እውቀትና የእውቀት ባለቤቶች ደረጃ ክፍል - 24 ነብዩ ﷺ ከማይጠቅም እውቀት በአላህ ﷻ መጠበቃቸው ሙስሊም በዘገበው ትክክለኛ ሐዲስ ዘይደ ብን አርቀም የሚከተለውን ተናግሯል:-
"እኔ የአላህ መልእክተኛ ﷺ የተናገሩትን እንጅ ሌላ አልነግራችሁም።
ረሱል ﷺ የሚከተለው ሀዲስ ተናግረዋል :-
"
اللهم إني أعوذ بك من العجز والكسل ، والجبن والبخل ، والهرم وعذاب القبر ، أللهم آت نفسي تقواها ، وزكها أنت من زكاها ، أنت وليها ومولاها ، اللهم إني أعوذ بك من علم لا ينفع ، ومن قلب لا يخشع ، ومن نفس لا تشبع ، ومن دعوة لا يستجاب لها" "አላህ ሆይ! ከድክመት ፣ ከስንፍና ፣ ከፍርሃት ፣ ከስስት ፣ ከእርጅና ፣ ከቀብር ቅጣት በአንተ እጠበቃለሁ ፤ አላህ ሆይ! ለነፍሴ ፍርሃቷን ስጣት ፣ አጥራት ከአጥሪዎች በላጭ ነህና ፣ አንተ ረዳቷ ጠባቂዋ ነህ ፤ አላህ ሆይ እኔ ከማይጠቅም እውቀት ፣ ከማይፈራ ልቦና ፣ ከማትጠግብ ነፍስ ከአንተ ዘንድ ተቀባይነት ከሌለው ዱዓ በአንተ እጠበቃለሁ፡፡” እውቀት በዚህ አለምም ይሁን በወዲያኛው ለባለቤቱ ጠቃሚ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም። ይህን ስንል ያለምክንያት አይደለም ባለቤቱን ከዚህ አለም ብልጭልጭ ሂዎት እንዲርቅ ፣ የአላህን ውዴታ በሚያስገኙ ተግባራት እንዲጠመድ የሚያደርግ በመሆኑ ነው። ጠቃሚ እውቀት ከተለያዩ የዚህ አለም ጭንቀቶች ፣ ሀሳቦችና የልቦና መደፍረስ የሚገላግል መሆኑ ነው ፡፡
በመሆኑም ሙእሚን አውቆ ሰዎችን ለማሳወቅ እንቅስቃሴ ከማድረጉ በፊት ከአላህ የሚገኘውን ምንዳ ታሳቢ ማድረግ አለበት። ሸሪዓዊ እውቀትን የተማረ ሰው በተማረው መስራት አለበት፡፡ ምክንያቱም የእውቀት ፍሬው ፣ ውጤቱና ትሩፋቱ ተግባር ነው፡፡ ከእርሱ ዘንድ ባለው ጠቃሚ እውቀት የማይሰራ ፣ አላህ ባዘዘው የማይተገብር ፣ ከከለከለው የማይከለከል ትክክለኛ አሊም አይደለም፡፡ ምሳሌው :- ልክ ፍሬ እንደማያፈራ ዛፍ ማለት ነው፡፡ የመማሩ አላማና ግብ በእርሷ ለመጠቀም ነው፡፡ በተማረው ትምህርት ካልተጠቀመ በእርሱ ላይ ጥፋት እና ኪሳራ ሆኖ ይመለስበታል። ለዚህ ነው ረሱል ﷺ ከማይጠቅም እወቀት ዘወትር በአላህ የሚጠበቁት።
እውቀት ያለተግባር የቂያማ ቀን በባለቤቱ ላይ ጸጸት ሆኖ ይመለሳል። በተማረው ትምህርት የማይሰራ ነገ ከአላህ ፊት ከሳሽ ሆኖ ይቀርብበታል፡፡ የሚያቀርበው ምንም አይነት ምክንያት አይኖረውም።
ሀፊዝ ብን ሀጀር ከሱፍያን አስሰውርይ ነቅሎ የሚከተለውን አስተላልፏል ፡ "أول العلم الاستماع ، ثم .... ، ثم الحفظ ، ثم العمل ، ثم النشر" “የእውቀት መጀመሪያው ማድመጥ ነው ፣ ከዚያም... ከዚያም ሂፍዝ ነው ፣ ከዚያም ተግባር ነው ፣ ከዚያም ማሰራጨት ነው፤” ከላይ የተመለከትነው የረሱል ﷺ ሐዲስ ጠቃሚ እውቀትን በመማርና ህብተሰብን በማስተማር ላይ ኡመቱን የሚያነሳሳ ነው፡፡
"علم لا ينفع" "የማይጠቅም እውቀት" ለባለቤቱም ለማህበረሰቡም የማይጠቅም የሆነው እውቀት ነው፡፡ ለዱንያም ለአኼራም የማይጠቅም እውቀት ነው፡፡ ከአላህ ፍራቻ የተራቆተ እወቀት ነው። ለሰዎች የማያስተምረው እራሱም የማይሰራበት እውቀት ነው፡፡ ስነምግባርን ፣ ንግግርን ተግባርን ለመቀየር ድርሻ የሌለው እውቀት ነው፡፡ ወደሰውየው ልቦና በረካው የማይደርስ እውቀት ነው፡፡ አንዳንድ አሊሞች እንዲህ አይነቱ እውቀት የኮከብ ቆጠራ (የጥንቆላ) ፣ የድግምት እና የፍልስፍና እውቀት ነው ብለውታል።
ጠቃሚ እወቀት ማለት አላህን መፍራት ነው፡፡ ፋሲቆች ፣ ጠማማዎች እና ዚንዲቆች የተሸከሙት እውቀት እውቀት አይባልም። እውቀት ማለት ፍትሀዊ ሀቀኛ የሆኑ አካላት የተሸከሙት እውቀት ነው። አሊሞችን ለመከራከር ወይም ጃሂሎችን ለመከራከር ወይም የሰዎችን ፊት ወደርሱ ለማዞር ዝና ለማግኘት ዶክተር ለመባል ፕሮፌሰር ለመባል አላማ የተደረገበት እውቀት እውቀት አይደለም። በዚህ አላማው አላህ እሳት ያስገባዋል፡፡ እውቀት ብሎ ማለት የዱንያን ፍቅር የሚቀንስ የአላህን ፍራቻ የሚጨምር ነው፡፡ ማንኛውም ወደ አላህ እምነት የማያደርስ ፣ በእርሱ መመካትን የማያስገኝ ለአኼራ ትኩረትን የማይጨምር እውቀት እውቀት አይባልም።
ሸውካኒ ከላይ ያሳለፍነውን ሐዲስ አስመልክቶ የሚከተለውን ትንታኔ ሰጠዋል ፡
“የአላህ መልክተኛ ﷺ እውቀትን በጠቃሚነቱ ፣ ሲሳይን ደግሞ በመልካምነቱ፣ ተግባርን ደግሞ በተቀባይነቱ የገደቡት ማንኛውም የማይጠቅም እውቀት ከአኼራ ተግባር ባለመሆኑ፣ ለጥመት በር የሚከፍት በመሆኑ ነው፡፡” ለዚህ ነው ረሱል ﷺ ከማይጠቅም እውቀት የተጠበቁት፡፡ መልካም ያልሆነ ሲሳይም ከቅጣት አያድንም፡፡ ማንኛውም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነፍስን በማይጠቅም ነገር ማልፋት ነው፡፡
የአውነል መእቡድ ባለቤት ከአቡ ጦይብ አልመኪይ የሚከተለውን ነቅሎ አስተላልፏል
“ ረሱል ﷺ ከሽርክ ከንፍቅና ከመጥፎ ስነምግባር አንደተጠበቁ ሁሉ ከማይጠቅሙ የእውቀት አይነቶችም ተጠብቀዋል ..." በረሱል ﷺ ዘመን አይሁዶች ሙሀመድ ﷺ የአላህ መልክተኛ መሆናቸውን ያውቁ ነበር። ነገር ግን ይህ እውቀታቸው አልጠቀማቸውም - ምክነያቱም ሁለቱ የምሰክርነት ቃሎች በሚያስፈርዱት አልሰሩምና፡፡: በአላህ አምነናል ብለው ቢሞገቱም ፣ በረሱል ﷺ መልእክተኛነት ባለማመናቸው በአላህ ማመናቸው አልጠቀማቸውም።
ጠቃሚ ካልሆኑ እውቀቶች መገለጫ ሰውየው በእውቀቱ ኩራትን ፣ የበላይነትን ፣ በዱንያ ፉክክርን የሚፈልግበት እውቀት ነው። ኡለሞችንም ይሁን ጃሂሎችን ለመከራከር ፣ የሰዎችን ፊት ወደርሱ ለማዞር ፣ ሀቅን ላለመቀበል ፣ ለሀቅ ተጎታች ላለመሆን አላማ የተደረገበት እውቀት ነው። እውቀት ማለት በንግግር ብዛት ወይም ንግግርን በማሳመር አይደለም። ጠቃሚ እውቀት ማለት ሀቅን ከባጢል ለመለየት የሚያስችል ከልብ ውስጥ የሚጣል የአላህ ብርሃን ነው።
በአንጻሩ የጠቃሚ እውቀት ባለቤቶች መገለጫ :
ውዳሴን የማይወዱ ፣ ወደርሱ የሚያደርሱ ነገሮችን የሚጠነቀቁ ፣ በእውቀታቸው በሰዎች ላይ የማይኮሩ ፣ በእውቀታቸው ወደ ዱንያ ፍላጎት እና ስልጣን ለመድረስ የማይጓጉ ናቸው። አላህ ሽቶላቸው ከነዚህ ነገሮች አንዳች ቢያገኙ እንኳ ለዲናቸው አጋዥ ያደርጉታል እንጅ ከአላማቸው ዝንፍ አያደርጋቸውም ፤ ባህሪያቸውንም አይቀይረውም። የአላህን ውዴታ ለማግኘት ፣ በጀነት ለመጎናጸፍ ፣ ከእሳት ነጻ ለመውጣት ሰበብ አድርገው ይጠቀሙበታል። ይህ ታላቅ ድል፡፡ ጠቃሚ እውቀት በቅድሚያ ሰውየው እራሱን ከጅህልና ለማውጣት ከዚያም ማህበረሰቡን ለመቀየር የሚማረው ነው።
ጠቃሚ እወቀት በሁለት ነገሮች ይታወቃል : አንደኛው ፡ አላህን ማላቅ ፣ ከፍ ማድረግ ፣ እርሱን መፍራት ፣ ማክበር ፣ በእርሱ ብቻ መመካት ፣ ቀዷእና ቀደርን መውደድ ፣ በመጣው መከራ መታገስ
ሁለተኛው ፡ ከእምነቶች ፣ ከንግግሮች ፣ ከተግባሮች አላህ የወደደውን መውደድ።
https://t.me/alateriqilhaq كن على بصيرة