የካቲት ፳፩ /21/
በዚችም ዕለት የከበረ የሐዋርያው የጳውሎስ ደቀ መዝሙር የሆነ ቅዱስ አናሲሞስ በሰማዕትነት አረፈ።
ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ፊልሞና ለሚባል ለሮሜ ሰው አገልጋይ ነበር። ሰይጣን የአናሲሞስን ልቡ ለወጠና የጌታውን ገንዘብ ሰርቆ ወደ ሮሜ ሔደ።
በእግዚአብሔርም ፈቃድ ወደከበረ ሐዋርያ ጳውሎስ ሔደ ትምህርቱንም ሰምቶ በክብርባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ ለቅዱስ ጳውሎስም ደቀ መዝሙሩ ሆነ። ነገር ግን የጌታውን ገንዘብ በመስረቁ በአናሲሞስ ልብ ጽኑ ሀዘን አደረ ለሐዋርያ ጳውሎስም የሠራውን ሁሉ ነገረው ሐዋርያ ጳውሎስም አትፍራ ልብህም አይዘን አለው የቀድሞ ጌታው በሰላም እንዲቀበለው ወደ ፊልሞናም መልእክትን ጻፈለት ይቺም ስለ አናሲሞስ የጻፋት ከመልእክቶቹ አንዲቱ ናት።
ይህ የከበረ አናሲሞስም ወደ ፊልሞና ወደ ጌታው በደረሰ ጊዜ በማመኑና በመጸጸቱ ደስ አለው ሐዋርያው እንዳዘዘውም ተቀበለው። ከዚህም በኋላ ሸኙትና ወደ ሮሜ አገር ተመለሰ በሰማዕትነት እስከ ሚሞትበት ጊዜ ሐዋርያ ጳውሎስን የሚያገለግልው ሆነ።
ከሐዋርያው ጳውሎስም የምስክርነት ሞት በኋላ የንጉሥ ጭፍራ ይህን ቅዱስ ይዞ ወደ አንዲት ደሴት ሰደደው በዚያም ያሉትን አስተምሮ አጠመቃቸው። ያ ጭፍራም ይህን በሰማ ግዜ በብዙ አሰቃይቶት በዚች ቀን ምስክርነቱንም ፈጸመ። የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር