሐፊስ መጻፍ በመፈለግ ብቻ ፊደል ሳያውቅ መጻፍ ይችላልን? መንጻት የሚፈልግስ ሳይታጠብ በመፈለግ ብቻ ይነጻልን? የተራበስ ስለ ምግብ በማሰብ ብቻ ይጠግባልን? ጽድቅንስ በመሥራት እንጅ በመውደድ ብቻ መዳን ይቻላልን?

ሁለተኛው ደግሞ  አልጸድቅም ማለት ነው።
እንደዚህ የሚያሰኛቸው ደግሞ ምእመናንን ነው። መጀመሪያ ጥቂት ጥቂት እያለ ከጽድቅ ስራ ያወጣቸዋል። ከዚያ እግዚአብሔር መሐሪ ነው እያሰኘ ኃጢአት እንዲጨምሩ ያደርጋቸዋል። ከዚያ ወዲያ ፍጹም ኃጢአተኛ ሲሆኑ በኋላ እንዳይመለሱ መቼም አልጸድቅ ያስብላቸዋል።

የእመቤ ታችን ልጆች ንቁበት። ላልጸድቅ ሲያሰኛችሁ ክርስቶስ የውበት ባሕር ነው ብላችሁ መልሱለት። በአንዲት ውኃ ብዙ ሰዎች ቢታጠቡ ትደፈርሳለች። ክርስቶስ ግን የጎሰቆሉ ሁሉ ወደ እርሱ ገብትው ሲነጹ የእነርሱ ጉስቁልና እርሱን የማይለውጠው የምሕረት ባሕር ነውና እየገባን እንንጻ! በጭቃ የተለወሰውን ወርቅ ወልውለው አጥርተው ለአክሊልነት ያበቁታል። በእግር ከሚረገጥ ጭቃ በታች የነበረውን አጥርተው ከራስ በላይ ያውሉታል። ከምእመንነት በታች ወርዶ ጌታውን የካደውን ቅዱስ ጴጥሮስን በንስሐ ጠርቶ ርእሰ ሐዋርያት እንዳደረገው  አትዘንጋ! እግዚአብሔር ቸር ነው ብሎ ኃጢአት መስራት ነው እንጅ ክፉ
እግዚአብሔር ቸር ነው እያሉ መመለስ ያድናል።

አሁንም ተስፋ ቆርጠን አንዘግይ! ለመመለስ ያብቃን!ደግሞ ማንንም የማትጸየፍ እናት አለችን።                                    ምን ብንገዳገድ እርሷን እየተመረኮዝን እንነሳ!( በትረ ሃይማኖት ድንግል ማርያም)

ርዕሰ_ሊቃውንት_አባ_ገብረ_ኪዳን

@mekra_abaw✝️❤️🙏


"ጽዮንን ክበቧት"  መዝ.፵፯፥፲፪

መጽሐፈ ኦሪት ዘፀአት የታቦተ ጽዮንን ነገር እንዲህ ይተርከዋል። ሙሴ እስራኤልን ከካራን ወደ ከነዓን ይዞ ሲወጣ በሲና ተራራ  ፵ መዓልትና ሌሊት ከዘረጋ ሳያጥፍ ከቆመበት ሳይቀመጥ በፍጹም ጽሙና ሁኖ በጾምና ጸሎት እግዚአብሔርን ጠየቀው። የለመኑትን የማይነሣ የጠየቁትን የማይረሳ እግዚአብሔርም ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፈበትን ሁለት ጽላት ለሙሴ ሰጠው። ሙሴም ወደ ሕዝበ እስራኤል ይዞ ወረደ። እስራኤል አሮንን አስገድደው፤ በጌጦቻቸው የጥጃ ምስል ያለው ጣዖት ሠርተው እያመለኩ ቢጠብቁት ሙሴ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ታቦት ሰበረ። ዳግመኛም እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ቀድሞዎቹ አድረገህ ቅረጻቸው ብሎ ጽላትን እንዲያዘጋጅ አስተማረው። ሙሴም እንደታዘዘው አድርጎ ሠራ። (ዘፀ.፳፬ እና ፳፭) ‹‹ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ሙሴ ጽላቶቹን ባይሰብር ጽላትን መሥራት እንዴት ይቻል ነበር? (ሮሜ ፰፥፳፰)

ለ፭፻ ዓመታት ገደማ በእስራኤል ብዙ ገቢረ ተአምራትን ስታደርግ የነበረችዋ ይህች በሙሴ የተቀረጸች ታቦት በቀዳማዊ ምኒልክ በኩል ለኢትዮጵያ ተሰጠች። (መጽሐፈ ክብረ ነገሥትን ሙሉውን ያንብቡ) የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች ስለ አመጣጧ እንዲህ ያስነብበናል፤   ‹‹በማእከላዊ ትግራይ አክሱም ሀገረ ስብከት አክሱም ከተማ የምትገኘው ታቦተ ጽዮን በቀዳማዊ ምኒልክ ከኢየሩሳሌም መጥታ በምኩራብ ትኖር ነበር። ይህም ከጌታ ልደት በፊት ፱፻ ዓመት ገደማ ነው።›› (የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች፣ በሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት፣ ገጽ ፪፻፭)

በምኩራብ ብትቆይም አብርሃ እና አጽብሐ የተባሉት ነገሥታት ፲፪ መቅደስ ፸፪ አዕማድ ያላት የመጀመሪያዋን ቤተ ክርስቲያን አሠርተውላታል። ቀጣዩ ቤተ መቅደስ በዐፄ አንበሳ ውድም ተሠርቷል፤ ይህን ደግሞ ግራኝ አቃጠለው፤ መልሰውም ዐፄ ፋሲል አሠርተውታል፤ አሁን ያለውን ደግሞ በዘመናዊ መንገድ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አሠርተዋል፤ ይህን ተከትሎም የጽዮን በዓል በታላቅ ድምቀት ኅዳር ፳፩ ይከበራል።

ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር ናት ከምትባልባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ የጽላተ ሙሴ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ኅዳር ፳፩ ቀን በታላቅ ክብር ታከብረዋለች፡፡ በዚሁ ዕለት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወዳጆች ምእመናን በዓሉን ለማክበርና ለመሳለም ወደ አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን በብዛት ይገሠግሳሉ፡፡ ዕጣን፣ ጧፍ፣ ዘቢብና መባ ይሰጣሉ፡፡ ካህናቱም ከዋዜማው ጀምረው በከበሮና በጸናጽል ስብሐተ እግዚአብሔር ያደርሳሉ፡፡ በድርሳነ ጽዮን መጽሐፍ እንደተገለጠው በጽዮን ፊት እንደ የመዓርጋቸው ቆመው ‹‹ዕግትዋ ለጽዮን ወህቀፍዋ፤ ጽዮንን ክበቧት፥ በዙሪያዋም ተመላለሱ›› የሚለውን መዝሙር ከዳዊት እያወጣጡ ይጸልያሉ፤ ይዘምራሉ፡፡ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ የታቦተ ጽዮንን ተራዳኢነት በምእመናን ፊት ይመሰክራሉ፡፡ (መዝ. ፵፯፥፲፪)

ታቦት የአመቤታችን ምሳሌ ነውናም ነቢያት ስለ ክርስቶስ በተለያየ ኅብረት፣ ትንቢትና አምሳል እንደ ተናገሩ ሁሉ ክርስቶስ ስለሚገኝባት አማናዊት ድንግል ማርያምም ተናግረዋል፤ እግዚአብሔር ወልድ ወደዚህ ዓለም በሥጋ ማርያም ከመገለጡ በፊት ከእግዚአብሔር ተልከው ሕዝቡን ከአምልኮተ ጣዖትና ከገቢረ ኃጢአት እንዲጠበቅ የሚመክሩ፣ የሚያስተምሩና የሚያጽናኑ ነበሩ፡፡ (ሉቃ.፲፮፥፲፯፣ኢሳ.፵፥፩፣ኢሳ.፵፬፥፩-፲፩) የነቢያት ትንቢት ዋናው ዓላማም እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቡን እንደተዋቸው እንደማይቀር፣ ወደዚህ ዓለም መጥቶ. ሰው ሆኖ ተገልጦ. ወንጌልን አስተምሮና ስለ እኛ መከራን ተቀብሎ እንደሚያድነን መግለጥ ነበር፡፡ በዚህም ስለ እግዚአብሔር ማደረያ እመቤታችን ትንቢት ተናግረዋል፡፡ (ኢሳ.፯፥፬፣ማቴ.፩፥፳፫፣ሚክ. ፭፥፪)

በታቦት ሰሌዳ ላይ ‹አልፋ ወዖ› የሚለው ስመ እግዚአብሔር እንደተቀረጸ ሁሉ በአማናዊቷ ታቦት በእመቤታችን ማሕፀንም ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀርጿል። በዚህ ዕለት በኢትዮጵያ የሚከበረው ታቦተ ጽዮን ባለችባት አክሱም ብቻ አይደለም። በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም በታነጹ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በተለያዩ ቦታዎች ይከበራል።

ስለዚህም ተወዳጆች ሆይ! ጽዮንን እንክበባት! በእርሷ ምልጃና ጸሎት እንዲሁም ተራዳኢነት አምላካችን እግዚአብሔር ምሕረቱን ያወርድልን፣ ሰላምና ፍቅር ይሰጠን ዘንድ!

የአምላካችን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የቅድስት ድንግል ማርያም አምላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!

@mekra_abaw✝️❤️🙏




https://www.youtube.com/live/7t-_wAk-F9E?si=wo9Lj-hvFqS33_07


ወደ አኩስም ጉዞ መሄድ የምትፈልጉ የመጨረሻ ምዝገባ ዛሬ የአምስት ሰው ብቻ ቦታ አለ

+251988232340

ምግብን ጨምሮ 3200
ያለ ምግብ 2000 ብር
ደብረ ዳሞ በጉብኝቱ አብሮ ይካተታል


ይኸው ተወለደ

ይኸው ተወለደ የዓለም መድኀኒት /3/
እሰይ ተወለደ የዓለም መድኀኒት /3/
አዝ

ትንቢት ተናገሩ ነቢያቱ ሁሉ /3/
አምላክ ቀዳማዊ ይወርዳል እያሉ /3/
አዝ

ሰብአ ሰገል መጡ ሊሰግዱ በሙሉ /3/
የእስራኤል ንጉሥ ተወልዷል እያሉ /3/
አዝ

ሰብአ ሰገል መጡ እጅ መንሻ ይዘው /3/
ወርቅ ዕጣን ከርቤውን ገበሩለት ሰግደው /3/
አዝ

ምዕመናን እንሂድ ከልደቱ ቤት /3/
ውኃው ሆኗልና ማርና ወተት /3/
አዝ

በሶርያ ታየ ፈጣሪ እንደ እንግዳ /3/
ብሥራተ ልደቱን ለሁሉ ሊያስረዳ /3/

የአእላፋት ዝማሬ መዝሙር ጥናት
ለሁሉም ሼር በማድረግ አዳርሱ!

💚 @mekra_abaw


+  ከአሸናፈዎች እንበልጣለን  +

ቅዱስ ጳውሎስ ኃጢአታችንን በደሙ ባጠበልን በእርሱ በተሰቀለው በልዑል ክርስቶስ ከአሸናፈዎች እንበልጣለን አለ ። እነርሱ የማይሰሩትን ስራ እኛ እንሰራለን ። ብዙ ታላላቅ ጦር ሜዳ ድል ያደረጉ ጀኔራሎች ( ታላላቅ የጦር ሰዎች ) ልባችንን ማሸነፍ አይችሉም ። ይኸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ታውቋል። አንዱን ወጣት የሃይማኖት ገበሬ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሰባው ነገስታት ከነሰራዊቶቻቸው ሊያሸንፍት አልቻሉምና ። እርሱ ድል አደረጋቸው እንጂ ፤ በእርሱ ጸሎት ሁሉንም እሳት በላቸው ፣ እርሱ ግን ማንም ድል ሊያደርገው ሊያሸንፈው አልቻለም ። ብዙ መከራ ቢያጸኑበትም ፤ ስጋውን አቃጥለው አመድ አድረገው ቢበትኑበትም ቅሉ ፤ ሃይማኖቱ አስነሳው ። መድኃኔ ዓለም ተገልጦ "ወዳጄ ጊዮርጊስ ሆይ ተነስ " አለው። ቅዱስ ጊዮርጊስ  ድል ያደረገው በወደደው በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ነው ። ጠላቶቹ ገደልነው ፣ አሸነፍነው ፣ ቆራረጥነው ፣ በተንነው ፣ ጠብስነው ፣ አቃጠልነው ፣ ሲሉ በወደደው በፈጣሪው በኢየሱስ ኃይል ከሙታን ብድግ ይልና ፤ ከጫጉላ ቤት እንደ ወጣ ሰው ታድሶ ፣ ለምልሞ እንደገና ሄዶ ይገጥማቸዋል ። ሶስት ጊዜ ገደሉት ሶስት ጊዜ ተነሳ ፣ በአራተኛው በእግዚአብሔር ፍቃድ ነብሱ ከስጋው ተለየች ። ነገር ግን መጀመርያ አነርሱን አጥፋቶ ነው ፤ እሳት ከሰማይ ወርዶ ጠላቶቹን አጥፍቶ  ሲያበቃ በሰይፍ ተሰየፈ ፤ ከአንገቱም ደም ፣ ውኃ ፣ ወተት ፈሰሰ። (ገድለ ጊዮርጊስ ) ስለዚህ በወደደን በእርሱ በኃያሉ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ከአሸናፈዎች እንበልጣለን ።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ (በሃይማኖት የሚሰራ ታላላቅ ስራ) እንዳለ ነግሮናል ። እንግዲህ ምን እላለሁ ? ስለ ጌዴዎን ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶን ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነብያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛል ። እነርሱ በእምነት መንግስታትን ድል ነሱ።" ዕብ 11:32:33 (ኦርቶዶክስያ ገጽ -94 የመ/ር  ግርማ ከበደ  ትምህርታዊ ስብከቶች ስብስብ )

@mekra_abaw


“የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለኹና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችኹ፤ እላችኋለኹ፥ እንዲኹ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይኾናል፤ ... እንዲኹ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ #በእግዚአብሔር_መላእክት_ፊት ደስታ ይኾናል።” (ሉቃ. 15፥6-10)

በዘማሪ ሐዋዝና በሌሎቹም 70 ነፍሳት መመለስ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ገና ብዙ ነፍሳት ወደቤተክርስቲያን ይፈልሳሉ።🤩🥰 አንድ ወንድማችን የጻፈው ነው፤ ስለማረከኝ እንደወረደ አቅርቤዋለኹ። ‛አንድ ሰው ንስሐ ገባ ወደ አባቱ ቤት ተመለሰ ሲባል የክርስቲያኑን ሕዝብ ደስታ ግን አስተውላችኋል? እኛ በኃጢአት ያለነው ክርስቲያኖች እንደዚኽ ከተደሰትን በሰማይ ድል አድርገው በፍጹም ቅድስና ያሉት እንዴት ይደሰቱ ይኾን?’

“ይኽ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ኾኗል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቷልም። #ደስም_ይላቸው_ጀመር።” (ሉቃ. 15፥24)

@mekra_abaw✝️❤️🙏


#ኑ በብርሃኑ ተመላለሱ ✝️⛪✝️❤️❤️❤️🙏🙏🙏

የቀድሞው ዘማሪ ሐዋዝ ተገኝ ወደ ቀደመው የአባቱ ቤት ወደሆነችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት መቅደስ ተመልሷል
***

በተ*ዶሶ እንቅስቃሴ ላይ የነበረው የቀድሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘማሪ የነበረው ሐዋዝ ተገኝ

ቀድሞ ያገለግልባት ወደነበረችው ቅድስት እና ንጽሕት ወደሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ መቅደስ በንሰኃ ጥምቀት ተመልሷል።

ስለማይነገር ስጦታዉ እግዚአብሔር ይመስገን!!!
@mekra_abaw✝️❤️🙏


ደጅ ጠናሁ

ደጅ ጠናሁ ቆይቼ ኪዳነ ምህረትን
ተፅናናሁኝ ረሳሁ ሀዘኔንን
የአምላክ እናት እመቤታችን
ሞገስ ሁኝኝ ቀሪዉ ዘመኔን /2/

የመከራዉ ዘመን አለፈ እንደዋዛ
አንችን ተጠግቼ የአለሟን ቤዛ
የልጅሽ ቸርነት የአንችም ደግነት
ባርያሽን ሰወረኝ ከአስጨናቂዉ ሞት
እናቴ ስምሽን ስጠራ
አለፈ ያሁሉ መከራ
እንባዬ በፊትሽ ፈሰሰ
እምዬ በአንች እየታበሰ ሰላም ለኪ
አዝ

ልቤ በአንች ፀና ከፍ ከፍም አለ
በጥላቶቼም ላይ አፌ ተናገረ
በማዳንሽ ስራ ባሪያሽ ደስ ብሎኛል
የኃያላኑን ቀስት ልጅሽ ሰብሮልኛል
እናቴ ስምሽን ስጠራ
አለፈ ያሁሉ መከራ
እንባዬ በፊትሽ ፈሰሰ
እምዬ በአንች እየታበሰ ሰላም ለኪ
አዝ

እጄ ባዶ ሲሆን ወዳጆቼም ሸሹ
በመርገም ምክራቸዉ ሊለያዩኝ ሲሹ
እሱ የሰጠኝን እሱ ወሰደ አልኳቸዉ
እመቤቴ አለችኝ ብዬ አሳፈርኳቸዉ
እናቴ ስምሽን ስጠራ
አለፈ ያሁሉ መከራ
እንባዬ በፊትሽ ፈሰሰ
እምዬ በአንች እየታበሰ ሰላም ለኪ
አዝ

ከአዉደ ምህረቱ ሆኜ ስጠራት
ዘንበል ብላ አየችኝ ኪዳነ ምህረት
ሀሳብሽን ምንም የለም የሚመስለዉ
እረፍት ያገኘሁት እናቴ ባንቺ ነዉ
እናቴ ስምሽን ስጠራ
አለፈ ያሁሉ መከራ
እንባዬ በፊትሽ ፈሰሰ
እምዬ በአንች እየታበሰ ሰላም ለኪ

ቀሲስ እንግዳወርቅ በቀለ


 🕊  ጾመ ነቢያት   🕊    

🌟🌟🌟🌟🌟🌟🌟🌟🌟🌟🌟🌟

የጾመ ነብያት ምስጢር ምንድነው ?

✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨
    

ጾመ ነቢያት [ የገና ጾም ] ከልደት አስቀድሞ የሚጾም ጾም ነው፡፡ ከህዳር ፲፭ [ 15 ] ጀምሮ ለ ፵፫ [43] ቀናት የሚጾም ሲሆን ፋሲካው [ ፍቺው ] በልደት በዓል ነው፡፡ ይህም ጾም በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ ቅዱሳንና ምዕመናን ጾመውታል፡፡

ጾመ ነብያት ስያሜውን ያገኘው ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ስለተፈጸመበት ነው፡፡ በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በእምነት ዓይን እያዩ ምስጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ ፣ የረቀቀው ገዝፎ ጎልቶ እየተመለከቱ ትንቢት ተናገሩ ፤ ያዩትም መልካም ነገር እንዲደርስላቸው ጾሙ ጸለዩ፡፡

ነቢያት ከእመቤታችን ስለ መወለዱ ፥ ወደ ግብፅ ስለ መሰደዱ ፥ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለ መጠመቁ ፥ ብርሃን በሆነው ትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ ፥ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለመቀበሉና ስለ መሰቀሉ ፥ ስለ ትንሣኤው ፥ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፡፡

ለአዳም የተሠጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍፃሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን ተማፀኑትም እንጂ፡፡ በየዘመናቸው ፦ "አንሥእ ኃይልከ ፣ ፈኑ እዴከ" እያሉ ጮኹ፡፡ በጾምና በጸሎት ተወስነውም እግዚአብሔር ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት ፣ በሳምንታት ፣ በወራትና በዓመታት ቆጠሩ፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ሥጋዌው ትንቢት በተናገረ በ፬፵፮ ዓመት ጌታችን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኗል፡፡

ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር ፦ "አያደርገውን አይናገር የተናገረውን አያስቀር" ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ ለዘመነ ሥጋዌ ቅርብ የነበሩ እነ ነቢዩ ኢሳይያስ ጾሙ እንዴት መፈጸም እንዳለበት ተናግረዋልም፡፡ [ኢሳ.፶፰፥፩]፡፡ በመሆኑም በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት ስለተፈጸመበት ይህ ጾም "የነቢያት ጾም" ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት ስለሆነም "ጾመ ስብከት" ይባላል፡፡

ይህንን ጾም በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ ብዙ ቅዱሳን ጾመውታል፤ በዚህም ምክንያት የሚከተሉት ስያሜዎች አሉት፡፡ እነርሱም፦

† ፩. [    ጾመ አዳም   ] ፦

አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከገነት ከተባረረ በኋላ በፈጸመው በደል አዝኖ ፥ ተክዞ ፤ አለቀሰ [እንባ ቢያልቅበት እዥ እስከሚያፈስ ፤ እዥ ቢያልቅበት ደም በዓይኑ እስከሚፈስና ዓይኑ ይቡስ ወይም ደረቅ እስከሚሆን ድረስ አለቀሰ] ፥ ጾመ፣ ጸለየ፡፡ ከልብ የሆነ ጸጸቱን፣ ዕንባውን፣ በራሱ መፍረዱንም እግዚአብሔር አይቶ ተስፋ ድኅነት ሰጠው፡፡ "ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ፣ በደጅህ ድኼ ፣ በዕፀ መስቀል ተሰቅዬ፣ ሞቼ አድንሃለሁ፡፡" የሚል ነው፡፡ [ገላ. ፬፥፬፣ መጽ.ቀሌምንጦስ] ስለዚህ ጾሙ የተሰጠው ተስፋ ፥ የተቆጠረው ሱባኤ ስለተፈጸመበት "ጾመ አዳም" ይባላል፡፡

† ፪. [   ጾመ ነቢያት   ] ፦

ነቢያትም የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገለጦ ስለታያቸው ፣ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ በትንቢት ተመልክተው ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ይባላል፡፡ ይህ ጾም ከአባታችን አዳም እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ የተነሱ አበውና እናቶች : ድኅነትንና ረድኤትን ሲሹ የጾሙት ጾም ነው:: በተለይ አባታችን አዳም : ቅዱስ ሙሴ : ቅዱስ ኤልያስ ፣ ቅዱስ ዳንኤልና ቅዱስ ዳዊት በጾማቸው የተመሰከረላቸው ቅዱሳን ናቸው:: [ዘዳ.፱፥፲፱ ፣ ነገ.፲፱፥፰ ፣ ዳን.፱፥፫ መዝ.፷፰፥፲ ፻፰፥፳፬] ቅዱሳን ነቢያት በጭንቅ በመከራ ሆነው የጾሙት ጾም ወደ መንበረ ጸባኦት ደርሶ: ወልድን ከዙፋኑ ስቦታል:: ለሞትም አብቅቶታል::

† ፫.  [   ጾመ ሐዋርያት  ] ፦

ሐዋርያት "ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብራለን ፣ ልደትን ምን ሥራ ሠርተን እናከብረዋለን?" ብለው ከልደተ ክርስቶስ በፊት ያሉትን ፵፫ ዕለታት ጾመዋልና፡፡

† ፬.  [   ጾመ ማርያም   ] ፦

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ቅድስናዋን አይቶ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ወልደ አምላክን ያለ ሰስሎተ ድንግልና በግብረ መንፈስ ቅዱስ ጸንሳ እንደምትወልደው ቢነግራትም የትሕትና እናት ናትና "ምን ሠርቼ የሰማይና ምድርን ፈጣሪ እችለዋለሁ?" ብላ ጌታን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማለችና "ጾመ ማርያም" ይባላል፡፡

† ፭.  [   ጾመ ፊልጶስ   ] ፦

ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በአረማውያን ዘንድ ገብቶ እያስተማረ ሳለ በሰማዕትነት ሲሞት ፤ አስክሬኑ ከደቀመዛሙርቱ ስለተሰወረ ፤ እግዚአብሔር የተሰወረውን የመምህራቸውን አስክሬን እንዲገለጽላቸው ከኅዳር ፲፮ ጀምረው ጾመው በሦስተኛው ቀን የመምህራቸው አስክሬን ተመልሶላቸዋል፤ ነገር ግን አስከሬኑ ቢመለስላቸውም ጾሙን ግን እስከ ልደት ቀጥለዋል፡፡

† ፮.  [   ጾመ ስብከት  ] ፦

የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት ፥ የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት ፥ የምስራች የተነገረበት ስለሆነ ጾመ ስብከትም ይባላል፡፡

† ፯.  [   ጾመ ልደት   ] ፦

የጾሙ መጨረሻ [ መፍቻ ] በዓለ ልደት ስለሆነ "ጾመ ልደት" ይባላል፡፡

በጾማችን በጸሎታችን - ስለ ቤተክርስቲያን ፥ ስለ ሀገር እና ስለ ሕዝብ በማሰብ በእንባ እራሳችንን ዝቅ በማድረግ እንጾም ዘንድ ይገባል፡፡


ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፡ ወለወላዲቱ ድንግል ፡ ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

@mekra_abaw

5.4k 0 105 2 21
20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.

23 930

obunachilar
Kanal statistikasi
Kanalda mashhur

 🕊  ጾመ ነቢያት   🕊     🌟🌟🌟🌟🌟🌟🌟🌟🌟🌟🌟🌟 የጾመ ነብያት ምስጢር ምንድነው ? ✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨      ጾመ ነቢያት [ የገና ጾም ...
"📖አቤቱ ቸሩ መድኃኔዓለም ሆይ ቀኑን ባርከህ በሰላም  እንዳዋልከን ምሽቱንም ያንተው ቸርነት  ሳይርቅ በሰላም አሳድረን 📖 እንደ እኛ ክፋት ሳይሆን እንደ...
በአረፈበትም ጊዜ ጌታችን ወደርሱ መጥቶ እጆቹን በላዩ ጫነ ለሥጋውም መፍረስና መበስበስ እንዳያገኘው ኃይልን ሰጠው በአባቱ በያዕቆብም መቃበር አኖሩት። #...
እነዚህን በገናዎች በ6000 ሽ ብር ብቻ ከእኛ ጋር ያገኛሉ ። @habmisget ይዘዙን ክራር :መሰንቆ: ዋሸንት እስከ ቦርሳቸው ከእኛ ዘንድ ...
"ከሁለቱ የጽድቅ እንቅፋቶች እናስተውል"!        ፩.ጸድቄአለሁና        ፪. አልጸድቅም ጸላኤ ሠናያት ሰውን የሚጎዳበት ሁለት ወጥመዶች  አሉት...