ኮሎምበስን ከረሀብ የታደገች ግርዶሽ
**************************ከ500 ዓመታት በፊት ያጋጠመ ፈገግ የሚያሰኝ እውነተኛ ታሪክ ነው።
ብዙዎቻችን እንደምናውቀው ክርስቶፈር ኮሎምበስ ዝነኛ መርከበኛ ነበር። በዋናነትም 'አሜሪካን ለመጀመርያ ጊዜ ያገኛት ሰው' በሚል ይታወቃል። ያኔ የሁሉ ነገር እምብርት አውሮፓ ስለነበረች አሜሪካንን ማንም ነገሬ ብሎ አያውቃትም ነበር!!
ታዲያ ይሄ ትውልዱ ጣልያን የሆነ የስፔን መርከበኛ እንደተለመደው ከተቀጠረበት ሀገር ከስፔን ተነስቶ ዓለምን ሲዞር ሲያስስ ከአራቱ መርከቦቹ ሁለቱ በጉዞ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ ይሆኑበታል። ደግሞ ብቻውን አልነበረም፤ ብዙ ሰዎች አብረውት ነበሩ። የተቀሩት ሁለቱ መርከቦቹም በውቂያኖሱ ጨው እንጨታቸው እየተበላ በስብሰው አላስኬድ ማለት ሲጀምሩ ወደ አንድ ጠረፍ ተጠግተው ለማረፍ ግድ ሆነባቸው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ እነዚያ ተጓዦች ስንቃቸውም ማለቅ ጀመረ።
ያረፉበት ቦታ ያሁኑዋ ጃማይካ የምትገኝበት አካባቢ ነበር። መቸም ያካባቢው ሰዎች እንዴት ያሉ ደጋጎች ነበሩ መሰላችሁ፤ በጥሩ አቀባበል አስተናገዷቸው፤ የሚበሉትን ቀለብ፣ የሚለብሱትን ቃጫ መሰል ልብስ እና የሚያርፉበትን ድንኳን መሳይ ቤት ሰጧቸው። ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ይፈልጋሉ?!
ኮሎምበስና ጀሌዎቹ በዚህ መልኩ ያገራቸው መንግስት መርከብ ልኮ እስኪወስዳቸው ድረስ በጃማይካ በእንግድነት ለወራት ሲጠባበቁ ከረሙ። ታዲያ በቆይታቸው ወቅት ግጭት መፈጠር ጀመረ። ለነገሩስ እንኳን ሰውና ሰው ድንጋይ ከድንጋይ ይጋጭ የለ፤ የተደበቀ አመልም ቀስ በቀስ ይወጣል።
ጃማይካውያኑ ባስተናገዷቸው የኮለምበስ ጀሌዎች ሴቶቻቸውን መጎምጀት፣ ንብረታቸውን መዝረፍ፣ ያይኑ ቀለም ያላማራቸውን በቡጢ መጠለዝ ሲጀምሩ ግጭት ተፈጠረ። በዚሁ መነሾ ጃማይካውያኑ ምግብና መጠጥ ከለከሏቸው። ኮሎምበስ ጨነቀው! ሰዎቹ በርሀብ ሊያልቁበት ሆነ። መፍትሄ ፍለጋ ሲያወጣ ሲያወርድ ቆይቶ አንድ ዘዴ መጣለት።
የዚያን እለት ማታ ከአካባቢው ሰዎች እና የጎሳ መሪው ጋር ቀጠሮ ያዘ። እናም ሲመጡ፣
"በምግብ እየቀጣችሁን በመሆኑ እግዚአብሔር ተቆጥቷል። ቁጣ እንደሚያወርድባችሁም ነግሮኛል። ዛሬ ማታ ጨረቃዋን በማንደድ ቁጣውንም ያሳያችሁዋል" አላቸው።
ይሄን ንግግር ሲሰሙ ከመደንገጥ ይልቅ ሰዎቹ ተሳለቁበት። የጎሳውም መሪ አላመነውም፤ በፍጹም ሊሸወድለት አልፈቀደም። እናም 'ሞኝህን ፈልግ' ሲል መለሰለት።
ደቂቃዎች ተቆጠሩ፤ ኮሎምበስና ጓደኞቹ በተስፋ እየጠበቁ ነው፤ ቀኑን ሙሉ ምግብ ባፋቸው ስላልዞረ በርሃብ ተጎሳቁለዋል፤ አንዴ መሽቶ ጨረቃ ከተራራው ጀርባ ወጥታ የሚበሉትን ነገር እስኪያገኙ ድረስ የዓመት ያህል ረዘመባቸው።
በመጨረሻም ጨረቃ ወጣች።
ጃማይካውያኑ ጨረቃን ሲያይዋት በፍርሀት ይርዱ ጀመር። በጣም ተደናገጡ። እንደተባለው ጨረቃ ደም ለብሳለች። ደሞም ከጎን በኩል የሆነ ነገር የገመጣት ትመስላለች። ያካቢው ነዋሪዎች ተሸበሩ፤ የሚያደርጉት ነገር ጠፋቸው።
ቢጨንቃቸው ኮሎምበስን መለመን ጀመሩ። ከፈጣሪ ቁጣ እንዲገላግላቸው ተማጸኑት። የጠየቃቸውን ምግብና መጠለያ እንደሚሰጡትም ቃል ገቡለት። ቅድም 'ሞኝህን ፈልግ' ሲል በኮሎምበስ የተሳለቀው ያ የጎሳ መሪ በተረበሸ ስሜት ሆኖ የተማጽኖ ድምጹን አሰማ።
"የፈለከውን ያህል ምግብ ላንተና ለጓደኞችህ መውሰድ ትችላለህ፤ ብትፈልግ ቤታችንን እንለቅልሃለን፤ አገልጋዮችም እንመድብልሃለን፤ ብቻ ከፈጣሪ አስታርቀን!" አለው።
ከብዙ ልመናና ጉትጎታ በሁዋላ ኮሎምበስ ተናገረ።
"እስኪ ፈጣሪ ከሰማኝ ጸሎት ላድርስ" አለና ወደ ድንኳኑ ገብቶ ቆየ።
ኮሎምበስ፣ ከዓመታት በፊት ጀርመናዊው የስነ-ክዋክብት አጥኝ ቮን ኮኒስበርግ ያዘጋጀውን የአስትሮኖሚ ሰንጠረዥ አንብቧል። ስለዚህም በዚያን እለት፣ የካቲት 29 1504 ዓ.ም (እ.አ.አ)፣ ለ48 ደቂቃ የሚቆይ የጨረቃ ግርዶሽ እንደሚያጋጥም ቀድሞ ያውቅ ነበር። እናም ወደ ድንኳኑ ገብቶ ያንን የአስትሮኖሚ ሰንጠረዥ ተመልክቶ የጨረቃው ግርዶሽ የሚያበቃበትን ትክክለኛ ደቂቃ ካልኩሌት አድጎ አረጋገጠ። ከዚያም ሁለት ደቂቃ ያህል ቀድሞ ወደ ጃማይካውያኑ ተመለሰና፣
"እግዚአብሔር ጸሎቴን ሰምቷል፤ ምህረት እንደሚያደርግላችሁም ነግሮኛል" አላቸው።
ወዲያው ጨረቃ በደም የተነከረ ክንብንቧን አወለቀች። ይሄን ጊዜ ያካባቢው ነዋሪዎች በእንባ ተሞልተው "ክብር ለፈጣሪ ይሁን" እያሉ ጨፈሩ። ኮሎምበስም በፈገግታ ተሞልቶ "ክብር ለሣይንስ" አለ፤ በሆዱ ነው ታዲያ።
በዚህ መልኩ ኮሎምበስና ጓደኞቹ ያካባቢው ሰዎች ሸውድው ምቹ መኝታና መጠለያ ከብዙ ምግብና መጠጥ ጋር አግኝተው ቆዩ። ከሦስት ወር በሁዋላም የስፔን መንግስት መርከበኛ ልኮ ወደ ሀገራቸው እስኪመልሳቸው ድረስ የጨረቃ ግርዶሽን እያመሰገኑ ተቀማጥለው ኖሩ።
(©መሳፍንት ተፈራ፣ ሰኔ 2012 ዓ.ም)
👉 በነገራችን ላይ ቆየት ያሉና ከገበያ የጠፉ መጽሐፍትን ማግኘት ከፈለጉ ቀጣዩን ቴሌግራም ይቀላቀሉ፣ ሜክሲኮ አምደ መጻሕፍት በማፋለግ ይረዳዎታል!!
https://t.me/mexibooks